Connect with us

በዋቤ ሸለቆ ከጉራጌ ደግ ልብ ጋር 

በዋቤ ሸለቆ ከጉራጌ ደግ ልብ ጋር
ሄኖክ ስዩም

ማህበራዊ

በዋቤ ሸለቆ ከጉራጌ ደግ ልብ ጋር 

በዋቤ ሸለቆ ከጉራጌ ደግ ልብ ጋር 

(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ወደ ዋቤ ሸለቆ ወርዷል፡፡ የውሃ ቱሪዝም የማትተዋወቀዋ የውሃ ማማዋ ኢትዮጵያን ከውሃ ቱሪዝም ለማቆራኘት ባለ ራዕዮች ዋቤ ሸለቆ ሲወርዱ አብሬ ወርጄ ተአምር አየሁ ሲል ትረካውን ይጀምራል፡፡)

(ሄኖክ ስዩም -ድሬ ቲዩብ)

ይህ የወደ ዋቤ ሰዎች ውሎ ነው፡፡ ዋቤ ሸለቆ ከደረሱ ሰዎች አንዱ ነኝ፡፡ ይበልጣል ጸዳሉ ታላቁ የ “Mystery of the Nile” ዘጋቢ ፊልም ሲሰራ አብሮ የነበረ ኢትዮጵያዊ የውሃ ቀዘፋ አስጎብኚ ነው፡፡ ሙሌና ኤንዲ የሚባሉ ብርቱ ወጣቶች ተጣምረውት  ኢትዮጵያን ከውሃ ቱሪዝም ሊያቆራኙ መንገድ ጀምረው ዋቤ ደርሰዋል፡፡ አብሬ አለሁ፡፡

ዋቤ የኦሞ መሃጸን ነው፡፡ የግቤ ጉልበት፤ ከዚያ በኋላ ሩቅ ተጓዥ፡፡ መነሻው 2850 ሜትር ከፍታ ያለው የጉራጌ ዞን ደጋ ምድር ነው፡፡ ከዚያ ውብ ሸለቆ ይሰራል፡፡ በእነ ኮሬብ ወንዞች ጉልበት ጉልበተኛ ይሆናል፡፡ ድንቅ ውበት በፈጠረ ምድር ሾልኮ ያልፋል፡፡

እንዲህ ከሚያልፍበት ስፍራ አንዱ ጋር ደርሰናል፡፡ ቅድስት የምትባል መልካም ሰው ከወንድሞቻችን ጎን ቁማ የሀገር ልጅ ዋቤን ሊቀዝፍ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ በወንድማችን ይበልጣል ስም travel251ን አመስግነናል፡፡

ድንኳናችን ተከልን፡፡ ዋቤ ድምጹ ይሰማል፡፡ ከዚህ ቀደም አንድ ዙር ስፍራው የወንዝ ቀዘፋ ተሞክሮበታል፡፡ አሁን ሌላ ዙር ነው፤ ግን የማይቆም፣ ሌሎች ወንዞችን ለመድፈር ህብረት የገመደው አብሮ መስራት እየተበሰረበት ያለ፡፡

ዋቤ በነሐሴ ቁጡ ነው፡፡ ደግሞ በመስከረም ቁጣውን ቀንሶ ውበቱን ይጨምራል፡፡ በጥቅምት ሌላ መልክ አለው፡፡ ወዲያ የጉራጌ ዞን ሌላ ወረዳ ነው ያለሁበት ደግሞ ሌላ ወረዳ፤ መካከላችን የተፈጥሮ ድንበር አለ ዋቤ ወንዝ፡፡

ዋቤ ቀላል ወንዝ አይደለም፡፡ ታላቁ የኦሞ ወንዝ ባለድርሻ ነው፡፡ ብዙ ዘመና ለጉራጌ ምድር ፈተና ሆኖ ኖሯል፡፡ ማዶና ማዶው እንዳይገናኝ የክረምት አበሳ ነው፡፡ ብዙ ሰው ይዞ ሄዷል፤ ብዙ እናት ከምድሩ ነጥቋል፡፡ ዛሬ ብዙ ቦታዎች ላይ ጉልበቱን ዘመን ረትቶታል፡፡ ድልድዮች ተሰርተዋል፡፡ ነገ ከዚህ የበለጠ አንገቱን ደፍቶ የሚገማሸርበት ቀን አለ፡፡ ውበት እንጂ ሞት፣ ልማት እንጂ ጥፋት የማይሆንበት ቀን ይቀርባል፡፡

የዋቤ ሸለቆ ከግቤ ሸለቆ የሚገጥም ውብ ምድር ነው፡፡ ብዙ ሀብት ያለው የወንዝ ዳር ዛፎች በዳርቻዎቹ የተገጠገጡበት፣ በርካታ ዱር እንስሳት የሚኖሩበት ለኦሞ የታችኛው ምድር ጤና መሆን ትርጉም ያለው አከባቢ፤

አንድ ቀን ዋቤ ሸለቆ ከዚህ የበለጠ ተጠብቆ የግቤ ዋቤ ብሔራዊ ፓርክ ሊሆን ይችል ይሆናል፤ ማን ያውቃል፤ የዋቤ ሸለቆ ማኅበረሰብ አቀፍ ጥብቅ ስፍራን እውን ሆኖ እናይም ይሆናል፡፡

ማኅበረሰቡ ደግ ነው፤ ልጆች እንዴት እንደተቀበሉን ሳስብ ልቤን ይሞቀዋል፡፡ ጉራጌ እንዲያውም እንዲያው ነው እንኳን ደጃፉ ደርሰውለት፡፡ ያሳሰባቸው የእኛ ሜዳ ላይ ማደር ነበር፤ ሁሉም ሰው ፊት ወሄም የሚል ደስታ አለ፡፡

ድንኳኖቻችን ጣልን፤ መንደሮቻችንን መሰረትን፡፡ ለማብሰያ የምትሆነው የዛፍ ጉያ ጎጆ ቀለስን፡፡ ሁለት አዳር እዚህ እንዲህ ባለ መልኩ እናሳልፋለን፡፡ ጥላ ሲበርድ ወደ ዋቤ ወንዝ እንገባለን፡፡

 

Click to comment

More in ማህበራዊ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top