የኢትዮጵያን ፍላጎት የሚጻረረውን የትሕነግን ጠማማ ቅዠት ማክሸፍ የሚቻለው ‘ተው’ እያሉ በማባበል ሳይሆን እንደ አዳነች አቤቤ ‘ሞክረው’ በማለት ነው!
(አሳዬ ደርቤ ለድሬ ቲዩብ)
ትሕነግ ከተባለ አሸባሪ ድርጅት ጋር ወደ ጦርነት ከገባን ድፍን አንድ ዓመት የሞላን ቢሆንም ህወሓትን በተመለከተ ምንም አይነት ቃላት ተንፍሰው የማያውቁ እልፍ አእላፍ የብልጽግና አመራሮች አሉ፡፡ ‹‹የተከበሩ›› በሚል ማዕረግ መንግሥት የሠጣቸውን ቪ8 መኪና እያሽከረከሩና በተንጣለለ ቪላ ቤት ውስጥ እየኖሩ ድምጻቸውን አጥፍተው የህወሓትን ኮቴ የሚያዳምጡ አመራሮች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ ለዚያም ነው አሸባሪው መግለጫ ባወጣ ቁጥር አንደ ገዥ ፓርቲ ብልጽግናን በጠላትነት በመፈረጅ ፈንታ የተወሰኑ አመራሮችን በሥም እየጠራ ‹‹ጠቤ ከእነ እንትና ጋር ነው›› የሚለው…
በሌላ መልኩ ደግሞ አንዳንድ የመንግሥት አመራሮች አሉ አገር በመታደግ ትግሉ ውስጥ ጥርት ባለ አቋም ተሰልፈው ዘመቻውን ሲያስተባብሩና የህወሓትን ቀብር ሲቆፍሩ የሚታዩ፡፡ ከእነዚህም አመራሮች መሃከል ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አንዷ ስትሆን በባለፉት ጊዜያት ወረራ ለተፈጸመባቸው ክልሎች የበጀት ድጋፍ በማድረግ፣ ለመከላከያ ሠራዊቱ ስንቅ በማቅረብ፣ ጁንታውንና አለቆቹን ተስፋ የሚያስቆርጡ ሰልፎችን በማስተባበር፣ በአዲስ አበባ ጉያ ውስጥ ሸምቆ የደሴውን አይነት ሽብር ለመፍጠር የተዘጋጀውን ሲቪል ለባሽ የአሸባሪ ክንፍ በመቆጣጠር፣ በአደባባይም ሆነ በሚዲያ ንግግሮቿ የህወሓትን ቅስም በመሰባበር ከፍተኛ ሚና ስትጫወት ነበር፡፡
ባለፉት ጊዜያት የመንግሥትን ወንበር ይዘው ከአማጺያን ጋር የሚማግጡ፣ ሥልጣናቸውን እና ጥቅማቸውን የሙጥኝ ብለው ከእነ አሜሪካ ዐይን ላለመግባት የሚጠነቀቁ ብሎም ሁለት አይነት ማሊያና ጭንብል ያጠለቁ አመራሮችን እንዳየነው ሁሉ ከውጭ ሃይሎችና ሚዲያዎች ጋር በሚደረገው ትግል ውስጥ ወይዘሮ ቤልለኔ ሥዩም ፣ ከውስጣዊው አሸባሪ ጋር በሚደረገው ትግል ውስጥ ደግሞ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከፍተኛ ተጋድሎ ሲያደርጉ ታዝበናል፡፡
ከዚህም ጋር ተያያዞ በቅርቡ ከንቲባዋ ባደረጉት ንግግር ‹‹ትሕነግ ክልሉን ለመገንጠል የሚፈልግ ከሆነ እራሱ በጻፈው ሕገ-መንግሥት ሕዝበ ውሳኔ አካሂዶ ዓላማውን ማሳካት እንጂ ኢትዮጵያን ማፍረስና መከላከያ ሠራዊታችንን መደምሰስ አያስፈልገውም›› በማለት ተናግረዋል፡፡ በዚህም ንግግራቸው ‹‹ክልሌን እገነጥላለሁ›› እያለ ሲፎክር የከረመው አሸባሪ በደጋፊዎቹና በተላላኪዎቹ አማካኝነት እልልታውን በመግለጽ ፈንታ ቁጣውን ሲያሰማ ተስተውሏል፡፡ አንዳንድ አርቆ አሳቢና ቅርብ አዳሪ ኢትዮጵያውያንም ‹‹እንዴት እንዲህ ይባላል›› የሚል ቅሬታቸውን ሲገልጹ ተሰምተዋል፡፡
በበኩሌ ግን ህወሓት ከአፈጣጠሩ ጀምሮ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያውያን ፍላጎት በተቃራኒው የሚያስብ ጠማማ ድርጅት እንደመሆኑ መጠን ለይስሙላም ቢሆን የመገንጠል ፉከራውን እንዲያስቀጥል የሚያደርገው ‹‹ማን ፈቅዶልህ›› የሚለው ክልከላ እንጂ ‹‹መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ›› የሚለው ይሁንታ አይመስለኝም፡፡
ከዚህ ባለፈ ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያን መብላት ካልቻልኩ ልበትናት ይገባል›› በሚል አቋም ወደ ወረራ የገባው አሸባሪ እንደ መዥገር አገራችን ላይ ተጣብቆ ደሟን መምጠጡን መተው ባይችልም በእራሱ ውሳኔ ትግራይ የተባለች አገር ከመሠረተ ግን ሦስት ድፍን ዓመታት አልፎታል፡፡ ትግራይን እንደ አገራችን ቆጥረን አል-ነጃሺ ሄደን ሦላት መስገድ ወይንም ደግሞ ታቦተ ጽዮን ተገኝተን ስለት መሳል ይቅርና በትውልድ መንደራችን መኖር ከከለከለን ቆዬ፡፡
ከመንግሥትም ሆነ ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ውጭ የሆነች ክልል መፍጠሩ አልበቃው ብሎ‹‹ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ብሔር ብሔረሰቦች በታትኜ ሰማንያ አገሮች አደርጋለሁ›› በሚል ቅዠት የትጥቅ ትግል ማድረግ ከጀመረ አንድ ዓመት አለፈው፡፡ በአገራዊ እሳቤ ትግራይን ላለማጣት ስንጠነቀቅ ወሎን ከወሎየዎች፣ አፋርን ከአፋሮች፣ ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያኖች በመንጠቅ ‹‹በአገራቸው የሚኖሩ ዜጎች›› መባሉ ቀርቶ ‹‹ከትውልድ ቀያቸው የተሰደዱ ተፈናቃዮች›› የሚል ዜና መስማት ከጀመርን ቆየን፡፡
ስለሆነም ‹‹ የአራት ኪሎን ዙፋን መቆጣጠር›› ወይም ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያን በታትኖ መቅበር›› በሚል ውሳኔ ወረራ ፈጽሞ ምድራዊ ሲዖል የሆነች አገር ለመፍጠር ሲሞክር በጀግኖች ልጆቿ ክንድ ተደቁሶ ሁለቱም እቅዱ የከሸፈበት አሸባሪ በሽንፈትና በደም ፍላት መንፈስ ወደ ‹‹ግንጠላ ሽለላው›› ተመልሶ ሲያስፈራራ ‹‹ተው›› በማለት ፈንታ እንደ አዳነች አበቤ ‹‹ሞክረው›› በማለት ብቻ ነው ፉከራውን ማኮላሸት የሚቻለው፡፡ ‹‹ትግራይን አገር አድርጎ ሕዝቧን ማብላት እና ኢትዮጵያን በጠላትነት ፈርጆ ሕዝቧን ማባላት የተለያዩ ነገሮች ቢሆኑም የመገንጠል ዛቻህን የሚቀበል ሕዝብ ካገኘህ ሞክረው›› ማለት ብቻ ነው መፍትሔው፡፡
በተረፈ ‹‹አማራን እና አፋርን አስገብሬ አራት ኪሎን እቆጣጠራለሁ›› በሚል ፕሮፖጋንዳ ከጦር ሜዳ ያስገባውን ቁጥር ስፍር የለሽ ወጣት እና ታዳጊ ሕጻናት ግብዓተ መሬት የፈጸመው ቡድን ወደ መቀሌ ተመልሶ ‹‹ክልሌን እገነጥላለሁ›› የሚል እቅዱን ሲናገር ‹‹ልጆቻችንን አምጣ›› በሚል ቁጣ እጅና እግሩን የሚገነጣጥለው ሕዝብ እንጂ ለሪፍረንደም የሚወጣ ሕዝብ ያገኛል ተብሎ አይታሰብም፡፡
የሽብር ቡድኑም ይሄንን ስለሚያውቅ ነው መደ መቀሌ ተመልሶ ሕዝበ ውሳኔ ከማድረግ ይልቅ ሚሌን መያዝ ዋነኛ ሕልሙ አድርጎ ሕዝቡን መጨረስ የመረጠው፡፡ ክልሉን አገር ከማድረጉና ስለ ሪፍረንደም ከማውራቱ በፊት ‹‹ህውሓት ይውደም›› የሚሉ ወላጆች ትግራይ ላይ እንደሚቀብሩት ስለሚያውቅ ነው ወደኋላ ከመመለስ ይልቅ ወደ ፊት እየተጓዘ መደምሰስን ምርጫው ያደረገው፡፡
ሚሌ ላይ መሰዋት የፈለገው መቀሌ ላይ የሚጠብቀው ሕይወት ስለሌለ ነው፡፡ ሸዋ ላይ መቀበር ያሻው አድዋ ላይ መኖር ስለማይችል ነው፡፡ ስለሆነም ከኢትዮጵያኖች የሚጠበቀው በክልሎች ላይ ወረራ ፈጽሞ የሚቅበዘበዘውን አሸባሪ ወደ መቃብሩና ወደ ትውልድ መንደሩ መሸኘት ብቻ ነው፡፡ ያን ጊዜ ደብረ ጽዮን እና ጌታቸው ረዳ ገነጣጥሎ የሚቀብራቸው ሕዝባዊ ማዕበል እንጂ የሚገነጥሉት ክልል አይኖራቸውም፡፡
ይሄው ነው!