Connect with us

አሸባሪው ህወሃት ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ልብና ህሊና ውስጥ ወጥቷል

አሸባሪው ህወሃት ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ልብና ህሊና ውስጥ ወጥቷል - አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ
Ethiopian News Agency

ዜና

አሸባሪው ህወሃት ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ልብና ህሊና ውስጥ ወጥቷል

አሸባሪው ህወሃት ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ልብና ህሊና ውስጥ ወጥቷል – አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ

“አሸባሪው ህወሃት ከስልጣን መወገድ ብቻ ሳይሆን ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ልብና ህሊና ውስጥ ወጥቷል” ሲሉ በተመድ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ገለጹ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ጸጥታ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለመምከር በተያዘው አጀንዳ ላይ የሚመክር ስብሰባ ተቀምጠል።

በመድረኩ ስለ ኢትዮጵያ ሁኔታ ያስረዱት በተመድ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ስለወቅታዊ ሁኔታ ማብራሪያ አቅርበዋል።

“በኢትዮጵያ አሁን የተፈጠረው ችግር መሰረቱ የተጣለው ከሶስት አስርታት በፊት ነው” ያሉት አምባሳደሩ፤ አሸባሪው ህወሃት በፖለቲካ፣ በደህንነትና በኢኮኖሚ የበላይነትን ወስዶ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ቡድኑ በዘመነ አገዛዙ ሁሉ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ ተቃውሞ ያስተናግድ እንደነበር አስታውሰው፤ ከፍተኛና ተከታታይ የህዝብ ተቃውሞ አስተናግዶ ከስልጣን ተወግዶ አገራዊ ለውጥ መምጣቱን ገልጸዋል።

“አሸባሪው ህወሃት ከስልጣን መወገድ ብቻ ሳይሆን ከሁሉም ኢትዮጵያውያን ልብና ህሊና ውስጥ ወጥቷል” ብለዋል።

በሚከተለው አካታች ያልሆነ ርዕዮተ ዓለም የተነሳ አንድነትን ለማሳጣት ከፋፋይ መንገድ ይከተል እንደነበር አስገንዝበዋል።

ከመንበረ ስልጣን የተወገደው ህወሃት የትግራይ ህዝባችንን እንደመያዣ ይዟል” ያሉት አምባሳደር ታዬ፤ መንግስት ቡድኑ ወደ መስመር እንዲገባና ለህግ እንዲገዛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል።

መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ አሳልፎ የአገር መከላከያ ሰራዊት ከትግራይ ክልል እንዲወጣ በማድረግ አርሶ አደሩ እንዲያርስና አሸባሪው ቡድንም የማሰቢያ ጊዜ እንደተሰጠው ገልጸዋል።

የተኩስ አቁም ውሳኔውን በመናቅ ህጻናትን በግዳጅ ለጦርነት በማሰማራት የጥይት ማብረጃ እያደረጋቸው እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከትግራይ ክልል አልፎ በአፋርና በአማራ ክልሎች የሚገኙ አርሶ አደሮች ስራቸውን መስራት እንዳይችሉ ማድረጉን አስረድተዋል።

ይህ ብቻ ሳይሆን የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ድጋፉ እንዳይደርስ አሸባሪው ህወሃት መዝጋቱን አብራርተዋል።

ቡድኑ ከውስጥና ከውጭ ተባባሪ ሃይሎቹ ጋር በመቀናጀትና በመናበብ ታላቋን ኢትዮጵያ አለመረጋጋት ውስጥ ለመክተት እየተንቀሳቀሰ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

የትግራይ፣ አፋርና አማራ ክልሎች ህዝቦች የማይገባቸው ስቃይ ውስጥ መግባታቸውን ገልጸው፤ ለህግ የማይገዛው ቡድን ላይ ጫና በማድረግ የሰላም ጥረቱን ማገዝ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብም ለቡድኑ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያቋርጥ ጠይቀው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ሰላም ለማምጣትና ህግን ለማስከበር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

በዛሬው ዕለት በጸጥታው ምክር ቤት አንዳንድ አባላት የቀረቡት ጉዳዮች በተሳሳተ መረጃ ላይ የተመሰረተ ስለመሆኑ ጠቅሰው፤ ሀይማኖት፣ ብሔርና ወይም ሌላ ጉዳይን መነሻ አድርጎ የሚፈጸም ማግለል እንደሌለ ገልጸዋል።

“እኛ እሴት ያለን ህዝብ ነን እንጂ፤ የወረደ ሞራል የለንም” ያሉት አምባሳደር ታዬ፤ የኢትዮጵያ አንድነት የተመሰረተው ልዩነትን በማክበር እንደሆነ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የውጭ ጣልቃ ገብነትን ማስተናገድ የሚችል ሁኔታ እንደሌለ አስገንዝበው፤ “ከእኛ ጋር ለመስራት ከሚፈልጉ ጋር አብረን ለመስራት ዝግጁ ነን” ብለዋል። 

የሩሲያ፣ የቻይና የህንድና የኬኒያ አምባሳደሮች ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሯን በራሷ መፍታት እንደምትችልም አስረድተዋል።

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top