ገበሬን ጊዜ፣ ስንቅና ትጥቅ አዋጣ በምንልበት ወቅት የኢቲቪ የመኪና ግዢ ዜና እውነት ከሆነ ያሳዝናል!
(ስናፍቅሽ አዲስ ~ድሬቲዩብ)
ሰሞኑን ለሀገር መከላከያ ድጋፍን አስመልክቶ የኢቲቪ ሰራተኞች ያላአግባብ ደመወዛችን እንዲቆረጥ ተወስኗል ሲሉ ለሙግት ያቀረቡትን የመኪና ግዢ ጉዳይ ሰማሁት፡፡ እውነት ለመናገር ለመከላከያ ድጋፍ ማድረግ እንደ ግለሰብ የሚከፈል የአጋርነት መስዋዕትነት ቢሆንም ቅሉ ዜናውን በሌላ በኩል ግን መፈተሹ ደግ ይመስለኛል፡፡
በዚህ ከባድ የፈተና ወቅት ብዙ ችግሮች ተጋርጠውብናል፡፡ ጉዳት መግታት ብንችል እንኳን በሺህ የሚቆጠር ትምህርት ቤትና ሆስፒታል የፈረሰብን ህዝቦችን ነን፡፡ ሚሊዮኖች ሜዳ ላይ ወድቀዋል፡፡ ቤታቸው ፈርሶ ጦሙን ያደረውን መሬትም የተደበቀ አይደለም፡፡
መንግስት ህዝቡን ተሳስበን እንለፈው ብሎ ስንቅ ሳይቀር ከደጀኑ እየጠየቀ ነው፡፡ ገበሬው ሞሰብ ተሸክሞ መከላከያናንና ህዝባዊ ሰራዊቱን አለሁ ይላል፡፡ ያለውን አንግቶ ይዋጋል፡፡ በዚህ ወቅት በሚሊዮን ብሮች አውጥቶ ቅንጡ መኪኖች መግዛት ያስተዛዝባል፡፡
መንግስት እንዲህ ባለው ወቅትም አስፈላጊ እንኳን ቢሆኑ አላስፈላጊ ጊዜ በሚል መርህ ያልተገቡ ግዢዎችን መቆጣጠር አለበት፡፡ ይህ ማሳያ ምናልባትም የግል አልያም ኮርፖሬትነት ስማቸው በሆነና ግዢ ኤጀንሲ በማያጣድፋቸው ወይም ደግሞ ኦዲተር የዕለት ራስ ምታታቸው ባልሆኑ ተቋማት የሚደረጉ ግብይቶችን ከመታዘብ ያለፈ ክትትል ማድረግ አለበት፡፡
ኢቲቪን የሚያህል ተቋም የሥራ ሃላፊዎች ቅንጡ መኪና ማሽከርከራቸው በራሱ ችግር አይደለም፡፡ ብቃት ያለውን አመራር ለማቆየትና ለመያዝም ቢሆን ምቹ ነገር መፍጠሩ አይኮነንም ግን ይሄ ወያኔን ለመጣል በሚደረግ የሞት ሽረት ትግል ወቅት የወያኔን ስራ የሚመስል ተግባር መፈጸም መልካም አይመስለኝም፡፡
የሠራተኞቹ ጥያቄ ይሄንን ያህል ብር ወጪ ሆኖ በዚህ ከባድ ጊዜ ቅንጡ መኪና ከሚገዛ ያ ብር ወደ መካላከያ ድጋፍ ቢሄድ ኖር የሚል ቅሬታ ነው፡፡ ጉዳዩን ከወቅቱ አንጻር ከመዘነው ግን እውነትም ከባድ ትዝብት ውስጥ ይጥላል፡፡
ተቋሙን እናውቀዋለን፤ ለሰራተኞቹ እንኳን ዘመኑን የሚመጥን ውሎ አበል የሚከፍል አይደለም፡፡ ያም ሲያልፍ እንዲህ ባለው ሀገራዊ የክተት ዘመቻ ወቅት በጀት የሚፈልግ ጠንካራ የዘገባ ስራ የሚያሻው ተቋም ነው፡፡ ተርፎት ነው እንዳንል ያንን የሚያሳይ ብዙ ትርፍ አፋሽነቱን በራሱ ዜና እወጃ አልነገረንም፡፡ ይሄ ሁሉ በሆነበት ይሄንን ቅሬታ መስማት ትንሽ ጥያቄ ያጭራል፡፡
ተቋማት ከመደበኛ ስራቸውና ከአስፈላጊው እንቅስቃሴያቸው በዘለለ ከርሞ መሆን የሚችልን ግዢ በይደር ቢያቆዩት መልካም ነው፡፡ አሁን እንደ ሀገር ጦርነቱ በጀታችንን ሳይቀር የመታ፣ ሁለንተናዊ ኪሳራ እንደሆነ የአደባባይ ሀቅ ሆኖ ሳለ እንደ አዘቦት አስረሽ ምቺው የምንልበት ሁኔታ መፈጠር የለበትም፡፡
የኢቲቪ ሰራተኞች ቅሬታ መንግስት ሌሎች ጉዳዮችንም በልዩ ሁኔታ ተከታትሎ ማጤን እንዲገባው እድል ይፈጥራል፡፡ ወቅቱን ግምት ውስጥ ያልከተተ የቱም ጤነኛ ተግባር እንደ በሽታ ይቆጠራል፡፡ አሁን ከባድ ፈተና ውስጥ ነን፤ በዚህ ውስጥ ሆነን ነገ የሚደርሰው ዛሬ ካልሆነ የሚል ሩጫ ውስጥ ከገባን ዛሬ ያደረግነው ነገር ሁሉ ወደ ነገ አያሻግረንምና ይታሰብበት፡፡