Connect with us

አርቤ ጎና የምንጮቹ መነሻ የጋራምባ እናት ምድር!!

ሄኖክ ስዩም

ባህልና ታሪክ

አርቤ ጎና የምንጮቹ መነሻ የጋራምባ እናት ምድር!!

አርቤ ጎና የምንጮቹ መነሻ የጋራምባ እናት ምድር!!

(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም የገናሌ ወንዝን መነሻ ፍለጋ የሎጊታና ጋላና ወንዝን ተከትዬ ሲዳማ ደጋ ምድር ደረስኩ ሲል ጋራምባ ተራራን እንዲህ ያስቃኘናል፡፡ እስከ ባሌ ተራሮች የሚዘረጋው የተፈጥሮ ቅርስ የመጪው ዘመን የኢኮ ቱሪዝም ቀጠና ነው ይለናል በተከታዮ ዘገባው፡፡)
(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)

“ወየት ነህ? ዩኔስኮ” እንኳን ይሄን አላየህ፤ ናላህ ዞሮ ግራ ይገባህ ነበር፡፡ ናላዬ ዞሯል፡፡ እንዲህ ያለ ደርባባ ተራራ ዓይን አይቶ አይጠግበውም፡፡ አርቤ ጎና ነኝ፡፡ ጋራምባ፡፡ ይህ አምባ ተራራ ብቻ አይደለም፡፡ የባህል ሰገነት ነው፡፡ የውበት ከፍታ ነው፡፡ የሲዳማ ቱባ ባህል ከነክብሩ እዚህ አለ፡፡

የገናሌ መነሻ፣ የጋዋ መፈጠሪያ፣ የጋለና ምንጭ፣ የብዙ ወንዞች መጀመሪያ- የአንጋፋዎቹ ወንዞች ማኅጸን፡፡ ከመቶ በላይ የምንጮች መገኛ፡፡ ሲዳማ ድንቅ ባህላዊ መልከዓ ምድር አለው፡፡ ይሄንን ከማመን ያለፈ ምስክር ትሆኑ ዘንድ እንደ እኔ እዚህ ድረሱ፡፡

የጋራምባ ተራራ አናት ከባህር ጠለል በላይ 3368 ሜትር ከፍታ አለው፡፡ የሲዳማ ምድር ትልቁ ከፍታ ነው፡፡ ትልቁ ተራራ ግርጌ ደርሻለሁ፡፡ አንድ ተራራ ብዙ መልክ፡፡ ወዲያ ውብ የሲዳማ የደጋ ቤቶች የቱሪስት መንደር መስለው ተኮልኩለዋል፡፡ ወዲህ ውበትና ሕይወት አለ፡፡ እዚህ እያንዳንዱ የአርሶ አደር ቤት ሎጂ ነው፡፡ ቅንጡ ሎጂ፡፡ ከአካባቢው የተራቀ ምድር፡፡

የጋራምባ ተራራ ከክልሉ መዲና ከሀዋሳ ደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ ይገኛል፡፡ ደግሞ ወዲያ ሲታይ ሌላኛው መልክ አለ፡፡ ጥቅጥቅ ደን፤ ውብ አምባ፤ የቀርቀሃ ዛፎች ያስጌጡት ምድር፡፡ የሲዳማ ወንዞች ወተት መስሎ መጓዝ ደጋው እንዲህ አረንጓዴ ካባ መጎናጸፉ እንደሆነ ገባኝ፡፡

ደግሞ ወዲያ አየሁ፤ የእርሻ ማሳ፣ የእንሰት ተክል፤ ውብ መስክ፡፡ ለዚህ ነው አንድ ተራራ አይደለም የምላችሁ፡፡ ሞገስ ያላቸው የባህል አባቶች መኖሪያ ነው፡፡ ሎካን ቁልቁል እያየ ስምጥ ሸለቆ አፋፍ በኩራት የሚኖር፤
ይህ ለኤኮ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ አዲስ ተስፋ ነው፡፡ ሀገር ገና ያልተጠቀመችበት ድንግል ሀብት፡፡ ብቻውን አይደለም፤ ባህል አጅቦታል፡፡ የሲዳማ እሴት እንደ ደኑ የከበበው ነው፡፡ ደግሞ ለዱር እንስሳት ቱሪዝም ይመቻል፡፡

ነብርና አቦሸማኔ ይዟል፡፡ ቀይ ቀበሮ አለው፡፡ የአፍሪቃ ዱር ውሻ መኖሪያ እንደሆነ ነግረውኛል፡፡ ደግሞ እጽዋቱ ሀገር በቀል ዛፉ፤ ብቻ ጋራምባ የውበትም የሀብትም ተራራ ነው፡፡
ከቁመቱ ጸጋው ይበልጣል፡፡ ሰንሰለቱ ከባሌ ተራሮች ይዛመዳል፡፡ ቱሉ ዲምቱ የሚደርስ የተፈጥሮ ጎዳና ነው፡፡

ለተራራ ቱሪዝም ምቹና ለተዛመደ የቱሪዝም ልማት እምቅ አቅም፡፡ አሉ መባል ምንኛ መታደል እንደሆነ አስቡት፤
ገና ዓለም አይደለም የሀገር ሰው አላየውም፤ ተራራ ላይ ያለ ጸጋ ቢሆንም በቱሪዝም ልማት ሸለቆ ውስጥ ያለን ምስኪኖች ነን፡፡ ማን ያውቃል፤ የኢትዮጵያ የመጪው ዘመን የኢኮ ቱሪዝም አምባ የሚሆንበት ቀን ቅርብ ይሆናል፡፡ ያ ቀን እንዲቀርብ እሰራለሁ፤ አንድ ቀን በቴሌቨዥን መስኮት ላሳያችሁ ሕይወት በጋራምባ ብዬ እሰነብትበታለሁ፡፡ ያን ቀን ሳስብ ጋራምባ ይናፍቀኛል፡፡ እንኳን የሀገሬ ሀብት ሆነ፡፡

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top