ምሁር ኢየሱስ ደርሻለሁ!
(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ወደ ጉራጌ ዞን ምሁር አክሊል ወረዳ ተጉዟል፡፡ ምሁር ኢየሱስ ደርሻለሁ በሚልበት ትረካው ታሪካዊውን ገዳምና የገዳሙን ገጽታዎች ያስተዋውቀናል፡፡ ቆይታው በምናብ እንመለከተው ዘንድ እንዲህ ያስቃኘናል፡፡)
(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)
የጉራጌ መንደር ለወትሮውም ውብ ነው እንኳን በክረምት፡፡ ወንዞቹ ይገማሸራሉ፡፡ ቀዬው ልዩ ቀለም አርፎበታል፡፡ ጆፎረው አረንጓዴ ምንጣፍ የተነጠፈበት ጎዳና መስሏል፡፡ ደስ የማይል እና ዓይን የማይገዛ ነገር ማየት ብርቅ ነው፡፡
ምሁር አክሊል ወረዳ ነኝ፡፡ ጠንካራዎቹ ኢትዮጵያውያን ሰፈር፡፡ ብዙ ነገር ይታያል፡፡ ብዙ ነገር ይሰማል፡፡ ተፈጥሮ ታሪክ ባህል ቅርስ የሌለውን ልንገራቸሁ? ጠብ፣ ቂም፣ ጥላቻ፣ ክፋትና ምቀኝነት ናቸው፡፡
ከወልቂጤ 52 ኪሎ ሜትር ተጉዤ መጥቻለሁ፡፡ አዲስ አበባ ከዚህ 207 ኪሎ ሜትር ገደማ ትርቃለች፡፡ ውበቱንና የአካባቢውን ጤናማ አየር ላጤነ ግን ብዙ ዘመን ርቆ የመጣ፣ ኪሎ ሜትር የማይለካው ጉዞ ተጉዞ የደረሰ ይመስለዋል፡፡ እንዲያ ያለ ስሜት ተሰማኝ፡፡
ሐዋርያትን አልፌያለሁ፡፡ የከተማ ስም ነው፡፡ የምሁር አክሊል ዋና ከተማ ሐዋርያት ትባላለች፡፡ ከሐዋርያት ከተማ ጥቂት ወጣ እንዳልኩ የገዳሙ ድባብ ጀመረ፡፡ ይህ ኢየሱስ ገዳም ቀበሌ ነው፡፡ ቀደምቱ የኢትዮጵያ ገዳም፡፡ ታሪካዊው ስፍራ፤እንዲህ ያለ ውብ ሥፍራ በመምጣቴ ደስ ብሎኛል፡፡
አካባቢው መንፈስ ያሳርፋል፡፡ እዚህ መድረስ ብቻውን መታደል ነው፡፡ ቀጥሎ የሚሆነውን አሰብኩት፡፡ አሁን ቀደምቱ ገዳም ደርሻሁ፡፡ እዚህ በደቡብ ኢትዮጵያ አንጋፋ ከሚባሉት ዋናው ገዳም ለዘመናት ኑሯል፡፡ ምድረ ጉራጌ-ምሁር አክሊል፡፡
ምሁር ኢየሱስ ረዥም ዘመን የኖረ ታሪክ አለው፡፡ ቅድመ ዘመነ ዩዲት የተተከለ ነው፡፡ የሺህ ሁለት መቶ አመት እድሜን ኖሯል፡፡ በየዘመናቱ ታሪክ ተቀምጦበት፣ እምነት ተሰብኮበት ዛሬ ደርሷል፡፡ ዛሬ እኔ እዚህ ደርሻለሁ፡፡ ምሁር ኢየሱስ፤ረዣዥሞቹ ዛፎች ረዥም ዘመን የኖረውን ገዳም ቅጥር ከበውታል፡፡
እንኳን ከእኔ ዓይን ከጉራጌ ተራሮችም ሸሽገውታል፡፡ ደርሼም የምመለከተው ዛፍ ነው፡፡ ሀገር በቀል እና ጉም ከሰማይ የሚዳስስ ዛፍ፤
የምሁር ኢየሱስ ታሪክ ወደ ገዳምነት የተቀየረው በታላቁ ቅዱስ በአቡነ ዜና ማርቆስ ነው፡፡ ዜና ማርቆስ ወንጌልን ለመስበክ እዚህ ደረሱ፡፡ እዚህ ብዙ መንፈሳዊ ተጋድሎዎች ሆኑ፡፡ ታሪካቸው ከስፍራው ጋር ታተመ፡፡
ጻድቁ አቡነ ዜና ማርቆስ የተወለዱት ሰሜን ሸዋ ነው፡፡ ተጉለትና ቡልጋ ይባል የነበረው ምድር፤ እቲሳ ተክለ ሃይማኖት፡፡ የአቡነ ተክለ ሃይማኖት አጎት ናቸው፡፡ ዘመኑ 14ኛው ክፍለ ዘመን ነው፡፡
ከዐፄ ይኩኖ አምላክ እስከ ዐፄ ናኦድ ዝናው የናኘ፤ ስሙ የተጠራ፣ ቅዱሳን በረገጥነው ሲሉ ከዳር ዳር ሀስሰው የሚረግጡት የበረከት ቦታ ሆኖ ታወቀ፡፡
አሁን ተጠጋሁ፡፡
የቤተክርስቲያኑ ቅጥርም፣ አዲሱ ህንጻ ቤተ ክርስቲያንም ታዩኝ፡፡ የገዳሙ ቅ0ጥር ገባሁ፡፡ እነኛ ረዣዥም ዛፎች የከለሉኝን በደንብ አየሁት፡፡ ከእኔ ጋር እዚህ ታላቅ ስፍራ ደርሳችኋል፡፡ እ”0ንዴት ያሉ አባቶች ተቀበሉኝ፡፡ ምሁር ኢየሱስ የሀገሬ ምድር ታላቁ ገዳም፤ ምሁር አክሊል!