Connect with us

እጅጋየሁ ሺባባው ( ጂጂ )  ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ….

እጅጋየሁ ሺባባው ( ጂጂ ) ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ....
ጥበቡ በለጠ

ነፃ ሃሳብ

እጅጋየሁ ሺባባው ( ጂጂ )  ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ….

እጅጋየሁ ሺባባው ( ጂጂ ) ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ….

(ጥበቡ በለጠ)

ከመንዙማ፣ ከአሚናዎች፣ ከጉባኤ ቃና የተፈለቀቁ ሙዚቃዎች

(በጣም የምወዳት ባለቅኔ ድምጻዊት/

ሸማ ነጠላውን ለብሰው

አይበርዳቸው አይሞቃቸው

ሐገሩ ወይናደጋ ነው

አቤት ደም ግባት – ቁንጅና

አፈጣጠር ውብ እናት

ሐገሬ እምዬ ኢትዮጵያ

ቀጭን ፈታይ እመቤት

እጅጋየሁ ሽባባው ጂጂ በአለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ትልቅ ደረጃ ካደረሱት ድምፃዊያንና ድማጻዊያት መካከል ከፊት ተሰላፊ ናት፡፡ ለምሳሌ በአለም ግዙፍ ቴሌቪዥን ጣቢያ የሚባለው CNN በተደጋጋሚ ጂጂን እና የሙዚቃ ስራዎቿን አቅርቧል፡፡ ሌሎች የሚዲያ ተቋማትም በአዘፋፈን ስልቷ፤ በድምጿ፤ በሙዚቃ ቅንብሯ እና በተለያዩ

ጉዳዮች ሰፊ ሽፋን እየሰጧት ከመጡ ቆይተዋል፡፡ ይህች ስመ ገናና ድምፃዊት ከ14 ዓመታት የውጭ ሀገር ቆይታ በኋላ ወደ ሐገሯ መጥታ በህዝቧ ፊት የሙዚቃ ስራዎቿን አቅርባለች፡፡እጅጋየሁ ሽባባው ባለፉት 20 ዓመታት እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥም የሙዚቃ፤ የሥነ ግጥም እና የሥነ ፅሁፍ ሃያሲያን ስራዎቿን በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲተነትኗቸው ቆይተዋል፡፡

በአንድ ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋዎች ጥናት ጉባኤ ላይ በቀረበው ጥናት ጂጂ ከኢትዮጵያ ድምፃዊያን የሚለያት ሙዚቃዎቿ እጅግ የጠለቀ ኢትዮጵያዊነት መንፈስን

ስሜትን በውስጣቸው አምቀው የያዙ በመሆናቸው እንደሆነ የተገለፀበትም አጋጣሚ አለ፡፡

እጅጋየሁ ሽባባው ሐገርን በየሙዚቃዎቿ ውስጥ የምትገልፅባቸው መንገዶችም እየተነሱ ተተንትነዋል፡፡ ለጂጂ ሀገር ማለት ቤተሰብ፣ ኑሮ፣ ትዝታ፣ መልክዐ ምድሩ፣ ወንዞች፣

ተራሮች፣ ርቃ የሄደችው ህዝቧ… ቢሆኑም የአቀራረብ መንገዶቿ ግን ጆሮ ግቡና እጅግ ማራኪ መሆኑም ተወስቷል፡፡ ለምሳሌ በአንድ ወቅት ደግሞ አባይ ወንዝ ላይ የተፃፉ ልዩ

ልዩ ኪነ-ጥበባዊ ስራዎች ተሰብስበው ሚዛን ላይ ቁጭ ብለው ነበር፡፡ ሚዛን ያልኩት ሂሳዊ ምዘናውን ለመግለፅ ፈልጌ ነው፡፡

እጅግ በርካታ ገጣሚያን እና ሙዚቀኞች አባይን በየራሳቸው እይታ ሲገልፁት፤ ሲያቆለጳጵሱት፤ ሲሞግቱት፤ ሲወቅሱት፤ ሲቆጩበት… እንደነበር በጥናት ተዳሷል፡፡ በመጨረሻም በግጥም፤ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኃህን፤ በሙዚቃ እጅጋየሁን

ጂጂን የሚያክል የጥበብ ሥራ ግን አልተገኘም ተብሏል፡፡ ፀጋዬ የስነ ግጥም ጣሪያ ሲሆን፤ ጂጂ ደግሞ የሙዚቃው ቁንጮ እንደሆነች ስራዎቻቸው እየተተነተኑ ቀርበዋል፡፡

ከፀጋዬ የሚከተለው ቀርቦ ነበር፡-

ዓባይ የጥቁር ዘር ብስራት፣

የኢትዮጵያ የደም ኩሽ እናት፤

የዓለም ስልጣኔ ምስማክ፣

ከጣና በር እስከ ካርናክ፤

ዓባይ የአቴንስ የጡቶች ግት፣

የዓለም የስልጣኔ እምብርት፤

ጥቁር ዓባይ የጥቁር ዘር ምንጭ፣

የካም ስልጣኔ ምንጭ፤

ዓባይ-ዓባይ ዓባይ-ጊዮን፣

ከምንጯ የጥበብ ሳሎን፣

ግሪክ ፋርስ እና ባቢሎን፣

ጭረው በቀዱት ሰሞን፡፡

ዓባይ የአማልእክት አንቀልባ፣

የቤተ-ጥበባት አምባ፤

ከእሳት ወይ አበባ

ይህ የሎሬት ፀጋዬ ግጥም በኢትዮጵያ ሥነ ግጥም ውስጥ ደረጃው አንደኛ ነው ተብሏል፡፡ ፀጋዬ ራሱ በባለቅኔነቱ ግዙፍ ስብዕና ቢሰጠውም ይህ አባይ የሚለው ግጥሙ ደግሞ

በተለያዩ የሥነ ግጥም መለኪያዎች ሲመረመር ልዕለ ጥበብ (Masterpiece) ነው በሚል ተፈርጇል፡፡ የእጅጋየሁ ሽባባው ጂጂ ዓባይም እንዲሁ ከሙዚቃው ዓለም ከፀጋዬ ገ/መድህን ዓባይ ጋር ተፈርጇል፡፡

የማያረጅ ውበት የማያልቅ ቁንጅና

የማይደርቅ የማይነጥፍ ለዘመን የፀና፡፡

ከጥንት ከፅንስ አዳም ገና ከፍጥረት

የፈሰሰ ውሃ ፈልቆ ከገነት፡፡

ግርማ ሞገስ

የአገር ፀጋ የአገር ልብስ

ግርማ ሞገስ፡፡

ዓባይ…

የበሐረው ሲሳይ

እያለች ከህሊና በማይጠፋ የሙዚቃ ስልት እያንቆረቆረች የምታወርድ ድምፃዊት እንደሆነች ተነግሮላታል፡፡ እነዚሁ ሁለት የኪነ-ጥበብ ሰዎች ዓባይ ላይ ባቀረቧቸው ስራዎቻቸው የዓባይን መልክ፤ ቁመና፤ ታሪክ እና ማንነት ገልፀዋል፡፡ እንዲሁም ጥበባዊ ሥራዎቻቸውም በሚዛን ሲቀመጡ ትልቅ ቦታ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ዓባይ በመፅሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሰፊው ከመገለፁም በላይ በተለይ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተያይዞ መጥቶ ጣና ሐይቅ ውስጥ ገብቶ

ግዙፍነቱ ይጨምራል፡፡ ጣና ላይ ደግሞ 37 ያህል ደሴቶች አሉ፡፡ በነዚህ ደሴቶች ከ21 የሚበልጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ገዳማት አሉ፡፡ እጅግ አስገራሚ የኢትዮጵያ ቅርሶችም በነዚህ ገዳማት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ስለዚህ ዓባይ ላይ ይፀለያል፤ ይቀደሳል፤ ይዘመራል፤ በብህትውና ይኖራል፤ ይታመንበታል፡፡ ዓባይ አባይ የኢትዮጵዊያን መንፈስ ነው፡፡ እምነት ነው፡፡ ሀብት ነው፡፡ ይሄን የጀርባ አንደምታ ይዘው ነው እነ ጂጂ ዓባይ ላይ ፍፁም

ተወዳጅ የሆኑ ስራዎችን ያቀረቡት፡፡ በጂጂ ሙዚቃዎች ላይ በተደረገው ውይይት ድምፃዊቷን

ከፀጋዬ ገ/መድህን ጋር እያነፃፀሩ ማቅረብ ተዘውትሮ ነበር፡፡ ጂጂ የፀጋዬ ተፅእኖ ያደረባት ድምፃዊት ናት ተብላለች፡፡ ለምሳሌ ፀጋዬ ዓድዋ ላይ የፃፈው ሥነ-ግጥሙ ሌላው

ተጠቃሽ ስራው ነው፡፡ እጅጋየሁ ሽባባውም ዓድዋ ላይ የዘፈነችው ዘፈን እንደ ፀጋዬ ዓይነት እጅግ ጥልቅ ስሜትን የሚያስተጋባ ሥራ እንደሆነ ተመስክሮላቸዋል፡፡ ፀጋዬ

በኢትዮጵያ ፍቅር ላይ የወደቀ ገጣሚ ነው በሚል ኢትዮጵያዊነት የተላበሱ ሥነ-ግጥሞቹ ተዘርዝረዋል፡፡ እጅጋየሁ ሽባባውም እንዲሁ ኢትዮጵያዊነት” በሰፊው

የምታስተጋባ ድምፃዊት እንደሆነች ባለፉት ጊዜት በልዩ ልዩ መድረኮችና ጥናቶች ቀርቧል፡፡ በቅርቡም እጅጋየሁ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረገችው ቃለ-ምልልስ የሥነ-ግጥም

አድናቂ መሆኗን እና እነ ፀጋዬ ገ/መድህንን በስራዎቻቸው እጅግ እንደምትወዳቸው ነግራኛለች፡፡

ከዚህ ሌላም የጂጂ ዘፈኖች ከኢትዮጵያ ባህልና ትውፊት ውስጥ የወጡ እንደሆኑም በሰፊው ተወስቷል፡፡ በተለይ በወለዬዎች መንዙማ እና በአሚናዎች የድምፅ ቅላፄ ላይ ተመስርታ ወደ ዘመናዊ ሙዚቃ አምጥታቸዋለች ይባላል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ጂጂ ራሷም ትስማማለች፡፡ ገና ከህፃንነቷ ጀምሮ የአሚናዎች የአገጣጠም እና የዜማ ስልት እጅግ እጅግ እንደሚገርማትና እንደምትወደው አውስታለች፡፡ እንደውም በአንድ ወቅት እነ ጂጂ ቤት ለመጣች አሚና ልብሶቿን አውጥታ እንደሰጠቻት የልጅነት ታሪኳን ታወሳለች ጂጂ፡፡ 

በነዚህ የፍቅር ተፅእኖዎች በሚመስል መልኩ ከመንዙማ እና ከአሚናዎች የሙዚቃ ስልት ተፈልቅቀው የወጡት ስራዎቿ ለህዝብ ጆሮ ቅርብ እንድትሆን አድርጓታል፡፡ በዚህ ስልት

ከተጫወተቻቸው ዘፈኖች መካከል ደግሞ “ናፈቀኝ የኛ ቤት ጨዋታ” እያለች የምትዘፍነው ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ሙዚቃም በአንድ ወቅት ሰፊ ጥናት

ቀርቦበታል፡፡ አቅራቢው ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ፅሁፍ መምህር የሆኑት አቶ ወንደሰን አዳነ ናቸው፡፡ ለዚህሙዚቃ ውበት እና የሥነ-ግጥም ብቃቱ እጅግ የተዋጣለት

መሆኑን አቶ ወንደሰን ተናግረዋል፡፡ በ1980ዎቹ መጨረሻ ላይ እጅጋየሁ ሽባባው የመጀመሪያዋን አልበም ለቀቀችው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ፅሁፍና የፎክሎር መምህር የሆኑት ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ በአጋጣሚ የጂጂን ካሴት ማታ ሰምተውት ነበር፡፡ ጠዋት ሊያስተምሩ ወደ ተማሪዎቻቸው ዘንድ መጡ፡፡ እንዲህም አሉ፡- “ዛሬ እንቅልፍ ሳይወስደኝ ነው ያደርኩት” አሉ፡፡ ተማሪዎቻቸውም “ምነው? ምን ሆንክ?” አሏቸው፡፡ እርሳቸውም “ፍቅር እየራበኝ” እያለች የምትዘፍን ልጅ እጅግ እየደነቀችኝ ደጋግሜ ስሰማት ነው ያደርኩት” አሉ፡፡ ልጅቷን ግን ያወቃት የለም፡፡ እሳቸውም ስሟ እጅጋየሁ ነው፤ የሚያውቃት አለ ከናንተ ውስጥ? አሉ፡፡

የሚያውቃት ጠፋ፡፡ እርሳቸውም ሲናገሩ በኢትዮጵያ ውስጥ ከ26 ዓመት በኋላ በሙዚቃ ስልቷ ነፍሴን የገዛችው ይህች ድምፃዊት ናት፡፡ በእኔ ግምት የኢትዮጵያን ሙዚቃ ትልቅ ደረጃ

ታደርሰዋለች ብዬ የምተማመነው በዚህች ልጅ ነው፡፡ ጉድ ነው ዘፈኗ.. እያሉ በስሜት ሲናገሩ ሰምቻቸው ነበር፡፡ በጣም የሚገርመው ዶ/ር ፈቃደ፤ ተስፋ የጣሉባት ጂጂ ሙሉ በሙሉ እንደተገመተችው የኢትዮጵያን ሙዚቃ በተለየ መንገድ ጥሩ ደረጃ ላይ እንዳደረሰችው በልዩ ልዩ መድርኮች ተመስክሯል፡፡

ባለፉት 26 አመታት ውስጥ በሐገራችን ኢትዮጵያ ከተሰሩ ሙዚቃዎች በሙሉ ለኔ የምርጦች ምርጥ የምላት፤ የመንፈሴ ምግብ የጂጂ ዘፈን ይህች ናት፡-

እህህ እሰከ መቼ እህህ: እህህ እስከመቼ

እህህ እሰከመቼ እህህ: ያዘላልቀናል

እህህ እሰከመቼ እህህ: ገና ብዙ መንገድ

እህህ እሰከመቼ እህህ: ብዙ ይቀረናል

እህህ እሰከመቼ እህህ: እስኪ ፍጠን ፍጠን

እህህ እሰከመቼ እህህ: እግር ተራመድ

እህህ እሰከመቼ እህህ: ምን ያኳትንአል

እህህ እሰከመቼ እህህ: አመድ ለአመድ

እህህ እሰከመቼ እህህ: አይ አይ አይ

እህህ እሰከመቼ እህህ: አሀ አሀ አሀ

ልቤ በፍርሃት: እጅግ ተበክሏል

በርሃብ በጥማት: ሰውነቴ ዝሏል

እግሬ አልንቀሳቀስ: እጄ አልሰራ ብሏል

ጆሮኤም አልሰማ: አይኔም አላይ ብሏል

የራበኝ እንጀራው: ወይ እህሉ መስሏቸው

የጠማኝ ወተቱ: ወይ ጠጁ መስሏቸው

ችግሬ ጭንቀቴ: ምንጩ ያልገባቸው

ያቺ ሰው ተራበች: ሲሉኝ ሰማዋቸው

እኔን የራበኝ ፍቅር ነው: እኔን የራበኝ ፍቅር

እኔን የራበኝ ፍቅር ነው: እኔን የራበኝ አይ አይ አይ

እኔን የራበኝ ፍቅር: እኔን የራበኝ ፍቅር ነው

እኔን የራበኝ: አይ አይ አይ

እኔን የራበኝ ፍቅር: እኔን የራበኝ

እህህ እሰከመቼ እህህ: እእእ እስከመቼ

እህህ እሰከመቼ እህህ: ያዘላልቀናል

እህህ እሰከመቼ እህህ: ገና ብዙ መንገድ

እህህ እሰከመቼ እህህ: አበባው ሲረግፍ

እእ እሰከመቼ እህህ: ብዙ ይቀረናል

እህህ እሰከመቼ እህህ: ስሩ ሲበጣጠስ

እህህ እሰከመቼ እህህ: ዝም ብለህ አትየው

እህህ እሰከመቼ እህህ: ወድቆ ሲበሰብስ

እህህ እሰከመቼ እህህ: አይ አይ አይ

እህህ እሰከመቼ እህህ: አሀ አሀ አሀ

ጎጃም ያረሰውን: ለጎንደር ካልሸጠ

ጎንደር ያረሰውን: ለጎጃም ካልሸጠ

የሸዋ አባት ልጁን: ለትግሬ ካልሰጠ

የሀረር ነጋዴ: ወለጋ ካልሸጠ

ፍቅር ወዴት ወዴት: ወዴት ዘመም ዘመም

ሀገርም አለችኝ: ወገኔ ነው ህመም

ስሩ እንዳይበጠስ: መቋጠሪያው ደሙ

አረንጓዴ ቢጫ: ቀይ ነው ቀለሙ

እኔን የራበኝ ፍቅር ነው: እኔን የራበኝ ፍቅር

እኔን የራበኝ ፍቅር ነው: እኔን የራበኝ አይ አይ አይ

እኔን የራበኝ ፍቅር: እኔን የራበኝ ፍቅር ነው

እኔን የራበኝ አይ አይ አይ: እኔን የራበኝ

እኔን የራበኝ ፍቅር ነው: እኔን የራበኝ ፍቅር

እኔን የራበኝ ፍቅር ነው: እኔን የራበኝ አይ አይ አይ

እኔን የራበኝ ፍቅር: እኔን የራበኝ ፍቅር ነው

እኔን የራበኝ አይ አይ አይ

እኔን የራበኝ ፍቅር: እኔን የራበኝ ፍቅር ነው

እኔን የራበኝ አይ አይ አይ

እኔን የራበኝ ፍቅር ነው: እኔን የራበኝ ፍቅር

እኔን የራበኝ ፍቅር ነው: እኔን የራበኝ አይ አይ አይ

እኔን የራበኝ ፍቅር: እኔን የራበኝ ፍቅር ነው

እኔን የራበኝ አይ አይ አይ

እኔን የራበኝ ፍቅር: እኔን የራበኝ ፍቅር ነው

እኔን የራበኝ አይ አይ አይ

እኔን የራበኝ ፍቅር: እኔን የራበኝ ፍቅር ነው

እኔን የራበኝ አይ አይ አይ

በ1995 ዓ.ም ደግሞ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ አድዋ የሚሰኘውን ፊልማቸውን ለማሳየት ወደ አዲስ አበባ መጥተው ነበር፡፡ ቃለ-መጠይቅ ላደርግላቸው በወቅቱ ባልደረቦቼ ከነበሩት ጋዜጠኛ ሙሉጌታ አያሌው እና ከአብይ ደምለው ጋር ሆነን ከኃይሌ ገሪማ ጋር ውይይት አደረግን፡፡ ኃይሌ ገሪማ በጨዋታቸው መሐል እንዲህ አሉ፡፡ “አሁን ባለው ትውልድ ውስጥ አንድ ነበልባል ትውልድ ብቅ ብሏል፡፡ እነዚህም እጅጋየሁ ሽባባው እና ቴዲ አፍሮ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ባልተጠበቀ ፍጥነት እያመጠቁት ነው፡፡ እድሜ ሰጥቶኝ የነርሱን ተደጋጋሚ ስራዎች ማየት እፈልጋለሁ” አሉን፡፡ እጅጋየሁ ሽባባው የተወለደችው ቻግኒ ጐጃም ውስጥ ነው፡፡ አባቷ እናቷን ከአዲስ አበባ ጠልፈውና በፍቅርም ጭምር ወደ ቻግኒ ሄዱ፡፡ እዚያም ገጠር ውስጥ ገብተው በርሻ እና በንግድ መተዳደር ጀመሩ፡፡ የእጅጋየሁም የሙዚቃ እና የስነ-ፅሁፍ

ንቃት የጀመረው በዚሁ አካባቢ ነው፡፡ እናቷ መፃህፍት ለልጆቻቸው ያነቡላቸዋል፡፡ ይሄ የነ እጅጋየሁን የጥበብ ተፈጥሮ ይበልጥ ጐልቶ እንዲወጣ አድርጐታል፡፡ እህቶቿም ድምፃዊያት ናቸው፡፡ ከዚህ ሌላ የሚኖሩበት አካባቢ የቤተ- ክህነት ሊቃንት የተሰባሰቡበት ደብሮች አካባቢ ስለሆነ ልዩ ልዩ መንፈሳዊና ባህላዊ ዜማዎችንም በአእምሮዋ ስታዳብር አድጋለች፡፡ እቤታቸው ውስጥ ወደ ስምንት እህቶች እና ሁለት ወንድሞችም አሏት፡፡ ቤተሰቧ ትልቅ ቤተሰብ ነው፡፡ እዚህ ቤተሰብ ውስጥ እርስ በርሱ እንዲዝናና እነ ጂጂ ይዘፍኑለታል፤ ቴአትር ይሰሩለታል፡፡ በዚህም ሳቢያ የጂጂ የጥበብ ተሰጥኦ እየዳበረ መጣ፡፡ ከዚህ በኋላ የሙዚቃ ፍቅሯ እየገዘፈ ሄደ፡፡ ሙዚቃን እስከ ጥግ ድረስ የምታውቅበትና በነፃነት የምትዘፍንበትን መንገድ

ሁሉ ትፈልግ ጀመር፡፡ ቤተሰቦቿ በባህር ዳር ከተማም ጥሩ መተዳደሪያ እና ኑሮ ቢኖራቸውም እሷ ሙዚቃን ፍለጋ ትዞር ጀመር፡፡ አዲስ አበባ መጣች፡፡ ሴንት ሜሪ የሴቶች ት/ቤት ገባች፡፡ ግን ትምህርቷን እያቋረጠች ሙዚቃን ማሠስ ጀመረች፡፡ በየቦታው መዝፈን ጀመረች፡፡ በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴስም አማካኝነት ወደ ውጭ ሀገር እየተዘዋወረች ሙዚቃዎች አቀረበች፡፡ በብርሃነ መዋ ፊልም ላይም በትወና ተሳተፈች፡፡ እውነተኛዋን ጂጂ ልታገኝ ግን አልቻለችም፡፡ ሙዚቀኛዋ ጂጂ ጠፋች፡፡ ኬንያ ሄደች፡፡ እዚያም ጂጂን ለማግኘት የሙዚቃ ባንድ አቋቋመች፡፡ አሁንም ጂጂ አልተገኘችም፡፡ ኬንያን ጥላ ወደ አሜሪካ ሄደች፡፡ የጂጂ መስመር የተሳካ ሆነ፡፡ የሙዚቃ ሊቆች ደብር ውስጥ ገባች፡፡ ባለቤቷንም ያገኘችው በምድረ አሜሪካ ነው፡፡ የድምፅ ኢንጅነር ነው፡፡ ከአንድ ሺ ያላነሱ የተለያዩ ድምፃዊያንን

ሙዚቃዎች ሰርቷል፡፡ ከዚህ ሰው ጋር የመሰረተችው ጥምረት የዛሬዋን ስመ ገናና ጂጂን እንዳስገኘ ራሷ ጂጂ አዲስ አበባየመጣች ሰሞን ነግራን ነበር፡፡ ጂጂ ዘንድ ያለው የስነ-ግጥም፤ የድምፅ፤ የዜማ እና የታሪክ እውቀት ከባለቤቷ የሙዚቃ ቅንብር ሊቅነት ጋር ተዋህደው የኢትዮጵያን የሙዚቃ ስልት ሀገርኛ ለዛና ውበት ሰጡት፡፡ የኢትዮጵያንም ስም በትልልቅ ቦታዎች ማስጠራት ጀመሩ፡፡ እውነተኛዋ ጂጂ ከተገኘች በኋላ እስከ አሁን ድረስ ወደ

ስድስት አልበሞች ታትመዋል፡፡ በሁሉም ስራዎቿ የተዋጣላቸው ሙዚቃዎች እንደሆኑ በሰፊው ይወሳል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የሥነ-ፅሁፍ ሰዎች የጂጂን የዘፈን ግጥሞች በተደጋጋሚ ሲመዝኗቸው ቆይተዋል፡፡ ኢትዮጵያዊ ለዛ እና ስሜት በስፋት የሚንፀባረቁባቸው እንደሆኑ ያወሳሉ፡፡

ለምሳሌ “ካህኔ” በሚለው ዘፈኗ የኢትዮጵያን ቤተ-ክርስትያን “ጉባኤ ቃና” የሚመስል ስልት ይዞ መምጣቱን ይናገራሉ፡፡

በቃላት ድርድር

በሙዚቃ ቃና

ስሜት ስታብራራ ነፍሴ

ስታጣራ አየሁኝ ጥበብ

ሰማሁኝ እውቀት

ልናገር ልመስክር

የዚህን ሰው ቅናት

እያለች ለየት ባለ የሙዚቃ ስልት ታወርደዋለች፡፡ የጂጂ ጭንቀት የስንኞች ቤት መምታት አይደለም፡፡ የምትዘፍንለት ታሪክ የዜማው አወራረድ ከገጠመላት ብቻ ነው የምታዜመው፡፡

የጂጂ ሙዚቃዎች በግጥም ስልታቸው ተራኪ ስንኞች (Narrative Verses) ናቸው፡፡ የታሪክን፤ አንድ የተወሰነ ጉዳይን፤ የነበረ ጉዳይን በሙዚቃዎቿ ትተርክልናለች፡፡ በዚህም ሳንወድ በግዳችን በፍቅር እናደምጠዋለን”:: ለዚህም “አባይ”፣ “ካህኔ”፣ “ናፈቀኝ” እና ሌሎችም በርካታ ዘፈኖቿ ይጠቀሳሉ፡፡ የጂጂ ሙዚቃዎች የጃዝ ስልትን በስፋት የያዙም እንደሆኑ ይወሳል፡፡ ጃዝ ደግሞ ተራኪ ለሆኑ ድምፆች እጅግ ተስማሚ ነው፡፡ ጂጂ ራሷ ስትናገር ሙዚቃዎቿ የጃዝ አቀራረብን በስፋት እንደያዙ ታወጋለች፡፡

እጅጋየሁ ሽባባው ጂጂ የታላቁን ደራሲ የሀዲስ ዓለማየሁን ፍቅር እስከ መቃብር ልቦለድ መፅሐፍን መነሻ በማድረግ በአባ ዓለም ለምኔ ስም ውብ ቅላፄ ያለው ሙዚቃም ሰርታለች፡፡

ይህ ደግሞ ደራሲ ሀዲስ በህይወት እያሉ የተሰራ በመሆኑ ራሳቸውም አዳምጠውታል:: በሙዚቃው እጅግ መገረማቸውንና መደሰታቸውን በወቅቱ ጠይቀያቸው በትሁት

አንደበታቸው ገልፀውልኛል፡፡ በዚህም በሥነ-ፅሁፍ አለም ውስጥ ያሉ ከያኒያን ሁሉ ልብ ውስጥ ዘልቃ የገባች ድምፃዊት እንደሆነች በወቅቱ የታተሙ ጋዜጣና መፅሔቶች ፅፈውታል፡፡

የእጅጋየሁ ዘፈኖች ለልዩ ልዩ ፊልሞችም ማጀቢያ (Sound Track) ሆነው አገልግለዋል፡፡ ኢትዮጵያ የሚለው ዘፈኗ “ያልደረቀ ዕንባ” ለተሰኘው ፊልም ሲያገለግል በኃይሌ ገብረስላሴ ህይወት ላይ ተመርኩዞ የተሰራም ፊልም የጂጂን ሙዚቃ በዋና አጃቢነት ተጠቅሞበታል፡፡ በአሜሪካም ሀገር ለተሰሩ አለማቀፍ ፊልሞች ጂጂ የማጀቢያ ሙዚቃ ሰርታለች፡፡

ጂጂ ከሙዚቃ መሳሪያዎች ክራርን፤ ማሲንቆን፤ ጊታርና ኪቦርድ ትጫወታለች፡፡ ክራርና ማሲንቆ የተማረችው ኢትዮጵያ እያለች ከሙዚቃ መምህሩ ከአለማየሁ ፋንታ ዘንድ ነው፡፡

አለማየሁ ፋንታ ጋር ያገናኟት ደግሞ የሙዚቃ ፍቅሯ ሀያል መሆኑን የተገነዘቡት አባቷ ናቸው፡፡ አባቷ በመጀመሪያ ድምፃዊ እንዳትሆን በንስሐ አባት ሁሉ አስመክረዋት ነበር፡፡ አሻፈረኝ ማለቷን በማየት ነው የጉዞዋን መንገድ ማቅናት የጀመሩት፡፡ ለጂጂ የሙዚቃ ስብዕና መሟላት ከፍተኛውን አስተዋፅኦ ካደረጉላት ሰዎች መካከል አንዷ እናቷ ናቸው፡፡ በቤት ውስጥ

የሚያነቡላት ግጥም እና ልዩ ልዩ የሥነ-ፅሁፍ ስራዎች የዛሬዋ ጂጂ እንድትፈጠር ማድረጉን ራሷ ትናገራለች፡፡ እናቷ ከዓመታት በፊት የፃፉትን የራሳቸውን ረጅም ልቦለድ አሳትመዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው የጥበብ ተሰጥኦው ከእናቷ ዘንድ መሆኑንም ጭምር ነው፡፡ ባጠቃላይ እጅጋየሁ ሽባባው የኢትዮጵያን ታሪክ፤ ባህል፤ ቅርስ፤ መልካም ገፅታ፤ ጥንታዊነቷን፤ ያልተነካ የድንግል

ውበት ባለቤት መሆኗን ለዛ ባላቸው ሙዚቃዎቿ በማቀንቀን ትልቅ ስፍራ የሚሰጣት ናት፡፡ የአፍሪካ ሕብረት ስብሰባን የመሳሰሉ ታላላቅ ጉባኤዎች ሲኖሩ እንዲህች ዓይነቷን

ኢትዮጵያዊት የጥበብ ሰው መድረክ አዘጋጅቶ መጋበዝ ለሀገርም ለወገንም ይጠቅማል የሚሉ በርካቶች ናቸው፡:

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top