Connect with us

ሎካ አባያ ብሔራዊ ፓርክ አስገራሚው ሀብታችን፡፡ 

ሎካ አባያ ብሔራዊ ፓርክ አስገራሚው ሀብታችን፡፡
ሄኖክ ስዩም

ባህልና ታሪክ

ሎካ አባያ ብሔራዊ ፓርክ አስገራሚው ሀብታችን፡፡ 

ሎካ አባያ ብሔራዊ ፓርክ አስገራሚው ሀብታችን፡፡ 

(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኘውን ሎካ አባያ ብሔራዊ ፓርክ ፍለጋ ተጉዟል፡፡ በሲዳማ ክልል የሚገኘው ይህ ፓርክ አስገራሚ የተፈጥሮ ጸጋ አለው ሲል የምሽቱን ድባብ እስከ ውሎው እንዲህ ያስቃኘናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡)

(ሄኖክ ስዩም -ድሬ ቲዩብ)

ነጋ፡፡ ምሽቱ ሸጋ ነበር፡፡ የሎካ አባያ ስካውቶች ጥሩ ጊዜ እንዳሳልፍ አድርገውኛል፡፡ ሲዳማ በኢትዮጵያ ጉዳይ ምን ድረስ ልቡ ስስ እንደሆነ ያየሁበት ነው፡፡ ወቅታዊው ሁኔታ ጭምር የዜማ ምክንያት ሆኖ ኢትዮጵያ ሻሎ ስንል አነጋን፡፡

ይሄ አርባ ሁለት ግዙፍ አጥቢ እንስሳት የሚኖሩበት ፓርክ ነው፡፡ በዋናነት የትም አጋዘን ይታያል፡፡ ሰስ ደንብራ ስትሮጥ መተላለፍ ብርቅ አይደለም፡፡ ደግሞ የአባያ ሐይቅ ዳር መዘርጋቱ የወፍ ሀብቱ የሚደንቅ ብሔራዊ ፓርክ እንዲሆን እድል ፈጥሮለታል፡፡ 115 የወፍ ዝርያዎች መመዝገባቸውን ነገሩኝ፡፡

የብሔራዊ ፓርኩን ክፍል ዞር ዞር ብለን ለመመልከት በጠዋት ጉዞ ጀምረናል፡፡ አንዳንዱ ቦታ ኮረብታው ውብ ቀለም ይዞ ያፈዛል፡፡ ደግሞ የወንዝ ዳር መሳይ ጥቅጥቅ ደን አጠገብም እንደርሳለን፡፡ ሳራማው ሜዳም ተዘርግቶ ይታየናል፡፡ ዓይነተ ብዙ ነው፡፡

ሁለተኛውን ቀን ምሽት ለማሳለፍ ለአዳር የመረጥነው ሥፍራ አባያ ሐይቅ ዳርቻን ነው፡፡ አባያ እዚህ ሌላ ውበት ፈጥሯል፡፡ ሀገር ይሄንን በአግባቡ ካለማችው እድሉ እድለኛ ያደርገናል፡፡ ሎካ አባያን ጎብኝቶ፣ በጌዴኦ ባህላዊ መልከዓ ምድር ቆይታ አድርጎ ወደ ነጭ ሳር መጓዝ መቻል መታደል ነው፡፡

ሦስት ክልል ከሚያገናኘው የአባያ ሐይቅ ገና አልተጠቀምንም፡፡ ለውሃ ትራንስፖርት ምቹ ሐይቅ ነው፡፡ የጎብኚን ብቻ ሳይሆን የሀገሬውን ድካምና ሸከም ማቅለል የሚቻልባቸው ወደቦች እውን ከሆኑበት ያኔ የሎካ አባያም ተስፋ ይለመልማል፡፡

የኃይሌ ሪዞርት ቤተሰብ ነኝ፡፡ የሎካ አባያ ጥቁር እንግዳ እሆን ዘንድ ከጎኔ ቆመዋል፡፡ አሁን ካለሁበት ፓርክ ሀዋሳ 60 ኪሎ ሜትር ትርቃለች፡፡ የመዝናኛዋን ከተማ ብሎ እዚህ የደረሰ ይሄንን መጥቶ ቢጎበኝ ብዙ ያተርፋል፡፡ ትርፉን ከመስማት ማየቱ በብዙ ይበልጣል፡፡

ከሎክ አባያ እስከ ነጭ ሳር በውሃ ላይ መጓዝ ይቻላል፡፡ አባያ ሐይቅ እዚህ ብቻ ሳይሆን የፓርክ አካል የሆነው የነጭ ሳርም ክፍል ነው፡፡ ሁለት ፓርኮች የሚጋሩት ግዙፍ ሐይቅ ከኦሮሚያ እስከ ጌዴኦ ከሲዳማ እስከ ወላይታ ከጋሞ እስከ ጋርዱላ የሚገሰግስ አንዳች የውሃ ላይ ትራንስፖርት አለመኖሩ ያስቆጫል፡፡ ከዳር ዳር 60 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውና 1162 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው አባያ የበርካታ ደሴቶች መገኛም ነው፡፡

በአባያ ሐይቅ ዳርቻ ደስ የሚሉ ፍልውሃዎች አሉ፡፡ ድካማችንን ፈወስን፤ አባያን እያየን ለማደር ዳርቻው ላይ ማረፊያችንን መሰረትን፤ ብዙ አልመሸም ቁጥርም ስፍርም የሌለው ጅም ወደ አለንበት ቀረበ፡፡ አንዱን በዚህ ሂድ ስንል ሌላው በዚህ ሲመጣ ትዕይንት ነበር፡፡

ከወዲያ የጉማሬው ድምጽ ይሰማል፡፡ አባያን ሲያተራምሰው እያየንም ነው፡፡ ደግሞ ዳርቻዎቹ የአዞ ማረፊያዎች ናቸው፡፡ ሎካን ታድሏል ያስባለው ይሄ ነው፡፡ የብስም ባህርም ውስጥ የሚኖር እንስሳ የሚታይበት መሆኑ፤

ሎካ የታደለ ፓርክ ነው፡፡ ብዙ እድሎች ከፊቱ አሉ፡፡ አስቸጋሪ የሚባሉ ፈተናዎች የሉበትም፤ የተጋረጠበት ፈተና በሙሉ በትኩረት ከተሰራ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ድንቅ ፓርኮች አንዱ ይሆናል፡፡ ያን ቀን ለማየት እጓጓለሁ፡፡

 

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top