Connect with us

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ፦

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወቅታዊ ሁኔታ ዙርያ የተሰጠ መግለጫ፦
የአዲስ አበባ አበባ ከተማ አስተዳደር

ዜና

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ፦

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወቅታዊ ሁኔታ ዙርያ የተሰጠ መግለጫ፦

የህወሃት ከሃዲ ጁንታ ስልጣኔን አሳጥተውኛል ብሎ በሚያስባቸው ወገኖችና መላ ኢትዮጵያውያን ላይ ጠንካራ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ይፋዊ ጦርነት ከከፈተብን  አንድ አመት ሞላው። ከሃዲው የትህነግ ጁንታ የዛሬ ዓመት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ከ20 ዓመታት በላይ በቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ሆኖ ሲጠብቀው በኖረው የሰሜን እዝ የመከላከያ ሃይላችን ላይ ታሪክ የማይረሳው ክህደት ከፈጸመ በኋላ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ ሁሉንም አይነት ጥቃት ሲፈጽም ቆይቷል።

የትህነግ አሸባሪ ቡድን በአሁኑ ወቅት  ያለሃፍረት ኢትዮጵያ ሳትፈርስ ነጻ ሃገረ ትግራይን መመስረት አይቻልም የሚል ግልጽ አላማ አንግቦ እየተፋለመን ከመሆኑም በላይ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚያግዙትን የውስጥና የውጪ አሸባሪዎችና ታሪካዊ ጠላቶቻችንን አስተባብሮ በሁሉም አቅጣጫ ውጊያ ከፍቶብናል።

አሸባሪው ሃይል በክልሉና ከክልሉ ውጪ የሚኖረውን የትግራይ ህዝብ በዘረኝነትና በሃሰት ፕሮፓጋንዳ በማስከርም በወረራ በተቆጣጠራቸው የአማራና የአፋር አካባቢዎች አስከፊ ግድያና ዝርፊያ እየፈጸመ ነው።

በዚህ ምክንያት በኛ ዘመን እጅግ የምንወዳትና  እንደ አይናችን ብሌን የምንሳሳላት ሃገራችን የተባበረ ጥቃት ሰለባ ሆናለች። እናም ኢትዮጵያውያን  አንድ ሆነን በመቆም ሃገራችንን መታደግ የግድ ከሚለን  የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ነን። እንደ ሃገርም ቁርጠኛና የተናበበ አመራር ከምንሰጥበትና የተደራጀ የህዝብ ንቅናቄ ከምናረጋግጥበት የትግል ምዕራፍ ውስጥ እንገኛለን።

ኢትዮጵያ በዘመናት መካከል የገጠሙኣትን የህልውና አደጋዎች በሙሉ የቀለበሰችው በህዝቦቹኣ ጠንካራ አንድነትና የተባበረ ክንድ ነው። በዚህ ዘመን ኢትዮጵያን ካልዘረፍኳትና እንደወትሮው ረግጬ ካልገዛኋት  ትፍረስ በሚል ስግብግብ ፍላጎት ክህደት የፈጸመብንና ጦርነት የከፈተብንን የህወሃትን ወራሪ ጁንታ የምንሰብረውና የምንቀብረውም ከታሪካችን በወረስነው በዚሁ የጀግንነትና የአንድነት መንፈስ ብቻ ነው።

በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሸባሪው የህወሃት ጁንታ የከፈተብን ሁለገብ ጥቃት የደረሰበትን ደረጃ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሁለንተናዊ አቅሙን ሃገራችን የተጋረጠባትን አደጋ ለመቀልበስ በሚያስችሉ እርምጃዎች ላይ ለማዋል ወስኗል።

የአዲስ አበባ አበባ ከተማ አስተዳደር የህወሃት ዘራፊ ጁንታ በኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ ቀጥተኛ ወረራ ከፈጸመበት ጊዜ ጀምሮ አመራሩን፣ ባለሃብቱንና መላ የከተማውን ነዋሪዎች በማስተባበር ለመከላከያ ሃይላችንና በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ የሚውል 4 ቢሊዮን ብር ያህል ሃብት በማሰባሰብ ለፌደራልና ለክልል መንግስታት አስረክቧል።

የከተማ አስተዳደራችን ዛሬም በየግንባሩ በጽናትና በጀግንነት የሚፋለሙት የመከላከያ ሰራዊታችንና መላ የጸጥታ ሃይሎቻችን ጠንካራ ደጀን ከመሆን ባሻገር አመራሩንና ህዝቡን በማስተባበር በግንባር በመሰለፍ ሁሉንም አይነት መስዋዕትነት አብሮአቸው ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል። የከተማ አስተዳደሩ በኢትዮጵያ ላይ የተደቀነውን የህልውና አደጋ በአጭር ጊዜ ለመቀልበስ ከህዝቡና ከሁሉም የኢትዮጵያ ወዳጆች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በቁጭትና በጥድፊያ መንፈስ እንደሚሰራም በዚሁ አጋጣሚ ይገልጻል።

በኢትዮጵያ ባለፉት ሶስትና ዓራት ዓመታት የታየውን ሁለንተናዊ  ለውጥ የፈጠሩት በባዶ እጃቸው አደባባይ ወጥተው የህወሓትን የአፈና ታንኮች የገጠሙ ፍትህና ዕኩልነት የጠማቸው ወጣቶችና ጭቆና የበረታባቸው ዜጎች ናቸው። የህወሓት አሸባሪ ሃይል ዛሬ በየአንዳንዳችን ደጀፍ ለመድረስ እየማሰነ ያለው ይህንኑ ነባራዊ ዕውነት ለመመለስ ነው።

በመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች በመቶ ሺዎች ተደራጅተው የአካባቢያቸውን ሰላምና ጸጥታ ከመጠበቅ በተጨማሪ በገፍ የመከላከያ ሃይላችንን በመቀላቀል  የህልውና አደጋውን ለመቀልበስ ከመቼውም በላቀ ቁርጠኝነት ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋማትና የውጊያ ግንባሮች እንዲተሙም አስተዳደራችን ጥሪውን ያስተላልፋል።የከተማው ነዋሪዎችም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በመኖሪያ አካባቢዎች ደረጃ በመደራጀትና ከሁሉም የጸጥታና የአስተዳደሩ አካላት ጋር በመናበብ ሰላምና ጸጥታቸውን በንቃትና በብቃት እንዲጠብቁ ይጠይቃል።

የከተማው የመኖሪያ ቤት አከራዮች፣ ሆቴሎችና ሁሉም አገልግሎት ሰጪ ተቃማት አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ  ሰርጎ ገቦችን ለመቀጣጠር የሚፈጸሙ መደበኛና ድንገተኛ ፍተሻዎችን ከመደገፍ በተጨማሪ ተገልጋዮቻቸውን በቅርበት  እንዲከታተሉም የከተማ አስተዳደሩ ያሳስባል።

የከተማ አስተዳደሩ በዚህ አጋጣሚ በህወሓት አስተባባሪነት በግንባር የሚፈጸመውን የሽብር ድርጊት በከተማችን ውስጥ  በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚደግፉ ማናቸውም አይነት እንቅስቃሴዎች ላይ ቋሚ ፣ ህጋዊና ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድ ያሳውቃል።

በመጨረሻም የከተማችን ነዋሪዎችና መላው ኢትዮጵያውያን በዚህ ወሳኝ ወቅት አንድ ሆነው በመቆምና ሁለገብ አቅማችሁን በማስተባበር የሽብር ቡድኑን ህልፈት ለማፋጠን የሚያስችል ፈጣንና ወሳኝ እርምጃ እንድትወስዱ የከተማ አስተዳደራችሁ ጥሪውን ያስተላልፍላችኋል።

ጥቅምት 22/2014 ዓ.ም

አዲስ አበባ

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top