Connect with us

የአንድ ግለሰብ ቃላት ያስነሳው አቧራ

የአንድ ግለሰብ ቃላት ያስነሳው አቧራ
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

የአንድ ግለሰብ ቃላት ያስነሳው አቧራ

የአንድ ግለሰብ ቃላት ያስነሳው አቧራ

(አሳዬ ደርቤ- ለድሬ ቲዩብ)

በእለተ እሁድ መስቀል አደባባይን የሞሉ እልፍ አእላፍ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የምዕራባውያንን ፍርደ ገምድልነት፣ የውጭ ሚዲያዎችን ዐይን ያወጣ ቅጥፈት አውግዘዋል፡፡ በአገራቸው ጉዳይ ላይ የሚመጣን ውጫዊም ሆነ ውስጣዊ ጠላት ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ ኢትዮጵያን በዘር ፖለቲካ ሲያባላ የኖረውን የሽብር ቡድን ወደ ዙፋን ለመመለስ ከመሞከር ይልቅ የወረደን ጽንስ ወደ ማሕጸን መመለስ እንደሚቀል ተናግረዋል፡፡

‹‹ከዚህ በኋላ በምርጫ ካርድ እንጂ በባሩድ ተዋግቶም ሆነ በባዕድ መንግሥታት ተደራጅቶ ሥልጣን መያዝ አይቻልም›› የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ‹‹ህውሓት ከተባለ አገር አፍራሽ አሸባሪ ጋር ተሰልፎ የሚመጣን የትኛውንም አካል ከመከላከያ ሠራዊታችን ጎን ተሰልፈን እስከ መጨረሻው ድረስ እንታገለዋለን›› የሚል ድምጽ ተስተጋብቷል፡፡

አውቆም ሆነ ሳያውቅ በህውሓት የሳይበር ጦር ሲጠለፍ የሚታየውና የእራሱን ግብ ጥሎ የጁንታውን አጀንዳ መሸከም የማይታክተው የሶሻል ሚዲያ ተጠቃሚ ግን መስቀል አደባባይ የተገኘው ሕዝብ ካስተላለፈው መልዕክት ይልቅ ከአንድ አርቲስት አንደበት የፈለቁትን ቃላት ርዕሱ አድርጎ ሲያወግዝና ሲፋተግ መታየቱ ያስገርማል፡፡(እርግጥ ነው፤ አርቲስቱ ዘግይቶ ይቅርታ ጠይቋል)

እርግጥ ከዚህ በፊት አርቲስቱን ሲያናንቁ የነበሩ ጸረ አገር ሃይሎች መስቀል አደባባይ ላይ ባደረገው ንግግር ተደስተው ሙዚቀኛውን ሲያደንቁ መታየታቸው የሚጠበቅ ነገር ነው፡፡ ዋነኛ ዓላማቸው የሕዝብን መፎክር በግለሰብ ንግግር መጋረድ ብሎም ሶሻል ሚዲያውን በመጥለፍ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መስቀል አደባባይ ላይ ተገኝተው ያስተጋቡት አገራዊ ድምጽ እንዳይተላለፍ ማድረግ በመሆኑ የታሪኩን ንግግር አጀንዳቸው ቢያደርጉ አይደንቅም፡፡

ይሄንን ዓላማቸውን ማክሸፍ የሚቻለው ታዲያ አንድ አርቲስት በየዋህነት በተናገረው ንግግር ፈንታ የአንድ ከተማ ሕዝብ ያስተላለፈውን መልዕክት በማስተላለፍ ቢሆንም ሶሻል ሚዲያው ግን የሰልፉን ዓላማ ጥሎ የጁንታው ደጋፊዎች የሰጡትን አጀንዳ አንጠልጥሎ ሲባክን ነበር፡፡

ፌስቡክ የሚጠቀመው ኢትዮጵያዊ ሃይል በሰልፉ ላይ የተወገዙትን ሚዲያዎች፣ የምዕራቡን ዓለም መሪዎች፣ የሽብር ድርጅቶች… ወደ ሶሻል ሚዲያው አምጥቶ ማስተጋባት ሲገባው የአንድ አርቲስትን ስብከት እንደ መንግሥት አቋም ወስዶ ሲያወግዝ መታየቱ የአሸባሪውን አጀንዳ ተሸካሚ ከመሆን አለመውጣታችንን የሚያሳይ ነው፡፡

በተረፈ አርቲስቱ ድሽታ ጊና የሚል ሙዚቃ ለቅቆ ወደ ዝና ማማ ከመውጣቱ በፊት በግብርና ሙያ ላይ ተሰማርቶ ሲኖር የነበረ እንደመሆኑ መጠን በእነ ተቀዳሚ ሙፍቱ ሐጂ ኡመር ኢድሪስና በእነ ሃይሌ ገብረ ሥላሴ የሚመራ የሽምግልና ቡድን መንግሥትን እና ህውሓትን ለማሸማገል አስቦ ወደ መቀሌ ከሄደ በኋላ ክብሩን በማይመጥን መልኩ ተስተናግዶ መመለሱን ላይሰማ ይችላል፡፡  ከዚህ ባለፈም አርቲስቱ ቀደም ባለው ጊዜ ከጦር ሠራዊቱ ባይወጣ ኖሮ የሰላም አማራጮችን ዘግቶ ነፍጥ ባነሳው አሸባሪ ከሰሜን እዝ ሠራዊት ጋር አብሮ ሊወጋ እንደሚችል ዘንግቶት ሊሆን ይችላል፡፡

ስለሆነም አንድ ሙዚቀኛ በተሳሳተ ጊዜ እና ስፍራ ያስተላለፈውን ቅን ስብከት እንደ ትልቅ ፖለቲከኛ አቋም ወስዶ አርቲስቱ ላይ የትችት ናዳ ሲወረውሩ መዋል የሕዝብን መልዕክት ትቶ የአሸባሪውን ፍላጎት ከማሟላት የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ ትችቱም ቢሆን መሰንዘር ያለበት ለሰልፉ አዘጋጆች እንጂ ለአርቲስቲ መሆን አልነበረበትም፡፡

በተረፈ ‹‹አገር አፈርሳለሁ›› በሚል ግልጽ ፉከራ ድሽቃ ጭኖ ሸዋ ድረስ የመጣን ዘረኛ የሽብር ቡድን በሰላም ሰባኪ ቃላትም ሆነ አዳም ወንድሜ በሚል ሰውኛ ሙዚቃ መመለስ እንደማይቻል የተረዳው የአዲስ አበባ ሕዝብ ግን ልክ እንደ መላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ መስቀል አደባባይ ላይ ተገኝቶ እንዲህ የሚል አቋሙን አንጸባርቋል፡፡

በአገሬ የብስ ላይ ሰላም እንዲነፍስ

እንደ እቃቃ ጎጆ አገር እንዳትፈርስ

ሽብር የተጫነው የፈርዖን ፈረስ

ተከዜ ወንዝ ላይ- ተውጦ ይደምሰስ፡፡

 

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top