ቴዲ “ኢትዮጵያ” አለ፡፡ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ “አቤት”፤ የምናከብረውን የጥበብ ሰው ያከበረልንን ዩኒቨርሲቲ አመስግነናል!
(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)
ስለጎንደር ዩኒቨርሲቲ ብዙ ጊዜ ብዙ ብያችኋለሁ፡፡ የተቋሙ ይሄን መምስል ስሪቱ ነው፡፡ ሀገሬው እንደውም ለእርሱ ቅርብ ለምናቡ ባለድርሻ ስለሆነ “የ” ጨምሮ “የጎንደር ዩኒቨርሲቲ” ይለዋል፡፡
መሪዎቹ ተቀያይረው ጀምሮ ሜዳ የጣለው ጉዳይ የለም፡፡
ከፍታው አስጠብቆ ለመቀጠል ያለ እረፍት ይሰራል፡፡ ብቃት ምዘና ካለ ዋንጫው ታሪካዊቷ ከተማ ከመግባት የሚያግደው አንዳች ነገር የለም፡፡ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ፤
አሁን ደግሞ “ኢትዮጵያ” ሲባል አቤት አለ፡፡ ጠሪው የጥበብ ሰው ነው፡፡ ቃሉ ነውር እስኪመስል በታወጀበት፤ የሀገር ምልክት እንዳይኖር በየሰፈርህ ብቻ ተሰለፍ በተባለበት፡፡
ሰፈር ያከበረው ሀገር ጋር ሊደርስ ሲል እንቅፋት በሚበዛበት ዘመን “ኢትዮጵያ” ብሎ የተጣራ የሚችል የጥበብ ሰው፡፡
ያን ድምጽ ሚሊዮኖች አቤት ብለውታል፡፡ በኢትዮጵያ የዝና ከፍታ አውራውን ስፍራ ይዟል፡፡ ትውልድ እንደ መንፈስ ያዳረሰ ሀገር መውደድን አስተጋብቷል፡፡ ኢትዮጵያ የማለትም ሆነ በኢትዮጵያ በጥበብ ከፍ የማለት ምልክት ሆኗል፤ ቴዎድሮስ ካሳሁን፡፡
የእሱን ጥሪ ነው ጎንደር ዩኒቨርሲቲ አቤት ያለው፡፡ ፍቅር ያሸንፋል ባዩ፤ በቃሉ ተቋም አሸንፏል፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አጸደ ወይን በፌስ ቡክ ገጻቸው ስለ አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን የ2013 ዓ.ም. የምረቃ ዘመን ለክብር ዶክትሬት ተመራጭነት ምክንያት ሲያሰፍሩ፤
“የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጉባኤ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር ፪፻፵፩/ ፳ሽ፫ በተሰጠው ስልጣን መሠረት ሐምሌ 22 ቀን 2013ዓ.ም ባካሄደው ጉባዔ “ፍቅር ያሸንፋል” በሚለው መርሑ ለሚታወቀው ተወዳጁና የዘመናችን የሙዚቃ ፈርጥ ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን በሂዩማን ሌተርስ የክብር ዶክትሬት ሰጥቷል።
ዩኒቨርሲቲያችን ለዚህ የአገር ባለውለታ ተገቢውን ክብርና እውቅና በመስጠቱ ታላቅ ደስታ ይሰማዋል።
ሐምሌ 22/2013ዓ.ም.” ብለዋል፡፡
የጥበበኛው አፍቃሪዎች ጥበበኛውን ስላከበረው ዩኒቨርሲቲ ክብር አለን፡፡ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከዚህ ቀደም ዘመን አይሽሬውን የትዝታ ንጉሥ መሐሙድ አህመድን አክብሮልናል፡፡ ያቺ ንስር ሯጭ መሠረት ደፋርን ክብር ዶክተር አድርጎልናል፡፡ አስቴር አወቀን ያከበርልን የተከበረው ይሄው ተቋም ነው፡፡ ታላላቆቻችንን በማክበር አንዱና ትልቁ ተቋማችን ስለሆነም እናመሰግናለን፡፡
ቴዎድሮስ ካሳሁን ሐምሌ 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን በድምቀት በሚያስመርቅበት ቅዳሜ በአፍሪካ ካሚሎት የመናገሻዋ ከተማ ተገኝቶ የክብር ዶክትሬቱን ይወስዳል፡፡ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ለድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን የክብር ዶክትሬት ሲሰጥ የመጀመሪያው መሆኑ በታሪክ ልዩ ስፍራ ይኖረዋል፡፡ ቴዎድሮስ ካሳሁን አምናለሁ ከዚህ በኋላ ከሀገር ውስጥና ከውጪ በርካታ የክብር ዶክትሬቶችን ይወስዳል፡፡
ፍቅር ያሸንፋል ብለው የማያሸንፉት አሰራር፣ ደጃፍ፣ ልብና መንፈስ የለም፡፡ ኢትዮጵያ ፍቅር የሚያሸንፍባት፣ ታላቅነት የሚመለስባት፣ ዓለም የሚያከብራት ትሆን ዘንድ አዲሱ ትውልድ ላይ አዲስ መንፈስ በመዝራት በጥበብ ሀገርና ትውልድ ለሰራው ለዚህ ስመ ጥር ድምጻዊ የተሰጠው የክብር ዶክትሬት ብዙ ለደከመው እና ብዙ ለከፈለው ቴዎድሮስ ካሳሁን፣ ከጎኑ ላለችው ባለቤቱ፣ ነገ ቀና ብሎ የሚያስኬድ ታሪክ ለሰራላቸው ልጆቹ፣ ለሚያደንቁት ሚሊዮኖች የምሥራች ነውና እንኳን ደስ ያለን፤ እንኳን ደስ ያላችሁ!!