Connect with us

ትዝታ ብቻ ነው ፥ ወሎ የተረፈው

አምባሰልን ትህነግ፥ ኦነግ ባቲን ያዘው
ትዝታ ብቻ ነው፥ ወሎ የተረፈው

ጥበብና ባህል

ትዝታ ብቻ ነው ፥ ወሎ የተረፈው

አምባሰልን ትህነግ፥ ኦነግ ባቲን ያዘው
ትዝታ ብቻ ነው ፥ ወሎ የተረፈው
(አሳዬ ደርቤ ከድሬቲዩብ)

የመከላከያ ሠራዊት አባል ለመሆን የተመዘገበ ታናሽ ወንድሜ ወደ ማሰልጠኛ ጣቢያ የሚሄድበት ቀን በመቃረቡ የተነሳ የሽኝት ፕሮግራም ተዘጋጅቶለታል፡፡

ወንድሜን ይሸኙ ዘንድ የተጠሩ ወዳጆቻችን እና ጎረቤቶቻችን ቤቱን ሞልተውታል፡፡ ከእነዚህም እንግዶች መሃከል ከሰሜን ወሎ የተፈናቀሉ ዘመዶቻችን ይገኙበታል፡፡

ታናሽ ወንድሜ አባታችን ጎን ተቀምጦ አንዳንድ ተሞክሮዎችን ይቀስማል፡፡አባቴ በደርግ ዘመነ መንግሥት የኢትዮጵያ ወታደር የነበረና የመቶ አለቃ ማዕረግ ያለው ሲሆን የመቶ አለቃ ማዕረጉን ከሚረሱበት ሥሙንና ያበደራቸውን መቶ ብር ቢዘነጉበት ይመርጣል፡፡

በመሆኑም መቶ አለቃ የሚል ማዕረጉን እረስተው ‹‹አቶ ይሳቅ›› በማለት ሲጠሩት ‹‹አቤት›› በማለት ፈንታ ‹‹ጥርስህ ይውለቅ›› በማለት ቁጣውን ይገልጻል፡፡ እኛ ልጆቹ እራሱ ‹‹አባዬ›› ከምንለው ይልቅ ‹‹መቶ አለቃ›› ስንለው ደስ ይለዋል፡፡

እናም በሽኝቱ ላይ ሜዳሊያውን እና ኒሻኑን ኮቱ ላይ ደርድሮ የተቀመጠ አባታችን የእራሳቸውን ሥራ ይዘውና ትዳር አፍርተው የሚኖሩ ልጆቹን ከምንም ሳይቆጥር ‹‹ከልጆቼ መሃከል ለትልቅ ሃላፊነት የታጬ አንድ ልጅ ወጣልኝ›› እያለ ደስታውን ይገልጻል፡፡

በነገራችን ላይ በባድሜው ጦርነት ጊዜ በአባቴ ተጽእኖ እና በወሎ የኪነት ቡድን ተገፋፍቼ ወታደር ለመሆን ሞክሬ ነበር፡፡ መዝጋቢዎቹ ‹‹እድሜህ አልደረሰም›› ብለው መለሱኝ እንጂ…

ይሄንንም ሁኔታ ለመቶ አለቃ ከነገርኩት በኋላ ጉቦ ከፍሎ ሊያስመዘግበኝ ሲሞክር እናቴ በመስማቷ ‹‹በምንም ተዓምር ያለእድሜው አታዘምተውም›› ብላ እሪታዋን ስላቀለጠች የልጅነት ሕልሜ ሊጨናገፍ ችሏል፡፡

ያን ጊዜ ታዲያ እኔ ልዘምት ስል በለቅሶና በእሪታ ያስቀረችኝ እናቴ ዛሬ በደስታና በፌሽታ ታናሽ ወንድሜን በመሸኘት ላይ ትገኛለች፡፡

ይሄንን የአስተሳሰብ ለውጥ ያመጣውም እናታችን የእኔን ያህል ታናሼን ስለማትወደው አይደለም፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የወሎ ምድር ያስተናገደው ጥቃት አንጀቷን እርር ስላደረገው እንጂ! ‹‹እርባና የለሽ ወጣት ሆኖ ከመላው ቤተሰቡ ጋር የስጋት ተቋዳሽ ከሚሆን ወታደርነት ሰልጥኖ አገሩንና ወገኑን ያስከብር›› ብላ ስለወሰነች እንጂ…

የቤተሰባችን የመጀመሪያ ልጅ የሆነችው ታላቅ እኅቴ ግን ወንድማችንን ከመሸኘት ይልቅ ለማስቀረት አስባ ቀኑን ሙሉ ስትለምነው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ‹‹አገሬንና ወገኔን ጠባቂ መሆን ስችል ከቤተሰቤ ጋር ተጠቂ የምሆንበት ምንም አይነት ምክንያት አይኖርም›› የሚል አቋሙን ማስቀየር ስላልቻለች ‹‹እባክህን ቅር›› የሚል ልመናዋን ትታ በሞባይሏ አማካኝነት ፎቶውን ታስቀር ይዛለች፡፡

ቤታችን ውስጥ የተሰባሰቡት ታዳሚዎች ምግቡን በልተው፣ ጠላና ብረታ ብረቱን እየተጎነጩ ወንድሜን ሲመርቁት ከቆዩ በኋላ አዝማሪው ይብቃ ማሲንቆውን ከጎኑ አንስቶ መገዝገዝ ጀመር፡፡ ቅኝቱንም አምባሰል ላይ በማድረግ
‹‹አምባሳል ተንዶ ፥ ግሼን ደግፎታል
አምባሰል መናዱ ፥ ያንቺ ቃል ፈርሶ ነው
ግሼን መደገፉ ፥ የኔ ቃል ማክበር ነው
ይብላኝልሽ ላንቺ ፥ ቃልሽ ለፈረሰው
የጁን መች ያጣዋል ፥ ቁሞ ከሄደ ሰው›› ማለት ሲጀምር ከሰሜን ወሎ የተፈናቀሉ ዘመዶቻችን ሆድ ብሷቸው እንባቸውን ያብሱ ጀመር፡፡ ከእነዚህም ብሶተኛ ተፈናቃዮች መሃከል አንዱ የሆኑት ሽማግሌ ‹‹ተቀበል›› ብለው አዝማሪውን ከተጣሩ በኋላ

የአምባሳል ማር ቆራጭ ፥ ክላሹን አንስቶ
ምድሩን እስኪያጸዳው ፥ መርሳ የጁ ዘምቶ
አፈር ስሆን ልጄ ፥ ቅኝቱን ቀይረው

ሕመም ነው አምባሰል፥ መሬቱን ላጣ ሰው›› የሚል ስንኝ አቀብለው ቅኝቱን አስቀየሩት፡፡ አዝማሪውም ቅኝቱን ባቲ ላይ አድርጎ፡-
‹‹ወጉን ጨዋታውን ፥ ልቤ ከወደደው
እስኪ ከሞቀበት ፥ ከባቲ ልሂደው›› ማለት ሲጀምር የቅድሙ ሽማግሌ በድጋሜ ‹‹ተቀበል›› ብለው ተጣሩ፡፡ ከዚያም፡-
‹‹አምባሰልን ትህነግ፥ ኦነግ ባቲን ያዘው
ትዝታ ብቻ ነው ፥ ወሎ የተረፈው›› የሚል ቅኔ ተቀኙ፡፡

ይሄንንም በጥቃት አርጩሜ የሚያንገበግብ ስንኝ ከጎኔ ተቀምጣ ስታዳምጥ የቆየች ታላቅ እኅቴ ወንድማችንን ለማስቀረት ስትለፋ እንዳልቆየች ሁሉ ‹‹አንተስ ለምን አትዘምትም?›› በሚል አኳኋን ‹‹ወታደር ለመሆን እድሜህ አልፏል እንዴ?›› ስትለኝ ጎፈሬ አልባ መላጣዬን ዳበስበስ እያደረግኩ እድሜየን እቆጥር ጀመር፡፡

 

Click to comment

More in ጥበብና ባህል

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top