Connect with us

አቡዬ ጣዲቁ…..

ሄኖክ ስዩም

ባህልና ታሪክ

አቡዬ ጣዲቁ…..

አቡዬ ጣዲቁ…..

(ሄኖክ ስዩም ~ድሬቲዩብ)
ዛሬ ልዩ ቀን ነው፡፡ የአድአ ገበሬዎች ናፍቀውት ቀኑ ደርሷል፡፡ የዝቋላ አምባ በዝማሬ የሚደምቅበት፣ የምድረ ከብድ ምድር ከእንሰቱ ቁጥር ሰው የሚበዛበት፡፡ የአቡዬ ጣዲቁ በዓለ ንግሥ፤ የሚናፈቅ ቀን ነው፡፡ ከልጀነቴ የተቆራኘ፡፡ የወጨጫን ሞገስ እያየን፣ የሜታ ገበሬ ደግ ልብ እየተቀበለን አቡዬን እናነግሳለን፡፡

እንዲህ ባለው ወቅት ይሄን ጊዜ ወደ ሜታ አቦ ጉዞ ላይ ነን፡፡ አዲስ አበባ በሁሉም አቅጣጫዎች ምዕመኖቿ አቡዬን ሊሳለሙ ይሄዳሉ፡፡ ወደ መካኒሳ አቦ፣ ወደ ሳሪስ አቦ፣ ወደ ፈረንሳይ አቦ፤ ደግሞ ዝቋላን አስባለሁ፡፡ ዛሬ የደከሙ እናቶች የበረታውን ዳገት ድል ያደርጉታል፡፡ ሦስት ሺህ ሜትር ሊጠጋ ጥቂት የቀረው ተራራ በብርታታቸው ይሸነፋል፡፡ ዛሬ እዚያ አምባ አናት ለመውጣት የማይጓጓ የለም፡፡ አቡዬ ጣዲቁን ለማንገስ፤
ደግሞ የአዱላላ ገበሬዎች ደግነት ያደምቀዋል፡፡

ምርት ገና ባልተበሰበበት በዚህ ወቅት ጎተራቸው ሙሉ ባይሆን እንኳን የአቡዬ እንግዶች ሆድ ባዶ እንዳይሆን ዘክረው እንግዳ የሚቀበሉ ደጋግ፤
የአድአ ገበሬ ደግ ልብ ልብ ይሞላል፡፡ ቡርቃዎች ሰው ናፈቀው ሰው የሚቀበሉበት ቀን ነው፡፡ የሀገሬ ሰው ቸርነት ታላቁን ገዳም ከቦታል፡፡ ከአምስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እንዲህ ባለ ክብር የኖረ ነው፡፡ ተፈጥሮን ከመንፈሳዊ ጸጋ ጋር አቆራኝቶ የጠበቀ፡፡ ጠንካራ ገዳማዊ ህይወትን ከሀገር ታሪክና ቅርስ ጋር ያሻገረ፡፡ ዝቋላ፡፡

ደግሞ እዚያ ምድረ ከብድ አለ፡፡ የጉራጌ መንደር የሚደምቅበት፡፡ ከእንሰቱ ቁጥር በላይ የእንግዳው ሰው መጠን በዝቶ በዝማሬ ሀገር የሚያዳርስበት፡፡
ዛሬ ስል ብዙ ቦታዎች አስብኩ፡፡ እንዲህ ባለው ቀን ድምቀታቸው ሌላ ነው፡፡ እናት ዓለም ጎንደር ልቤ ሄደ፡፡ ፊት አቦን አስባሁ፡፡ የዐፄ ፋሲል ትክል ሲሆን ከጎንደር ዓቃቤ ታቦታት አንዱ ነው፡፡

ጎንደር ታላቁ ንጉሥ ሲቆረቁሯት አውሬው አስቸገረ፡፡ ዐፄ ፋሲል አቦ ቤተ ክርስቲያንን ያሰሩ ዘንድ የንጉሡ የቅርብ ሰው አባ ተስፋ ሐዋርያት መከሩ፡፡ ፊት አቦ ተተከለ፡፡ በ1630 ዓ.ም. እስከሁን ፊት ሆኖ ፊት አቦ እየተጠራ ይገኛል፡፡
ደግሞ አንኮበር የወረደ ደዋይ ሲደርስ 250 ዓመት እድሜን ያስቆጠረውን ይገም አቦ ዛሬ ደምቆ ያገኘዋል፡፡ ሽታን አቦ ሲባል ከሰማችሁ እሱ አብርሃ ወ አጽብሃ የተከሉት ነው፡፡ ደቡብ ጎንደር ላይ ጋይንት፡፡

ደቡብ ጎንደር ብዙዎቹን የአቡዬ ገዳማት አይቻቸዋለሁ፡፡ የዐጼ ሰይፈ አርእድ ትክሉንና የሙጃውን እንኑም አቦ እስከዚያ ተአምረኛ ጸበሉ ወርጃለሁ፡፡ የእስቴን ድንቅ የዋሻ ውስጥ ደብር ዙምባራ አቦን አይቻለሁ፡፡ ዛሬ ደምቀው ይነግሳሉ፡፡ ዛሬ ድባባቸው ልዩ ነው፡፡
አቡዬ ጣዲቁ……..
እንኳን አደረሳችሁ፡፡

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top