ለኢትዮጵያውያን ያለውን ዛቻ ጨርሶ ለግብጻውያን መፎከር የጀመረው ኣይተ ጌታቸው ረዳ
(አሳዬ ደርቤ~ ድሬቲዩብ)
ጌታቸው ረዳን ሳስብ Crime & Punishment በሚለው የደስቶዮቭስኪ መጽሐፍ ላይ ያለው ራስኮልኒኮቭ የሚባል ገጸ ባሕሪ ትዝ ይለኛል፡፡ ይሄውም ካራክተር ‹‹ወንጀል የመፈጸም መብት አላቸው›› ብሎ ከሚያስባቸው ‹‹ልዩ ሰዎች›› ተርታ እራሱን ይመድብና አራጣ አበዳሪዋን አሮጊት በመጥረቢያ ይገድላታል፡፡
ይሄንንም አሰቃቂ ወንጀል ፈጽሞ ሊወጣ ሲል የአሮጊቷ እኅት (ሊሳቬታ) እንዳየችው ስለተረዳ እሷንም ይገድላትና በኅሊና ፍርድ መሰቃየት ይጀምራል፡፡ እጁን ለፖሊስ ሰጥቶ እስኪገላገል ድረስ የፈጸመው ወንጀል ከአሮጊቷ ባለፈ በውስጡ ያለውን ምርጥ ማንነት እንደገደለበት እያስታወሰ በጸጸት ይታመሳል፡፡
በስህተት የተሞላ ተራ ሰው ሆኖ ሳለ ‹‹ልዩ ሰው ነኝ›› ብሎ የሚያምነው ‹‹ጌታቸው ረዳም›› ያጋጠመው የማንነት ቀውስ ከራስኮልኒኮቭ ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ ራስኮልኒኮቭ በአሮጊቷ ላይ የፈጸመው ወንጀል ለሌላ ወንጀል እንዳነሳሳው ሁሉ ጌቾም በቅሌት ላይ ቅሌት፣ በወንጀል ላይ ወንጀል የሚደራርብ ሰው ሆኗል፡፡
ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ትከሻው ላይ የተተከለ ጭንቅላቱ በተለያዩ ጊዜያት የተናገራቸውን አሳፋሪ ንግግሮች እያስታወሰ፣ በድርጅቱና በክልሉ ላይ ባደረሰው ጥፋት እየከሰሰ፣ ባንድ ወቅት ከአፉ የወጡትን ባዶ ፕሮፖጋንዳዎች ወደ አሁን እየመለሰ፣ ከሞት ጋር የሚጋፈጥበት ጊዜ መድረሱን የሚያረዱ አስፈሪ ትዕይንቶችን እየጸነሰ የሚረብሸው መሆኑ ነው፡፡
ያን ጊዜ ታዲያ ጌቾ በፌስቡክና በትዊተር አካውንቱ ላይ ከጭንቅላቱ ጥያቄዎችና ወቀሳዎች በተቃራኒ የሆኑ መልሶችን ይዞ ከተፍ ይላል፡፡ ማለትም፡-
‹‹ለድሮን ጥቃት እንዳትዳረግ ከቤት አትውጣ›› ወይም ደግሞ ‹‹ጃንጥላ ይዘህ ውጣ›› የሚል አስፈሪ ምክር አእምሮው ሲሰጠው ‹‹ድሮኖች እኮ ተራ አሻንጉሊቶች ናቸው›› የሚል ፖስት በመለጠፍ እራሱን ያጽናናዋል፡፡
‹‹ያለ ምንም አደጋ በአንድ ሳምንት ውስጥ አራት ኪሎ ትገባላችሁ ወይም ደግሞ የጅቡቲን መስመር ትቆጣጠራላችሁ ብለህ ወደ አፋር ያስገባኻቸውን ሕጻናት በአጭር አስቀራኻቸው አይደል?›› የሚል ወቀሳ ሲያቀርብለት ‹‹ከአፋር የወጣነው እኮ መፈጸም ያለብንን ተግባር አከናውነን ነው›› በሚል ፖስት ረግፎ የቀረውን ሠራዊት ከሞት አስነስቶ በሌላ ግንባር ያሰማራዋል፡፡
‹‹ከሞት ማምለጥ ከቻልክ ‘ቃሊቲን ተቆጣጥረነዋል’ እያልክ ወደ እስር ቤት የምትወርድበት ቀን እየተቃረበ ነው›› በማለት ልቡ ሲያስፈራራው ‹‹የአራት ኪሎው መንግሥት በቁጥጥር ስር የሚውልበት ቀን መቃረቡን የሚገልጽ ጽሑፍ ግድግዳው ላይ በመለጠፍ እራሱን ይሸነግለዋል፡፡
‹‹ሒሳብ እናወራርዳለን ወይንም ደግሞ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እንከ እንጦሮጦስ ድረስ እንወርዳለን” የሚል ፉከራህ ያመጣውን ውጤት አየኸው? በሚል ጥያቄ መከላከያ ሠራዊት ለመሆን አስቦ የሚመዘገበውን ቁጥር ስፍር የለሽ ወጣት ሲያሳየው… ከግብጽ ሚዲያ ላይ ቀርቦ ‹‹ኢትዮጵያን እናፈርሳታለን ማለት እናፈርሳታለን ነው›› እያለ ብስጭቱን ይገልጻል፡፡
በንዴትና በብስጭት ውስጥ ሆኖ የተናገራቸውን የወረዱ ንግግሮች እያስታወሰ ‹‹ኢትዮጵያ የተባለች አገር ሕያው ሆና ከቀጠለች አመራር ይቅርና ተራ ዜጋ ሆነህ መኖር የምትችለው እንዴት ነው?›› በሚል ጥያቄ ከጥይት ቢተርፍ እንኳን በእፍረት እንደሚሞት ሲነግረው ‹‹በኢትዮጵያ መቃብር ላይ ሀገረ ትግራይን እንመሠርታለን›› በሚል ጩኸት የጭንቅላቱን እውነት ያድበሰብሰዋል፡፡
ስለሆነም ‹‹ኢትዮጵያን እናፈርሳታለን›› የሚለው የጌቾ ፉከራ እራሱን እንጂ አገሩን ከመጥላት የሚመነጭ አይደለም፡፡ ‹‹ትግራይን እንገነጥላለን›› የሚል ዲስኩሩም ከእራስ ወዳድነት ጓዳ እንጂ ትግራይን ከመውደድ የሚቀዳ አይደለም፡፡
እንዳጠቃላይ ጌቾ ባሁኑ ሰዓት ያበት ሁኔታ ሲገመገም፡-
ከስሌት ጋር ፍቺ ፈጽሞ በስሜት ሞገድ የሚዳክር፣ ከስክነትና ብስለት ተለያይቶ በንዴት የሚፎክር፣ ከእውነት ጋር ተቀያይሞ በውሸት ፕሮፖጋንዳ የሚተዳደር፣ ሌላውን ቀርቶ እራሱን ሊያሳምን የማይችል ባዶ ቃላት የሚቀባጥር፣ ‹‹የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም›› በሚል አስተሳሰብ ማጥ ለማጥ የሚዳክር፣ ፍርሐትና ስጋት ሲሰማው ጀግንነቱንና መረጋጋቱን ለማሳየት የሚጥር፣ በቅሌት ሐዲድ ላይ የሚሽከርከር፣ ምድር ላይ ሽንፈትና ክስረት ያስተናገደ ቀን ሳይበር ላይ ድሉን የሚዘክር፣ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚሰነዝረውን ዛቻ ጨርሶ ለግብጻውያን የሚፎክር… ከንቱ ሰው ሆኗል፡፡
እናም ጌቾ ግጥም የሚወድ ሰው እንደመሆኑ መጠን የገጣሚውን ሥም ማስታወስ ባንችልም የሚከተለውን ስንኝ ብንጋብዘው ያለበትን ሁኔታ የምትገልጽለት ይመስለናል፡፡
ፉከራው የት አለ?
እልልታው የት አለ? ምነው ዝም አላችሁ?
እኔን ያክል ጠላት ፥ ገድዬ እያያችሁ››
……አበቃሁ!!….