Connect with us

ከቁዘማ መልስ

ከቁዘማ መልስ
Photo: Social media

ማህበራዊ

ከቁዘማ መልስ

ከቁዘማ መልስ

(ሙክታሮቪች ዑስማን)

በሀገር ጉዳይ መረጃ ማቅረብ የመንግስት ግዴታ ነው። የዜጎች መብት ነው። በርግጥ የጦርነት መረጃ ሁሉም ያለወቅቱ አይነገርም። ነገር ግን መሰረታዊ መረጃዎችን መንግስት ለዜጎች ማድረስ አለበት። መረጃን በማፈን እየደረሰ ያለው ከፍተኛ ውዥንበር ነው። በዚህም ምክንያት ማህበራዊ ሚዲያው የጁንታው የፕሮፓጋንዳ መጫወቻ ሆኗል። በመረጃ ጨለማ ውስጥ የወገን ድል እየኮሰመነ የጠላት የተጋነነ ወሬ መንደሩን እያመሰው ነው።

መንግስት የፕሮፓጋንዳ እና የካውንተር ፕሮፓጋንዳ ፅንሰ ሀሳብም ያለው አይመስልም። የጁንታው ፕሮፓጋንዳ ክፍል እየሰራ ያለው ሀሰትን ከእውነት የቀላቀለ ነገርግን የተዋጣለት ፕሮፓጋንዳውን ማፍረስ የሚችል ካውንተር ፕሮፓጋንዳ ላይ መንግስታችን ከምኑም የለበትም። ከመገረም ውጪ ምን ማለት ይቻላል።

ኢትዮጵያ እውነትን ታቅፋ በሀሰት ስትደበደብ ባለስልጣናት አንቀላፍተዋል። አንዳንዱ ጁንታው ቢመለስ ሸሚዙን አውልቆ ለመቀላቀል ያሰበ ይመስላል። የፌደራል፣ የክልል እና የየወረዳው ኮምኒኬሽኖች በግልፅ አመራርና ተልዕኮ የሰጣቸው አካል የለም ለማለት ያስደፍራል። በተለይ በዚህ ጦርነት ላይ የጠራ አቋም የላቸውም። ጠላት ባመረረበት መጠን አላመረሩም። በወላዋይነት የተቸገሩ ይመስላል። 

ወደ ጠቅላያችን ስንመጣ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው ያለው። የስንዴ ማሳን መጎብኘት ምንም ችግር የለውም። ኢትዮጵያ በተራበ ዜጎችዋ ሆድ ነው ምዕራባውያን እጇን ለመጠምዘዝ ዘውትር የሚታትሩት። በምግብ እራስን መቻል ብዙ ችግርን ይቀርፍልናል። ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትራችን የሚናገሩት ቃልን ደጋግመው ማሰብ አለባቸው። የኢትዮጵያ ህዝብ መሪውን ያከብራል። የመሪውን ቃል በአፅኖት ነው የሚያዳምጠው።

በዚህ የጦርነት ወቅት፣ ጠላት ህዝባችንን እየጨፈጨፈ ፣ መንደር እያወደመ፣ ዘግናኝ ግፎችን እየፈፀመ፣ የጦር ጀግንነትን እና የዘመቻን አስፈላጊነት ከጥያቄ የሚያስገባ አገላለፅ በፍፁም መጠቀም የለባቸውም። የኢትዮጵያ ህዝብ በጠላቱ ላይ እንዲጨክን ኢትዮጵያዊ ወኔ መቀስቀስ እንጂ፣ የአባቶቹን ታሪክ እያስታወሱ ለወኔ ስንቅ የወታደሩን እና የደጀን ሀዝብን መንፈስ ማነቃቃትና ማነሳሳት እንጂ: መዝመት፣ ጦርና ጋሻን ማዘጋጀትን መኮነን ከሀገር መሪ አይጠበቅም።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር አውዱን ለማስረዳት የሚሻ ወዳጅ ሊኖር ይችላል። ወሳኙ አውዱ አይደለም። ጠላት ሊጠቀምበት የሚችልን አነጋገር ቀድሞ አስቦ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ሀገር በጦርነት አሳርዋን እያየች ከወሎ ህዝብ ውጪ ያለው የሀገር ሰው እንደ የአዘቦት ቀን ውሎ ሁሉን ትቶ ለሽ የሚለው መሪው በየጊዜ በቲቪ፣ በሬዲዮና በማህበራዊ ሚዲያ ስለማያነቃው ነው። 

ወሎ እየደማ የአማራ ክልል እንኳ በሹም ሽር ውስጥ ነው ጊዜውን የሚያባክነው። እለታዊ መረጃዎች እያሸቆለቆሉ መጥተዋል። በዚህም ዜጎች ለጁንታው ውዥንብርና ለአሉባልታና የሀሰት ናዳ ተጋልጠዋል። የኢትዮጵያ ህዝብ በጭንቅ ወቅት ቆራጥና ቆምጨጭ ያለ መሪ ነው የሚሻው።

ስለሀገር ግድ ብሎን ከትህነግ ጋር በዚህ የዲጂታል አለም ስንታገል ቀን ከሌሊት እንቅልፍ የምናጣ ልጆች አለን። እኔን በተመለከተ በልበ ሙሉነት የምናገረው ማንም አካል ይህን ፃፍ ብሎኝ አያውቅም። በጥቅም ተታልዬ አላውቅም። ሆኖም የምዕራባውያንን ፈረስ ተፈናጦ እየመጣ ያለውን ወያኔን ለመታገል ይህ መንግስት ከነድክመቱ ሊደገፍ ይገባል ብዬ በማመን ደግፌዋለሁ። ለሀገሬ ይጠቅማል ያልኩትን ሳደርግ ሰንብቻለሁ።

ሰሞኑን ግራ ገባኝ፣

የመንግስትነትን መቀመጫ ካመቻቸ በኋላ አካሄዱ ግን ግራ ነው። መያዣ መጨበጫ የለውም። የፕሮፓጋንዳ እና የካውንተር ፕሮፓጋንዳ ክፍሉን በማደርጀት፣ የማስታወቂያ እና የህዝብ ግኑኝነት ክፍሉን አጠናክሮ ሀገርን እንደመታደግ አክቲቪስቶችን ማስፈራራት ስራዬ ብሎ የያዘው ይመስላል። እኔ በመረጥኩት ጊዜ ብቻ ልናገር እናንተ ዝም በሉ ሊል ይቃጠዋል። የመረጃን እና የፕሮፓጋንዳን ሀያልነት አለማወቅ ነው። የእኛን አፍ ቢዘጋም የጠላትን መዝጋት አልተቻለውም። ህዝብ ለውዥንብርና ለሀሰተኛ ዜና ደርጎታል። ምንም ነገሩ አላማረም። የገባንበት ጦርነትን አጣዳፊ ሁኔታ የተገነዘበ አይመስልም።

በመጨረሻ፣

ስለ ወዳጄ ሱሌማን አብደላ ትንሽ ልበል። የመንግስትን ዳተኝነት በብዙ መልኩ ያስረዳል። ሱሌማንን ለናንተ አልነግርም። ስንት በዶላር የሚከፈላቸውን ዲፕሎማትና አምባሳደሮች ያልሰሩትን ስራ ለሀገር የሰራ ድንቅ ልጅ ነው። ብቻውን ተቋም የሆነ የኢትዮጵያ ጠበቃ የሆነ ልጅ ነው። የአረብ ሀገራትን እያንዳነዱን ድርጊት ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም አንፃር እየተነተነ ዜጎችን ሲያነቃ የነበረ የልጅ አዋቂ ትልቅ የሀገር ሀብት የሆነ ልጅ ነው። በቲዊተር የኢትዮጵያን እውነት የሞገተ ልጅ ነው። ቲዊተርን ከወዳጆቹ ጋር በመሆን ከጁንታው የሀሰት ናዳ ያዳነ ልጅ ነው።

ሱሌማን የደህንነት ችግር ገጠመው። አባ ከና የሚለው ጠፋ። የቆመላት ሀገር ልትቆምለት ይገባ ነበረ።

ለዚህ ልጅ የኢትዮጵያ ሳውዲ ኢምባሲ ጥበቃ ማድረግ ይችል ነበረ። አላደረገም። የውጪ ጉዳይ ትዕዛዝ በመስጠት ሱሌማንን ያለበትን የደህንነት ችግር መቅረፍ ይችል ነበረ። አልቻለም። ይህ ምን ማለት ነው። ዳተኝነት ብቻ አይገልፀውም። ለሀገር የሚሟገትን ወገን  ሁሉ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ መቸለስ ነው።  ያበሰጫል።

ሳይረፍድ አሁንም የውጪ ጉዳይ አቶ ደመቀ ለአምባሳደር ሌንጮ ባቲ ትዕዛዝ ማስተላለፍ ሊታደጉት ይገባል።

በተረፈ፣ እኔም ከቁዘማዬ ወጥቼ ወደ ትግሉ ተመልሺያለሁ። 

ለሀገር የሚጠቅም ትግል ለማድረግ በአዲስ መንፈስ ተነሳስቼኣለሁ። ለሀገር የሚጠቅም ማለት መንግስት ሊያስተካክለው የሚገባን ጉዳይ አንስቶ መተቸትን ይጨምራል። ይህ የማይዋጥለት ከፈለገ ጠንካራ ቅርንጫፍ ያለው ረጅም ዛፍ ፈልጎ እራሱን ይስቀል። እዚህ ስሰደብ የምውለው ለሀገር እንጂ የማንንም ወንበር ለመጠበቅ አይደለም።

ትግሉ ይቀጥላል።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር

Click to comment

More in ማህበራዊ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top