Connect with us

ትዳራቸውን አፍርሰውና ቤተሰባቸውን በትነው ሲጨርሱ ከአገር አፍራሹ አሸባሪ ጋር ጋብቻ መፈጸም ለሚሹ ሕይወት አልባ ፖለቲከኞች

ትዳራቸውን አፍርሰውና ቤተሰባቸውን በትነው ሲጨርሱ ከአገር አፍራሹ አሸባሪ ጋር ጋብቻ መፈጸም ለሚሹ ሕይወት አልባ ፖለቲከኞች
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ትዳራቸውን አፍርሰውና ቤተሰባቸውን በትነው ሲጨርሱ ከአገር አፍራሹ አሸባሪ ጋር ጋብቻ መፈጸም ለሚሹ ሕይወት አልባ ፖለቲከኞች

ትዳራቸውን አፍርሰውና ቤተሰባቸውን በትነው ሲጨርሱ ከአገር አፍራሹ አሸባሪ ጋር ጋብቻ መፈጸም ለሚሹ ሕይወት አልባ ፖለቲከኞች

(አሳዬ ደርቤ ለድሬ ቲዩብ)

በ2010 ዓ.ም ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መልኩ የሥልጣን ርክክብ የተደረገው በአቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝና በዶክተር ዐቢይ መሃከል እንጂ በህውሓትና በኢሕአዴግ መሃከል አልነበረም፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ለውጥ ከተደረገ በኋላም በህውሓት ተይዞ የነበረውን ሥልጣን በሌሎች ለመተካት ሲሞከር አሮጌ ጅቦቹ አራስ ነብር ሆነው አረፉ፡፡ ሳይወዱ በግዳቸው አራት ኪሎን እና አዲስ አበባን አስረክበው ወደ መቀሌ ከፈረጠጡ በኋላም ሰሜን እዝን በማገት ሽግግሩን አደናቀፉ፡፡ ከኦሕድድ እና ከብአዴን ጋር አብረው በመሥራት ፈንታም ከኤርትራ የገባውን የኦነግ ሠራዊት ፈረስ በሚያስጋልብ ዳስ ውስጥ ደግሰው በመቀበል አንገት ለአንገት ተቃቀፉ፡፡

ከዚያ በኋላም ኢሕአዴግ ሥሙን ቀይሮ ብልጽግና ለመሆን ሲሞክር ከፓርቲው ተገንጥለው ‹‹ደህንነት›› በሚል ሥም ጌታቸው አሰፋ በአገር ደረጃ የዘረጋውን የጥፋት መዋቅር በመጠቀም ኢትዮጵያን ማተራመሳቸውን ቀጠሉ፡፡ 

ለሁለት ዓመታት ያክልም ፍጹም ሰላማዊ በሆነችው የመቀሌ ከተማ ውስጥ ሁለተኛ ሕገወጥ መንግሥት ሆነው ኢትዮጵያን ሲያምሱ ከከረሙ በኋላ፣ መንገድ ዘግተው ካስቀሩት የሰሜን እዝ ሠራዊት ላይ መብረቃዊ ጥቃት በመፈጸም ለብልጽግና ያስረከቧትን የአዲስ አበባ ከተማ ለመቆጣጠር በቅራቅርና በራያ በኩል ጉዞ ጀመሩ፡፡

ስለሆነም ባለፈው አንድ ዓመት ሲደረግ የነበረውና አሁንም እየተደረገ ያለው ጦርነት በህውሓት መቃብር ላይ እውነተኛ የሥርዓት ሽግግር ማድረግን ታሳቢ ያደረገና ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በቄሮና በፋኖ ሲደረግ የነበረው የትግል አካል እንጂ ሌላ አይነት ትርጉም የሚሠጠው አይደለም፡፡ ምንም እንኳን በትግሉ መሃከል ትግራይን እና አንዳንድ ዞኖችን ያላካተተ አገራዊ ምርጫ ቢደረግም አሁንም ድረስ ኢትዮጵያኖች በምርጫው ማግሥት ወረራ ከፈጸመውና በካርድ ፈንታ በባሩድ ትግል ፈላጭ ቆራጭነቱን ማስቀጠል ከሚሻው የቀድሞው ሥርዓት ጋር ግብግብ እንደገጠሙ ናቸው፡፡ 

አሁንም ድረስ በልዩ ሃይልነትና በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ የታቀፉ የአማራ፣ የአፋር፣ የኦሮሞ፣ የደቡብ፣ የሶማሌ… ወጣቶች ህውሓትን በማስወገድ ሂደት ላይ ናቸው፡፡ ‹‹ከአራት ኪሎ የተባረረው የሽብር ቡድን ከኢትዮጵያ ምድር ካልተወገደ በስተቀር ለውጥ የሚባል ነገር አይታሰብም›› በሚል እምነት ዛሬም ፋኖዎች ትግል ላይ ናቸው፡፡ ህውሓቶችም ቢሆኑ ዋነኛ ጠባቸውን ከዶክተር ዐቢይና ከጥቂት አመራሮች ጋር ያደረጉት የሥልጣን ርክክብ የተደረገው በጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ እንጂ በመዋቅር ደረጃ አለመሆኑን ስለሚያዉቁ ነው፡፡

ሐቁ ይሄ ቢሆንም ታዲያ እድሜ ያነቀዛቸው አንዳንድ ቁሞ ቀር ፖለቲከኞች በህውሓትና በመንግሥት መሃከል የሥልጣን ሽግግር ከተደረገ በኋላ ለውጡ እንደተደናቀፈ ያስባሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር ዳር ተነቃንቆ ከጥፋት ወንበሩ ወደ መቃብሩ ሊያወርደው ‘ሆ’ ብሎ የዘመተበትን የሽብር ቡድን ወደ አራት ኪሎ ግቢ ለማምጣት ሲሞክሩ ይታያሉ፡፡

ከዚህም ጋር በተገናኘም ባለፈው በሀገረ አሜሪካ በዘጠኝ ግለሰቦች የተመሠረቱ ዘጠኝ ፓርቲዎች ከህውሓት ጋር ጥምረት ፈጠሩ የሚል ዜና ቀርቦልናል፡፡ እኒህም ዘጠኝ ፓርቲዎች የተመሠረቱበት እና የተዋሃዱበት ቅጽበት ከፓስታ እና ከስጎ መፍጠኑን የታዘቡ ዜጎች እንዲህ በሚል ሥም ንቅናቄውን ሲጠሩት ሰምተን በእጅጉ ስቀናል፡፡

‹‹የኤትዮጵያ ንኮች እና ዶካዎች ሚና የለሽ ንቅናቄ (ኢንዶሚን)

በቅርቡ ደግሞ ዶክተር ደጺ ‹‹በትግራይ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸሙን አምነው እውቅና ከሚሠጡ የአማራ ፖለቲከኞች ጋር የሽግግር መንግሥት መመሥረት እንፈልጋለን›› የሚል ማስታወቂያ ማውጣቱን የሰሙ አንዳንድ ቁሞ ቀር ፖለቲከኞች ሲቪያቸውን ለማቅረብ ዱብ ዱብ እያሉ ነው፡፡

ምንም እንኳን በጀግኖች ክንድ በመደቆስ ላይ የሚገኘው አሸባሪ የዙፋን ምኞቱን ትቶ የሬሳ ሳጥን የሚያገኝበትን መንገድ በመፈለግ ላይ ቢሆንም… በተለያዩ ጊዜ በሕዝብ ላይ በፈጸሟቸው ክህዴቶች  ሥማቸውን ያጠፉና ኅሊናቸውን ያጎደፉ እንኩቶ ፖለቲከኞች ዐይናቸውን በጨው አጥበው ከህውሓት ጋር አብረው ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ሲገልጹ እየሰማን ነው፡፡

በየትኛውም መልኩ ቢሆን የአገራችን ዋነኛ ችግር ከሆነው ሃይል ጋር የሽብር ድርጅት እንጂ የሽግግር መንግሥት መመሥረት የማይቻል ቢሆንም በእርጅና እና በሥንፍና ተሸብበው ‘አሜሪካ’ በተባለች ‹‹አገር አፍራሽ አገር›› ውስጥ በድብርትና በስልችት መንፈስ የሚሰቃዩ አንዳንድ ፖለቲከኞች ግን፤ በኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል ቀብሩ የተማሰውን አሸባሪ ሕያው እንደሆነ አምነው ‹‹በመንግሥትህ አትርሳን›› እያሉት ነው፡፡

በመሆኑም ለእነዚህ የእንጨት ሽበቶች እንዲህ የሚል መልዕክት ማስተላለፍ እንሻለን፡፡

‹‹ትዳር መመሥረትና የመሠረተውን ትዳር መምራት የተሳነው ግለሰብ የሽግግር መንግሥት መሥርቶ አገር መምራት አይቻለውም፡፡ ያፈራውን ቤተሰብ በትኖ የሚቅበዘበዝ ፖለቲከኛ የካደውን ሕዝብ ወክሎ የሚወዘፍበት ወንበር ይቅርና ተራ ዜጋ ሆኖ የሚኖርበት አገር የለውም፡፡ ህውሓትም ቢሆን ባሁኑ ሰዓት የሚያስፈልገው ቀብሩን የሚያሰናዳለት ጠንካራ እድርና ለቀስተኛ እንጂ ከሬሳ ሳጥን ወደ ዙፋን የሚያሸጋግረው አጋር ፖለቲከኛ አይደለም፡፡

በመሆኑም ከዚህ በኋላ ከህውሓት ጋር መሞትና ወደ መቃብር ቤት መውረድ ካልሆነ በቀር ወደ ቤተ-መንግሥት መግባት አይታሰብም፡፡ ቀደም ባለው ጊዜ በቁማቸው ሞተው እንደ ቫምፓየር የሕዝብ ደም በመምጠጥ የሚኖሩ ሕይወት አልባ ፖለቲከኞች ደግሞ የሽብር ቡድኑን ተከትለው ወደ ሥልጣን መምጣት ይቅርና አብረውት ለመሞትም መስፈርቱን አያሟሉም፡፡ 

እናም በቀብሩ አፋፍ ላይ የሚገኘውን አሸባሪ ከሞት ለመታደግ ከመሞከራቸው በፊት ‹‹እኔ ማን ነኝ›› ብለው በተናጠል እራሳቸውን ቢጠይቁ ሕዝባዊ ተቀባይነት ቀርቶ ሕይወት አልባ ሙታኖች መሆናቸውን ይረዱ ነበር፡፡

 

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top