የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን የሸለማችሁልን የሀገር ባለውለታዎችን ነውና እናመሰግናለን!
(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ትናንት በሸራተን አዲስ የተካሄደውና በባሌ ተራሮች ቃጠሎ ለተፈጥሮ ፍቅር መስዋዕት የሆነውን ቢኒያም አድማሱ ጨምሮ በርካቶች የተሸለሙበትን የቱሪዝም አዋርድ የሀገር ባለውለታዎችን የሸለመ ነው ይለናል፡፡)
(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)
እጅ ነስተናል፡፡ እጅ የሚያስነሳ ሥራ ሰርታችኋል፡፡ የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን እንደ ሀገር አመታዊ የቱሪዝም ሽልማት /አዋርድ/ የጀመረ የመጀመሪያው ተቋም ነው፡፡ ትናንት ምሽት በሸራተን አዲስ ሆቴል የመጀመሪውን አድርጓል፡፡ እርግጥ ነው ከቀናት በፊት በዓለም ቱሪዝም ቀን በዓል ላይ ሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪ ባለውለታዎች ያላቸውን እውቅና ሰጥቷል፡፡
ይሄኛው ግን ሽልማት በሚል መርህ በራሱ ደንብና ሥርዓት ተሰርቶ በየዓመቱ ሊከወን የተዘጋጀ የመጀመሪያ የቱሪዝም ዘርፍ እውቅና ነው፡፡
ምን እንደምል አላውቅም፤ ደስታዬ ወደር የለውም፡፡ ቢኒያም አድማሱን የህይወት ዘመን የቱሪዝም ባለውለታ ብላችሁ ሸለማችሁት፤ ሽልማታችሁ የመንዝ ጓሷን ገበሬዎች ልብ ያሞቃል፡፡ ሽልማታችሁ ከስሜን ጫፍ እስከ አርሲ ገጠሮች የሚገባ ነው፡፡
ቢኒያም ለተፈጥሮ ፍቅር እሳት የበላው እሳት የሆነ የአካባቢ ተቆርቋሪ ነው፡፡ የዓለም ዘናጭ ሀገራት ሳያጓጉት ከሚኮበልሉ ጓዶቹ እየተለየ እናት ሀገሬ ባላት ምድር ለሀገሩ የተፈጥሮ ቅርስ የወደቀ፤ ሀገር ሸልማችኋል፡፡ ሀገር ያመሰግናችኋል፡፡
የሰንቀሌ ቆርኪዎች መጠለያ ትምክህታችን ነበር፡፡ በዓለም የተፈጥሮ ጥበቃ ታሪክ ለዱር እንስሳቱ መቆርቆር እንጂ የዱር እንስሳቱን ከሰው እኩል በማድረግ መታደግ ሌላ ጥበብ ነው፡፡ ሀምቤቶ ይሄንን አድርጎታል፡፡ አዳ ሮባ የገዳ ሥርዓት ተአምር ሰርቷል፡፡ ዓለም ብርቅዬ ዝርያ ከጥፋት ሲድን አይቷል፡፡
ሀገር እንዲህ ላለው ተግባር እውቅና ሰጥታም ሸልማም አታውቅም፤ የሚገርመው አፍሪቃ ሸልማለች፤ ቀጥሎ ኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን እናመሰግናለን፡፡
አዚዝ አህመድ ስፍራው የት ነው? በሁሉም የሀገር ቀጠና፣ በሁሉም የሀገር ተፈጥሮ ቅርስ ዱር አድሮ የዱር ምስል ያስቀረ፣ የሀገር መልክ እንዲህ ነው ወይ እስኪያስብል ራሱን ከሞት ጋር አፋጥጦ ድንቅ የሰራ እንደ እኔ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የዱር እንስሳት ፎቶ ግራፈር ነው፡፡
አዚዝን መሸለም ባሌ አልያም አዋሽን ብቻ መሸለም አይደለም፤ ስለ ጨበራ ጩርጩራ ውብ ምስሎች እውቅና መስጠት ነው፤ ስለ ስሜን ድንቅ ገጾች ማመስገን ነው፣ ስለ ሃላይደጌ እጅ መንሳት ነው፤ ለዚህ ነው ኮሚሽኑን እኔም እጅ የምነሳው፡፡
አዩባ አህመድ የመጣውን አስጎብኚ ብቻ አይደለም፤ ያልመጣውን የሚጠራ ድንቅ የቱሪዝም ሰው ነው፡፡ የተፈጥሮ ቱሪዝም ረሃብን የሚያጭር ሰባኪ፤ ከሀገሬ አካባቢ አስጎብኚዎች እንደ እሱ ማኅበራዊ ሚዲያውን ለሀገር መልካም ምስል የተጠቀመ አላየሁም፡፡ ምርጥ የአካባቢ አስጎብኚ የሚለውን ሽልማት በመውሰዱ ኮርቻለሁ፡፡
ስለ ታላቋ የአደ ሲንቄ አንባሳደርና ስለ ባህል እናት አብዮተኛዋም ምስጋናችን የላቀ ነው ብቻ እውነት ለመናገር እከሌ ከእከሌ የለውም፤ በክልሉ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ላይ ሚና ነበረው ብላችሁ የሸለማችሁት ሁሉ በእናት ሀገር ኢትዮጵያ ቱሪዝም ላይም ድርሻ ያለው ባለውለታ ነውና ምስጋናችን ከልብ ነው፤ ከልብ፤