Connect with us

የዶላር ዋጋ ለምን ጨመረ?

የዶላር ዋጋ ለምን ጨመረ?
ሲራራ

ነፃ ሃሳብ

የዶላር ዋጋ ለምን ጨመረ?

የዶላር ዋጋ ለምን ጨመረ?

(ፀጋዬ ዳባ)

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በትይዩ (ጥቁር) ገበያው እና በባንኮች መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሪ ተመን ልዩነት ለማጥበብ የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል፡፡ በዚህም የተገኙ ውጤቶች ነበሩ፡፡ አሁን ግን በትይዩ ገበያው እና በባንኮች መካከል ያለው ልዩነቱ ከዚህ ቀደም ከነበረውም  ከፍ ብሏል፡፡ አንድ ዶላር በባንክ ቤት 45 ብር እየተመነዘረ ሲሆን፣ በትይዩ ገበያው ላይ ግን ከ60 እስከ 70 ብር ድረስ ሲመነዘር ሰንብቷል፡፡ ይህም ከባንክ ጋር ያለውን የተመን ልዩነት ከ20 ብር እስከ 25 ብር እንዲደርስ አድርጎታል፡፡ ትይዩ ገበያው ሊረበሽ የሚችባቸው በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ 

እነዚህ ምክንያቶች ውስጥ አንዳንዶቹ ከገበያው/ከኢኮኖሚው ጋር የማይገናኙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

አገራችን ግጭት ውስጥ እንደሆነች ይታወቃል፡፡ አገር በግጭት ውስጥ ስትሆን ለሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ የሚውለው ዶላር መጠን እየጨመረ ስለሚሄድ የዶላር ፍላጎቱ ከፍ እያለ  ይመጣል፡፡ ጦርነት ሲኖር የመሣሪያ ግዥዎች ይጨምራል፡፡ በአሸባሪው አካል ጦር መሣሪያ ሲፈልግ የሚገዛው በትይዩ ገበያ ላይ ባለ ሕገወጥ ዶላር ነው፡፡

በዓለም ዐቀፍ ላይ ባለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ብዙ አገራት ከገቡበት ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ማገገም አልቻሉም ነበር፡፡ ይልቁንም ሁለተኛው ዓይነት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመነሳቱ ዓለም ስጋት ውስጥ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ከውጭ አገራት በተለያየ መንገድ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው የውጭ ምንዛሪ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል፡፡ በውጭ አገራት የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በትይዩ ገበያ ወደ አገር ቤት የሚልኩትን ዶላር ቀንሰዋል፡፡  

ሁለተኛው ለትይዩ ገበያው ትልቅ የዶላር ምንጭ የነበረው የሰዎች ዝውውር (ጉዞ) እና ስብሰባ በኮቪድ-19 ምክንያት ቀንሷል፡፡ ሰዎች ጉብኝት እና ስብሰባ ሲመጡ ያመጡትን ዶላር ይመነዝሩ የነበረው በትይዩ ገበያው ላይ ነው፡፡ አሁን ላይ ይህ የዶላር ግኝት ተቀዛቅዟል፡፡

መንግሥት ከሰሞኑ የሕወሓትን አሸባሪ ቡድን በገንዘብ ሊደግፉ ይችላሉ ያላቸውን ተቋማት እያሸገ እና እየዘጋ፣ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ግንኙነቶች ለመያዝ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ በተለያዩ አካላት ላይ መደናገጥን ፈጥሯል፡፡ ይህም ሰዎች ተደናግጠው ያላቸውን ንብረት በዶላር ቀይረው  ከአገር ለማስወጣት ሊፈልጉ ይችላሉ፡፡

አሁን በገበያው ላይ ባለው የዋጋ ንረት ምክንያት ሰዎች ገንዘባቸውን በዶላር ቀይረው የማስቀመጥ ልምዳቸው ከፍ ሊል ይችላል፡፡ የተሻለ ገንዘብ ያለው ገንዘቡ በዋጋ ንረት እንዳይበላ  መኪና እና ቤት እየገዛ ነው፡፡ እጁ ላይ ለመኪና እና ቤት የሚበቃ ገንዘብ የሌለው ሰው ገንዘቡን በዶላር ቀይሮ ሊያስቀምጥ ይችላል፡፡ በቤት ውስጥ ማስቀመጥ የሚፈጥረው የደህንነት ስጋት እንዳለው ልብ መባል አለበት፡፡

ከዚህ በላይ ባነሳኋቸው የግል ምልከታዎቼ ምክንያት በትይዩ ገበያው ላይ ያለው የዶላር አቅርቦት እና ፍላጎት መጣጣም አልቻለም፡፡ በዚህ ምክንያት የዶላር ዋጋ ሊጨምር ይችላል፡፡የትይዩ ገበያው ላይ መከፋፈል እንዳለ እያየንም ነው፡፡ አንድ ዶላር አንዳንድ ቦታ 55 ሌላ ቦታ 65  እስከ 70 ብር ድረስ እየተሸጠ ይገኛል፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አንድ ዶላር እስከ 67 ብር  ድረስ ሲሸጥ የሰነበተ ሲሆን፣ ወደ ድንበር አካባቢዎች ላይ ወደ 70 ብር  ከፍ ብሎ ነበር። እርግጥ በዚህ ሳምንት ለውጥ አለ።

አንዳንድ ባለሞያዎች የንግድ ባንክ ከሰሞኑን ለነጋዴዎች የለቀቀውን የ‹ኤል.ሲ› ዶላር እንደ ምክንያት ያነሳሉ፡፡ ይህ ምክንያት በተወሰነ መልኩ አስተዋጽዖ ሊያበረክት ቢችልም፣  እንደ ዋና ምክንያት ሊጠቀስ የሚችል አይደለም፡፡ በቅርብ በተደረጉ ጥናቶች የትይዩ  ገበያው 60 በመቶ የሚውለው ለነጋዴዎች እንደሆነ ታይቷል፡፡ የተቀረው 40 በመቶ ለጉዞ እና ሕገ-ወጥ እቃዎችን ለመግዛት ነው፡፡ ያ ማለት ቀድሞም ነጋዴው ለንግድ ሥራው የትይዩ ገበያን ይጠቀማል፡፡ የንግድ ባንክ ‹ኤል.ሲ› መፍቀድ አዲስ ነገር ላይሆን ይችላል፡፡ በእኔ እምነት ትልቁ ምክንያት የፖለቲካው ቀውስ እና መረበሽ ነው፡፡ ፖለቲካው ላይ አለመረጋጋት ሲኖር ሰው በስጋት በሚያደርገው እንቅስቃሴ የዶላርን ዋጋ ሊጨምረው  ይችላል፡፡ እሱ መልክ እየያዘ ሲመጣ ሌላውም መስመር ይይዛል።(ሲራራ)

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top