ሎካ አባያ-የአባያ ሥር፤ በሲዳማ ቆላ ምድር
(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በሲዳማ ክልል የሚገኘው ሎካ አባያ ብሔራዊ ፓርክ የአባያ ሥር ነው ይለናል፡፡ ለቀናት በብሔራዊ ፓርኩ የነበረውን ቆይታ እንዲህ ይተርክልናል፡፡ ሎካ አባያ የአጋዘን ምድር ነው ሲል ተከታታይ ትረካውን ይጀምራል፤ መልካም ንባብ፡፡)
(ሄኖክ ስዩም -ድሬቲዩብ)
ይህ የሲዳማ ቆላ ምድር ነው፡፡ ህንጣጤ ታላቁ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ ያረፈች ከተማ ናት፡፡ ሎካ አባያ የወረዳውም ስም ነው፡፡ ሲዳማ ክልል ነኝ፡፡ ህንጣጤ ከአዲስ አበባ 344 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኝ ከተማ ናት፡፡ ለመዲናችን ቅርብ ወደሚባለው አንዱ ብሔራዊ ፓርክ መጥቻለሁ፡፡ ሀዋሳ የደረሳችሁ 69 ኪሎ ሜትር ብትጓዙ የደረስኩበት ትደርሳላችሁ፡፡
በፓርኩ ከተማ በራፍ ላይ የምትገኘው የስምጥ ሸለቆ ከተማ እያደገች ነው፡፡ ነገ ይህንን ፓርክ ተስፋ አድርጋ የውብ መዳረሻ ከተማ ለመሆን ሩቅ ታማትራለች፡፡
ወደ ሎካ አባያ ገባን፡፡ እዚህ ይሄ አለ ብሎ ማመን ቢከብድም አስር አመታትን እንዲህ የኖረ ብሔራዊ ፓርክ ከዚህ ውበቱ ጋር በክብር ይታያል፡፡ የብሔራዊ ፓርኩ ደቡባዊ ክፍል ብላቴ ወንዝ ድንበሩ ነው፡፡ እስከ ብላቴ እንጓዛለን፡፡
ደግሞ ምዕራቡ ከጩኮ ወረዳ ይዋሰናል፡፡ ሰሜኑ የቦርቻ ወረዳን ይዞ እስከ ወላይታ ዞን የሚዘልቅ ነው፡፡ ከብዙ የኢትዮጵያ ፓርኮች አንድ ክልል ብቻ ሳይሆን አንድ ወረዳ ውስጥ የተካለለ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡ ሲዳማ ክልል ሎካ አባያ ወረዳ፤ ሎካ አባያ ብሔራዊ ፓርክ ደርሰናል፡፡
500 ካሬ ኪሎ ሜትር ስኩዬር ቆዳ ስፋት አለው፡፡ ቀድሞ በደቡብ ክልል ከሚገኙ ብሔራዊ ፓርኮች አንዱ ተብሎ የተካለለ ነበር፡፡ ሲዳማ ክልል ሲሆን በሲዳማ ክልል የሚገኘው ብሔራዊ ፓርክ ለመሆን በቅቷል፡፡ ሲዳማ የሰንቀሌ ቆርኪዎች መጠለያን ከኦሮሚያ ክልል ጋር የሚጋራ ሲሆን እንደ ዐይኑ ብሌን የሚመለከተው ይህ ፓርክ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ በክልሉ ግዛት ይገኛል፡፡
ሰንሰለታማ ተራሮች መታየት ጀምረዋል፡፡ አባያ ሐይቅ የብሔራዊ ፓርኩን አንድ ክፍል ይጋራል፡፡ ብላቴ የፓርኩ ገጸ በረከት ነው፡፡ ብላቴ ሲባል የምትሰሙት ወታደር ማሰልጠኛ ስሙን ያገኘው ከወንዝ ነው፡፡ የዚህ ወንዝ መጨረሻ እዚህ ፓርክ ደርሶ አባያ መግባት ነው፡፡ ደግሞ ሌላው ወንዝ ጊዳቦ ነው፡፡ ደርባና ማንቻ የሎካ አባያ ገጸ በረከት የሚባሉ ወንዞች ናቸው፡፡
የእጽዋት አይነቱ ብዙ ነው፡፡ ክረምት የደረሰ በበጋ አያውቀውም፤ ወቅት እየቀየረ ልብሱን ይቀይራል፡፡ አሁን ክረምት ደርሻለሁ፡፡ ሎካ አባያ አረንጓዴ ካባ በለበሰበት ዘመን ሳየው ዓይኔን ማመን አቅቶኛል፡፡
ከመጋቢት እስከ መስከረም የዝናብ ወቅት ነው፡፡ ነሐሴ የመጣሁት እንግዳ ለም ሆኖ የምመለከትው ብሔራዊ ፓርክ እጽዋት አብበው አየሁ፡፡
ሎካ አባያን ፓርክ ማድረግ ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት ተኩላን ለመጠበቅ ነው፡፡ የአፍሪካ ተኩላ ቀደም ባለው ጊዜ እንደልብ የሚታይበት ቀጠና ቢሆንም አሁን አሁን ግን ቦታና ወቅት የሚመርጥ ሆኗል፡፡
ደክሞናል፤ እዚህ እናድራለን፡፡ ሻሎ ሻሎ ብለን ወገን እያሞገስን ደስ የሚል አየር እየሳብን አባያን እያየን እንከርማለን፡፡ ምሽቱ ምን ይመስል እንደነበር ሲነጋ እነግራችኋለሁ፡፡