Connect with us

ይድረስ ለጋዜጠኞች እና ‘የማህበረሰብ አንቂዎች’፤ ሳንመከር አንምከር

ይድረስ ለጋዜጠኞች እና 'የማህበረሰብ አንቂዎች'፤ ሳንመከር አንምከር
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

ይድረስ ለጋዜጠኞች እና ‘የማህበረሰብ አንቂዎች’፤ ሳንመከር አንምከር

ይድረስ ለጋዜጠኞች እና ‘የማህበረሰብ አንቂዎች’፤ ሳንመከር አንምከር

(ያሬድ ኃ/ማርያም – የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

ይህ ጦርነት ኢትዮጵያን ብዙ ዋጋ እያስከፈላት ነው። ሕዝባችን ጭንቅ ውስጥ ነው። ከዛሬ ነገ ምን ሊፈጠር ይችላል፣ የጦርነቱ ሰደድ የቱጋ ይበርዳል፣  አገሬ ምን ትሆናለች፣ ልጆቼ፣ ነብረቴ ምን ይሆናሉ እያለ በስጋት እንቅልፍ አጥቶ ያድራል። ጦርነቱ የሚካሄድባቸው አካባቢዎች ያሉ ወገኖች ደግሞ ለመግለጽ በሚያዳግት ሁኔታ ውስጥ ናቸው። 

በእንዲህ ያለ ክፉ ወቅት እውነተኛ መረጃን በማቅረብ ሕዝብን ከማረጋጋት እና በአገር ላይ ያንጃበበው አደጋ የሚቀለበስበትን ቀና መንገድ ከማመላከት አልፋችሁ በሀሰት መረጃ እና በፕሮፓጋንዳ ሕዝቡን የምታሸብሩ፣ ለሰበር ዜና ሽሚያ ያላጣራችሁትን ነገር ሁሉ ዜና የምታደርጉ፣ ለመንግስት ይሁን በተቃርኖ ለቆሙት የወያኔ ታጣቂዎች አጉል ምክር እና ቅስቀሳ የምታደርጉ ጋዜጠኞች እና ‘የማህበረሰብ አንቂዎች’ እባካችሁ ከዚህ አስነዋሪ ተግባራችሁ ታቀቡ።

ለወዳጄ የኢሳት ጋዜጠኛው መሳይ መኮንን #MessyMekonnen ከዚህ በታች ያለውን እጅግ አስነዋሪ፣ የተወገዘ፣ ጭካኔ የተሞላው፣ በዘረኝነት የሚያስፈርጅ ከዚህ በታች ያለውን ምክረ ሀሳብ ለመንግስት መስጠትህ እጅግ አስደንግጦኛል። ጋዜጠኛ መሳይ ለመንግስት ያቀረበው ጥሪ ቃል በቃል እንዲህ ይላል፤

“… ጥብቅ መልዕክት ለመንግስት፣፣ አሁንም አልረፈደም። የትግራይ ተወላጆችን፣ ከህወሀት ጋር ግንኙነት የሌላቸውንም ቢሆን በጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያዎች እንዲሰባሰቡ ማድረግ ያስፈልጋል። አሜሪካን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት፣ ወደ ጦርነቱ ከመግባቷ በፊት በሀገሯ የሚኖሩ የጃፓን ዜጎችን በሙሉ ወደካምፕ አስገብታ ነው የጃፓን ወራሪንና የሂትለርን ጦር ማሸነፍ የቻለችው። ጃፓኖችን በብብቷ ስር ወሽቃ ወደ ጦርነቱ መግባት የሽንፈት መጀመሪያ መሆኑን በመረዳቷ እርምጃውን ወስዳለች። 

ኢትዮጵያም ከዚያ የከፋ አደጋ ውስጥ ናት። የደሴው ግብግብ ዋናው ተዋናይ ከህዝቡ ጋር አብረው የሚኖሩት የህወሀት ደጋፊዎች መሆናቸው በስፋት ታምኗል። እነሱን በጉያ ይዞ ጦርነቱን ማሸነፍ በፍጹም የሚቻል አይደለም። ለእነሱም ደህንነት ተብሎ እርምጃው በአስቸኳይ ሊወሰድ ይገባል።”

መሳይ እንደ ጥሩ ምክር የለገሰው የጃፖን ተወላጆችን ወደ ማግለያ ካንፕ ያስገባው የአሜሪካ የነውር እርምጃ የተወሰደው በ2ኛው የአለም ጦርነት ወቅት ዘረኛ የነበረው የአሜሪካ ፕሬዚደንት Franklin D. Roosevelt በመቶ ሺዎች የሚሆኑ የጃፖን ዝርያ ያላቸውን አሜሪካዊያንን ሳይቀር ስጋት ናቸው ብሎ የማጎሪያ ከካምፕ ውስጥ የጨመረበትና በአሜሪካ ታሪክ ጥቁር ጥላ ትቶ ያለፈ አስነዋሪ እና ዘረኛ ፋሽስታዊ ክስተት ነው። ጋዜጠኛ መሳይ ይህን ታሪክ ሙሉውን በቅጡ የተረዳው አልመሰለኝም። የታሪኩን ጫፍ ይዞ ለምክር የቸኮለ መሰለኝ።

ይህ ክስተት ከተፈጸመ አስርት አመታት በኋላ በፕሬዚዳንት ጂሚ ካርተር ዘመን በዚህ አስነዋሪ ድርጊት ዙሪያ የቀረቡ ክሶችን መነሻ በማድረግ Commission on Wartime and Internment of Civilians (CWRIC) የሚባል አጣሪ ኮሚሽን ተቋቁሞ ሰፊ ምርመራ ከተካሄደ በኋላ በ1983 እ.አ.አ የፕሬዝዳንት ሮዝቬሌት እርምጃ የዘር ፍረጃ ላይ የተመሰረት፣ አለም አቀፍ ሕጎችን የጣሰ፣ በጦርነት ከወታደራዊ ዲሲፕሊን የራቀ የነውርና የተጋነነ እርምጃ -war hysteria፣ የሮስቬልት ደካማ የፖለታካ አመራር በሚል ተፈርጆ ተወግዟል። 

በዚህም ምክንያት የአጣሪ ኮሚሽኑን ሪፖርት መነሻ በማድረግ ፕሬዚደንት ሮናልድ ሬገን Civil Liberties Act of 1988 የሚል ሕግ በማውጣት በአሜሪካ መንግስት ስም በጃፓኖች ላይ ለተፈጸመው የግፍና የነውር እርምጃ ይቅርታ ጠይቀዋል። ከዛም አልፈው በካንፕ ታጉረው ለቆዮት ትውልደ ጃፖናዊያን በነፍስ ወከፍ 20,000 ዶላር ካሳ እንዲከፈል አድርገዋል። በጠቅላላው ለ82ሺ በላይ ጃፖናዊያን አሜሪካ 1.6 ቢሊዮን ካሳ ከፍላለች።

ወዳጄ ጋዜጠኛ መሳይ እንዲህ ያለውን አስነዋሪ እና ዘረኛ እርምጃን ኢትዮጵያ እንድትደግመው መምከርህ አንድም ካለማወቅ፤ አለያም ስሜታዊነትህ የጋዜጠኝነት ሙያህን ቀብሮት ይሆናልና ብታርመው ጥሩ ነው። እንዲህ ያለው ስህተት ከዚህ ቀደምም ከጦርነቱ መጀመር በፊት ጋዜጠኛ ሲሳይ አጋና በዚሁ በኢሳት ላይ ትግራይን በኤርትራ ማስመታት ነው የሚል ምክር ሲለግስ ሰምቼ ሰቅጥጦኝ ነበር። ጦርነቱ ተጀምሮ የሆነውን ሳይ የዛሬውን የመሳይ አስደንጋጭና ዘረኛ ምክር ችላ ብዮ ማለፍ አልቻልኩም።

ሳንመከር አንምከር!

ፎቶ፡- ያሬድ ኃ/ማርያም

 

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top