በኢትዮጵያ ፀሐይ ያጠላው ጥቁር ደመና
(ፍትሕ መጽሔት ~ ቹቹ አለባቸው )
የኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነት ከ120 ዓመት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በተለይ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ የወዳጅነቱ መሰረት የተጣለበት ነበር፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ በወታደራዊ፣ በትምህርት፣ በግብርና፣ በጤና… ትርጉም ያለው ድጋፍ አግኝታለች፡፡
የፋሽስት ጣሊያን የአምስት ዐመት ወረራ በ1933 ዓ.ም በአርበኞች ከተቀለበሰ በኋላ፤ አንዳንድ አገራት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማዳከም ያደረጉትን ሙከራ፣ የዐፄው መንግሥት የአሜሪካንን አጋርነት በመጠቀም ማክሸፉም ይታወሳል፡፡
ይህ የውጭ ጉዳይ ባህል፣ ሌሎች ነፃነታቸውን ጠብቀው የኖሩ አገራት የተጠቀሙበት ቢሆንም፤ የአሜሪካንን አጋርነት አጉልቶ ያሳየ ነበር፡፡ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ መስራች ብትሆንም፤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታና የማቋቋሚያ አስተዳደር ተጠቃሚ መሆን የቻለችውም በአሜሪካ አጋርነት ነበር፡፡
ኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ ፀረ-አፓርታይድ እና ፀረ-ቅኝ አገዛዝ የትግል ታሪክ የነበራት ተሳትፎና ተጽእኖ ከአህጉሩም ተሻግሮ፤ ለሌሎች አገራት በአርአያነት ይጠቀሳል፡፡ ይህንን የታሪክ ሀዲድ አስጠብቃ መጓዝ በመቻሏም ነበር፣ በኮሪያ ዘመቻ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከአሜሪካና ሌሎች የተባበሩት ኃይሎች ጋር ለኮሪያውያን ነፃነት የተዋደቁት፡፡ ይህ ገድል፣ በተራ የፖለቲካ ኃይሎች አሰላለፍ የተፈጠረ ሳይሆን፤ ለዓለም ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌት የመሆን የታሪክ አስገዳጅነት ያመጣው ዕድል ነበር፡፡ በርግጥም ይህ የነፃነት ጥብቅና ነው፣ የኢትየጵያና የአሜሪካ ወታደሮችን ከጥምር ጦሩ ጋር በአንድ ምሽግ አውሎ-ያሳደረው፡፡
በዚህ መሰል አጋርነት ከፍ ያለው የሁለቱ አገራት ወዳጅነት፣ የጋራ ጉዳዮቻቸው እያደጉ መምጣታቸውን ተንተርሶ፣ 32ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሩዝቤልት “ተገናኝነተን እንወያይ” የሚል ጥያቄ፣ ለቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አቀረቡላቸው፡፡ የግንኙነት አካል የሆነውና በታሪክ የሚጠቀሰው ‹የስዌዝ ካናል ምስጢራዊ ጉዞ›ም፣ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ወሳኝ እንደነበረ አመላክቷል፡፡ ሁለቱ መሪዎች በመከሩበት ወቅት፣ በኢትዮጵያ በኩል ስድስት ነጥቦች የቀረቡ ሲሆን፤ የውይይቱ ማሰሪያ የኢትዮጵያ ነፃነት በማንም ሊደፈር እንደማይችል በጋራ ወዳጅነት መተባበረን ማዕከል ያደረገ ነበር፡፡ (ዘውዴ ረታ፣ “የቀ.ኃ.ሥ. መንግሥት” ገጽ 512)።
የሁለቱ መሪዎች ግንኙነት ፍሬ አፍርቶም በርካታ ወታደራዊ መኮንኖች በስመጥሮቹ የአሜሪካ ኮሌጆች ወታደራዊ ሳይንስ እንዲማሩ አድርጓል፡፡ ይህን ታሪክ ለአብነት አነሳን እንጂ፤ በጂኦ-ፖለቲክሱና ዘርፈ-ብዙ በሆኑ መስኮች በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ፈጥረው የነበረ መሆኑ መሬት የረገጠ እውነታ ነው፡፡
በ1966ቱ አብዮት ማግስት…
ኢትዮጵያ የሥርዐት ለውጥ ካደረጋች በኋላ፣ ከአሜሪካ ጋር የነበራት ወዳጅነት የተቀዛቀዘ ቢመስልም፤ ከውጭ ፖሊሲ አኳያ በተፈጠረው መዛነፍ፣ የሁለቱ አገራት ግንኙት ሻክሯል፡፡
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዋና ዋና ዓላማዎች የአገሪቱን ደህንነት፣ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ስለመሆኑ በተለያየ የታሪክ ምዕራፍ ታይቷል:: በደርግ መንግሥት የአገር ውስጥና የውጭ የደህንነት ሥጋት ተጋርጦ ስለነበረ፣ እንደቀደመውሁሉ፤ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ለሉዓላዊነትና ለግዛት አንድነት የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ ቆይቷል። በዚህ የታሪክ እውነታ ውስጥ፣ ኢትዮጵያ በተስፋፊው የዚያድ ባሬ ጦር 700 ኪ.ሜ. ድንበሯ ተጥሶ ሲወረር፤ አሜሪካ የጦር መሳሪያ ግዥ ክልከላ ከማድረግ አልፋ፣ ለወራሪው ኃይል መወገኗ ኢትዮጵያውያንን ያሰከፋ ጉዳይ ነበር፡፡
ደርግ የሶሻሊዝም ርዕዮት አቀንቃኝ ቢሆንም፤ በ17 ዐመት አገዛዙ፣ ወደ ምስራቁ ጎራ ይበልጥ ያጋደለው በዚያድ ባሬ ወረራ ጊዜ፣ አገሪቱ ላይ የተጣለው የጦር መሳሪያ ግዥ ማዕቀብና ክልከላ ከባድ የመገፋት ስሜት ያሳደረበት እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ፡፡ በምክንያትነት የሚቀርበው ደግሞ፣ በየዘመኑ እንደታየው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዋና ዋና ዓላማዎች፡- የአገሪቱን ደህንነት፣ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ከመሆኑ ጋር ይያያዛል፡፡ ከዚህ መርህ ጋር የሚቃረኑ ውሳኔዎች ኢትዮጵያን የሚጎዱ በመሆኑ ተቀባይነት አልነበራቸውም፡፡
ድኀረ-ደርግ
በድኀረ-ደርጉ ሥርዐት፣ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ወደ ዐዲስ ምዕራፍ ያደገ ሲሆን፤ በተለይ የቀጠናውን ሰላምና ፀጥታ በማስጠበቅም ሆነ ሽብርተኝነትንና አክራሪነትን በጋራ በመከላከሉ ረገድ፣ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ስታደርግ የቆየችው ትብብር ያስመሰግናታል፡፡ የአሊተሓድ፣ አል-ኢስላሚያ፣ የአልሸባብና የአልቃይዳን የሽብር ጥቃት አፍኖ ለማስቀረት በተደረገው ትግልም፣ የኢትዮጵያና የአሜሪካ የጋራ መደጋገፍ ትርጉም ያለው ለውጥ የተመዘገበበት ነበር ቢባባል ማጋነን አይሆንም፡፡
ከንግድ ጋር በተያያዘም፣ የቦይንግ አውሮፕላን ግዥን ጨምሮ፤ በሌሎች ዘርፎች ያለው የንግድ ትስስር በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በአሜሪካ የተሰጣት ከታሪፍና ኮታ ነፃ የሚያደርገው “AFRICAN GROWTH AND OPPORTUNITY ACT (AGOA)” ዕድልም በቀላሉ አይታይም፡፡ በትንሹ ለአንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ምንም እንኳ የምስራቁ አገራት ኢንቨስተሮች፣ በዚህ ዕድል ሰፊ ተጠቃሚ ቢሆኑም፤ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን በማግኘት ላይ ያሉት ጥቅም፣ ለነገ ትልቅ ዐቅም የሚፈጥር ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለኢኮኖሚ ልማት አጋዥ የሚሆኑ የፋይናንስ፣ የቴክኒክና ሰብዓዊ ድጋፍ ማግኘት፣ በአገሪቱ መልካም አስተዳደር የማስፈንና የዴሞከራሲ ሥርዐት ግንባታ እንቅስቃሴ በማድረግ በትብብር መሥራት ትኩረት ትሰጣለች፡፡ በእነዚህ መስኮች ከአሜሪካ ጋር አበረታች የሆነ ድጋፍና ትብብር አለን፡፡
ይህ ሁሉ መልካም ትስስር ግን፣ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንድትገባ ቀዳዳ የሚፈጥር አይፈቅድም፡፡
የህልውና ዘመቻውና ሉዓላዊነት፣
በሥራ ላይ ያለው የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲና ትግበራ ትብብርን፣ የጋራ ጥቅምንና ሉዓላዊነትን በማስከበርም ሆነ በማክበር ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይሁንና አሸባሪው ትሕነግ ጦርነት በመክፈቱ፣ ሕግ የማስከበር እርምጃ መውሰድ ከተጀመረ ወዲህ፣ የአገሪቱን ሉዓላዊነት በሚጋፋ መልኩ አሜሪካና ሸሪኮቿ ተጽዕኖና ጫና እያሳደሩ ነው፡፡
በዛሬቷ ኢትዮጵያ ከውስጥና ከውጭ የተጋረጠውን ብሔራዊ አደጋ ለመቀልበስ፣ መንግሥትና ሕዝብ የጋራ ዐቅም ፈጥረው ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ነው፡፡ ይሁንና፣ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያለቸውን ኢትዮጵያ፣ ሱዳን ሉዓላዊነቷን ስትጋፋ ‹ድርጊቱ ተቀባይነት የለውም› ብሎ ከማውገዝ ይልቅ፤ ዝምታን የመረጡ አካላት በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት መፈለጋቸው፣ የቀደመውን ታሪካዊ ግንኙነት እንደማበላሸት ይቆጠራል፡፡
የኢትዮጵያ ወዳጆች የዘነጉት አልያም ማስታወስ ያልፈለጉት፣ ትሕነግ በተፈጥሯዊ ባህሪው እኩልነትን የማይቀበል ፀረ-ሕዝብ መሆኑን ነው፡፡ ዓለም ከደረሰበት የዴሞክራሲ እሴት ጋር አብሮ መጓዝ የማይችል ኋላቀር ድርጅት ነው፡፡ በማኒፌስቶው፣ በግልጽ ዐማራን በጠላትነት የፈረጀ፣ ወደ ሥልጣን ከወጣ በኋላም ዐማራን ለማጥፋት ፋሽስቶች የጣሉትን የማጥቂያ ስልት የተከተለ ቡድን ነው፡፡ እጁም በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ የንፀሃን ደም ተነክሯል፡፡ በፖለቲካ ሴራውና ቀጥተኛ እርምጃው በኢትዮጵያ ደም ያልፈሰሰበት መሬት፣ ጥቃት ያልተፈጸመበት ብሔር የለም፡፡ በዘር ማጥፋት ወንጀል መጠየቅ ያለበት ስለመሆኑም፣ በ27 ዐመት ዘመነ-መንግሥቱ ከኦጋዴን እስከ ጋምቤላ፣ ከሎቄ እስከ ወልቃይትና ራያ… የፈጸማቸው ጭፍጨፋዎችዋቢ ናቸው፡፡
በገዥው ፓርቲ ውስጥ በነበሩ የለውጥ ኃይሎች ውስጣዊ ፍላጎትና በሕዝብ ግፊት የመጣውን የፖለቲካ ለውጥ ለማጨናገፍም፣ ከመጋቢት 2010 እስከ ጥቅምት 2013 ዓ.ም ድረስ ከትግራይ ክልል በቀር፣ 113 ያህል ጥቃትና ግጭቶችን አቀነባብሯል፡፡ በዚህም በርካታ ንፁሃንን ገድሎሏል፤ አስገድሏል፡፡ የአገሪቱን ሰባ ከመቶ የሕዝብ ቁጥር የሚሸፍኑትን ዐማራና ኦሮሞን በማጋጨት ፖለቲካ ለመሥራት፣ በርካታ የጥፋት ድርጊቶችን ቢፈጽምም፤ ዋጋ እየተከፈለም ቢሆን፣ በወንድማማችነት ስሜት ችግሮችን ተቋቁሞ ማለፍ ተችሏል፡፡
ለውጡን በዚህ መንገድ ለማጨናገፍ ሲሞክር የነበረው ትሕነግ፣ የሀገረ-መንግሥቱ የመጨረሻ ምሽግ በሆነው የመከላከያ ሠራዊቱን ሰሜን ዕዝ ከጀርባ በመውጋት ክህደት ፈጽሟል፡፡ ድንገት የተጠቃው የኢትዮጵያ ሠራዊት አልሸባብን የመሰሉ የአፍሪቃ ቀንድ ሽብርተኛ ቡድኖችን በመደምሰስ፣ ለቀጣናው ያለው የሠላም አበርክቶ ፋይዳው የበዛ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሠራዊቱ ለሠላም ማስከበር በተመሰማራባቸዠው ተልዕኮዎቹ ሁሉ የተመሰገነ ስለመሆኑ ዓለም ዐቀፉ ማኀበረሰብም የሚመሰክረው እውነታ ነው፡፡
የፌዴራሉ መንግሥት ለትግራይ አርሶ ዐደር የእርሻ ወራት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርና ለመላ ሕዝቡም የጥሞና ጊዜ ለመስጠት፣ በሰኔ አጋማሽ የተናጠል የተኩስ አቁም ቢያውጅም፤ ከሥልጣን ጥመኝነቱ በቀር፣ ለዜጎች ሠላምና ደህነት ምንግዴው ትሕነግ ዐማራና አፋር ክልሎችን በመውረር፣ ንፁሃንን ዒላማ ያደርጉ ተከታታይ ጭፍጨፋዎች ፈጽሟል፡፡
የሕግ ማስከበር ዘመቻው ሲጀመር በማይካድራ ከ1600 በላይ ዐማራዎችን በማንነታቸው መጨፍጨፉ ሳይዘነጋ፤ ባለፉት ሦስት ወራት፡- በአፋር ጋሊኮማ፣ በዐማራ አጋምሳ፣ ንፋስ መውጫ፣ ጭና፣ ቦዛ፣ ራያ ቆቦ… አካባቢዎች ብቻ በድምሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁሃንን ጨፍጭፏል፡፡ ከአንድ ሚሊዮን የሚሻገሩ ዐማራዎችን ከቀያቸው አፈናቅሏል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 256 ሺሕ ያህሉ ከአምስት ዐመት በታች ያሉ ህፃናት ሲሆኑ፤ ከ76 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ነፍሰ-ጡርና የሚያጠቡ እናቶች ናቸው፡፡
ቁሳዊ ውድመቶችን ስንመለከት ደግሞ 14 ሆስፒታሎች፣ 153 ጤና ጣቢያዎችና 642 ጤና ኬላዎች፤ እንዲሁም 2635 ትምህርት ቤቶች እና 16 ሙያና ቴክኒክ ኮሌጆችን ዘርፏል፡፡ 268 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፡፡ 19 ሺሕ የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ሙሉጭ ተደርገዋል፡፡ በጥቅሉ ቁልፍ የማኀበራዊ ልማት ተቋማት ወድመዋል ማለት ይቻላል፡፡
ደረቁ ሃቅ ይህ ቢሆንም፤ የአሜሪካ መንግሥት አቋም በኢትዮጵያ ያለውን እውነታ ያላገናዘበ መሆኑ ያሳዝናል፡፡ ከታሪካዊው ግንኙነት በዘለለ፤ ዓለም ከደረሰበት የሉዓላዊነት ጸንሰ-ሀሳብ ጋር በሚጋጭ መልኩ፣ አሸባሪና ወራሪ ቡድንን፣ ከኢትዮጵያን መንግሥት እኩል መመልከቱ በሰባራ ሚዛን የመለካት ያህል እውነታውን ያጎድለዋል፡፡ ስለዚህም የአሜሪካ መንግሥት፣ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ የሚያይበት መንገድ፣ በተለይ የመረጃ ምንጮቹን እንዲፈትሽ እንደ አንድ አገር ወዳድ ዜጋ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
አሜሪካ፣ ከቬተናም እስከ አፍጋኒስታን የሠራችውን ስህተት፣ ኢትዮጵያ ላይ እንድትደግመው አንፈቅድላትም፡፡ የተለወጠው የዓለም ሥርዐትም ይህን አንድታደርግ አይመችም፡፡ ከምንም በላይ ግን፣ የኢትዮጵያ ተስፋዋ የዜጎቿ የሀሳብና የተግባር አንድነት ነው፡፡
እንደ አገር ሕግ የማስከበር ተልዕኳችን የሀገረ-መንግሥቱን ህልውና ለማስቀጠል ብቸኛው አማራጭ በመሆኑ፣ በተልዕኳችን እንፀናለን፡፡ ዋጋ የማይከፈልበት ሉዓላዊነት እንደሌለ ከአያት፣ ቅድመ አያቶቻችን ተጋድሎ የተማርነው የታሪክ ውርሳችንም ተጨማሪ ዐቅም ይሆነናል፡፡
በጥቅሉ፣ ኢትዮጵያ ተገዳ የገባችበት ሕግ የማስከበር ተልዕኮ፣ በውጭ ኃይሎች ጫና የተራዘመ ቢመስልም በአጠረ ጊዜ መፍትኄ ያገኛል፡፡ በሉዓላዊ መንግሥቷና በሕዝቧ ሙሉ ዐቅም የውስጥ ችግሯንም ትፈታለች፡፡ በኢትዮጵያ ፀሐይ ላይ ያጠላው ደመናም ይገፈፋል፡፡
ይህም ሁኖ፣ ጽሑፌን በአንድ መጠየቅ መቋጨት ወድጃለሁ፡- ለመሆኑ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ተቃቅራ፣ ከአሸባሪው ትሕነግ ጋር በመወገኗ የምታገኘው ጥቅም ምንድነው? Banana republic?