የም ይችልበታል፤ መሬት ላይ በላቡ ከአፈር ለመታረቅ እንዲህ ጦማር ጽፏል
(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በየም ቆይታዬ የሞች መሬት ላይ ሲጽፉ አየሁ ብሎ ድንቅ የአፈር ጥበቃ አዲስ ባህልና የኮረብታዎችን ውብ ገጽ አንድም አፈር ማዳን አንድም ዐይንን ማሳረፊያ መፍጠር ሲል እንዲህ ይተርክልናል፡፡)
(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)
የም በመስከረም ሄድኩ፡፡ መቼም የየም ምድር በመስከረም ልዩ ነው፡፡ ከራስ ዓይን ያጣላል፡፡ ራስን እንደ ውሸታም ያሳማል፡፡ የማየው የሚታየውን ነው፡፡ የም ውብ ምድር፡፡ የየም ምድር የቦጊኛ ዜማ ማድመጥ ሲጀምር የደረስኩ እንግዳ ሆኛለሁ፡፡
ያለሁት ወደ ፎፋ ነው፡፡ ፎፋ ቀደምት የየሞች መዲና ናት፡፡ እግር ጥላችሁ ከመጣችሁ አንጋሪን አሳዩን በሏቸው፡፡ ቀደምቱን ቤተ መንግሥት፤
የየም ታሪክ ሩቅ ደራሽ ነው፡፡ ቀደምት ከሚባሉ የሀገሬ የታሪክ ሰበዞች የም ብዙውን ይጋራል፡፡ የዞፍካር ትክል ድንጋዮች ይሄንን ቆመው ይመሰክራሉ፡፡ ፎፋ መድኃኒዓለም ብዙ ታሪክ አለው፡፡
የየም ታሪክ ትናንት ላይ አልቆመም፣ ዛሬም ድንቅ ነገር ያደርጋል፡፡ በየም በየዓመቱ መስከረም ከመስቀል በኋላ የሄቦ በዓል ይከበራል፡፡ ከዚያ ደግሞ የቻሎ ሥርዓት፤
ቻሎ ሰበር ሰሚ ችሎትም ነው፡፡ ዓመቱን የካደው ምን ቢከርም መስከረምን አይሻገርም፡፡ እዚህ ይመጣል፡፡ አሁን ያለሁበት የቻሎ ሥርዓት የሚከናወንበት ሥፍራ ነው፡፡ ከዚያ ሰበር ሰሚው ይሰማል፡፡
ጭፈራው ሌላ ነው፡፡ ዛሬ በዕለቱ አይደለም የመጣሁት ግን ያ የሆታ ድምጽ ምስሉ ከነድምጹ ውስጤ ቀርቶ ይሰማኛል፡፡
የም ይችልበታል፡፡ ተራሮቹን ይታደጋል፡፡ የዓመት መድሃኒቱን ከቦር አናት ይለቅማል፡፡ የአደረ ችሎቱን በቻሎ ይቋጫል፡፡ ደግሞ ተራራን እንደ ሰሌዳ እንዲህ አድርጎ ድንቅ ነገር ይጽፍበታል፡፡
የስልጣኔ መገለጫ አፈርን ማዳን ነው፡፡ ከዚያ ከራስ ምድር ከርስ በራስ ውሃ ጥምን መቁረጥ፤ ወንዝን ኩልል ማድረግ መቻል ትልቅ ድል እንደሆነ አምናለሁ፡፡ አፈር እየሸኙ ሀገርን መጠበቅ የለም፡፡ ሀገር አፈሩ ነው፡፡ ሰው በአፈሩ የሚኖር በአፈሩ የሚቀር ነው፡፡
የየም ተራሮች አሁን ተአምር እየተሰራባቸው ነው፡፡ እንደ ኮንሶ ባህላዊ መልከአ ምድሮች በእርከን አጊጠዋል፡፡ የም ኮረብታዎቹን የኮረዳ ራስ አስመስሏቸዋል፡፡ ቁንዳላ የተሰሩት የመሰሉ ተራሮች በአፈርና ውሃ ጥበቃ አጊጠዋል፡፡
የም አፈሩን ከታደገ ግቤን ከደለል ያድነዋል፡፡ ግቤን ከደለል ካዳነ መንደሩን ብቻ ሳይሆን ሀገሩን ታደገ ማለት ነው፡፡
ያን ሰርቶ ዓይኔ ድንቅ ነገር አየ፡፡ ደግሞም መስህብ ሆነ፡፡ የዚህ ትውልድ ስራና ምስክር ሆኖ የሚታይ ውብ ምስል፡፡
ብዙዎቹ ኮረብታማ ቦታዎች ውብ ገጽ ይታይባቸዋል፡፡ የውበታቸው ምስጢር የእርከኑ ገጽና መስመር የፈጠረው ትዕይንት ነው፡፡ ይሄንን አለማድነቅ አይቻልም፡፡ ይሄ አሁን አዲሱ ትውልድ ሰራው ተብሎ የሚጎበኝ ሀብት ሆኗል፡፡
እንዴት እንደሚያምር መግለጽ ያቅተኛል፡፡ የሞች እንዲህ ኮረብታዎች ላይ ከአፈር ለመታረቅ ለአፈር ጦማር ጽፈው አነበብኩ፡፡ ይሄ ትውልድ ሊያኖረውን የሚገባ ህያው ሀውልት አቁመዋል፡፡ የቆመው ድንቅ የተፈጥሮ ትዕይንት ደግሞ የደረሰ የሚመለከተው፣ ያረሰ የሚበላበት፣ ትውልድ ሀብቱን ለትውልድ የሚያሻግርበት ነው፡፡