የሀኒሽ ደሴቶች ነገር….
(እስክንድር ከበደ – ድሬቲዩብ)
የሀኒሽ ደሴቶች በቀይ ባህር የሚገኙ የደሴቶች ስብስብ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1915 የሀኒሽ ደሴቶች በብሪታኒያ መያዛቸው ይነገራል፡፡ ብሪታኒያ ደሴቶቹን የተቆጣጠረችው ፤ ጣሊያን እንዳትይዛቸው ለመከላከል ነበር፡፡
በኃላ በኤርትራ የጣሊያን ቀኝገዢ አስተዳደር ስር እስከ እ.ኤ.አ 1941 ይተዳደሩ ነበር፡፡
በኤርትራ የጣሊያን አገዛዝ በብሪታኒያ ጦር መሸነፉን ተከትሎ ፤ ብሪታኒያ ተቆጣጥራቸው እንደነበር ይነገራል፡፡ ብሪታኒያ ኤርትራን ለኢትዮጵያ አስረክባ ስትወጣ የሀኒሽ ደሴቶችም በኢትዮጵያ መተዳደር ቀጠሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ አመታት ወቅት ኢትዮጵያና የመን የሀኒሽ ደሴቶች ይገባኛል በሚል ሲወዛገቡባቸው ቆይተዋል፡፡
የኤርትራ ነጻ አውጪ ቡድኖች በሀኒሽ ደሴቶችና በአቅራቢያው በምትገኘው ዛኩራ ደሴት እንደ ጦር ምድባቸው ተጠቅመው በኢትዮጵያ ወታደራዊ ጥቅሞች ላይ ጥቃት ያደርሱ ነበር፡፡ የሀኒሽ ደሴቶች በኢትዮጵያ የግዛት ተደርገው የሚወሰዱ ስትራቴጂክ ይዞታዎች ነበሩ፡፡
እ.ኤ.አ በ1991 ኤርትራ ነጻ ሀገር መሆኗን ተከትሎ፤ ከ5 አመታት በኋላ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር በሚል የሀኒሽን ደሴቶች ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር ባደረገችው እንቅስቃሴ ከየመን ጋር ውጊያ አካሄደች፡፡ የሀኒሽ ደሴቶች አራት ዋና ዋና የደሴቶች ቡድን ይዟል፡፡
ሀኒሽ ከባብኤል መንደብ በስተሰሜን በ160 ኪሎሜትር ርቀት የሚገኝ ስትራቴጂክ የደሴቶች ስብስብ ነው፡፡ ከሰሜን ወደ ደቡብ 65 ኪሎሜት ርዝመት የሚዘልቅ ሲሆን፤ከኤርትራ ይልቅ ለየመን ይቀርባል፡፡ ከየመን ባህር ዳርቻ በስተምእራብ ከ32 እስከ 72 ኪሎሜትር ይርቃል፡፡ ጀበል ዙኩራ ትልቁ ደሴት ወጣገባ ቅርጽ ያለው ነው፡፡
ጀበል ዙኩራ ከሰሜን እስከ ደቡብ 16 ኪሎሜትር የሚረዝም ሲሆን፤ከምስራቅ ወደ ምእራብ 13 ኪሎሜትር ድረስ ይሰፋል፡፡ አል ሀኒሽ አል ሳቅሂር (ትንሹ ሀኒሽ) ፣አል ሀኒሽ አል ከቢር (ትልቁ ሀኒሽ) እና ሱይል ሀኒሽ (በደሴቶቹ መካከል ተበታትነው የሚገኙ አነስተኛ ደሴቶች በደቡብምእራብ እስከ ኤርትራ ባህርዳርቻ ድረስ የተዘረጉ) ናቸው፡፡
ትልቁን ሀኒሽ በኤርትራ ለአጭር ጊዜ ተቆጣጥራ የነበረ ሲሆን፤ የመን ድግሞ ትንሹን ሀኒሽና ዛኩራን ይዛ ነበር፡፡ የደሴቶቹ ስብስቦች እሳተጎመራ የተፈጠሩ ናቸው ፡፡ እነዚህ ደሴቶች በአሳሀብት የበለጸጉና በደሴቶቹ አካባቢዎች በማአድንና በነዳጅ ዘይት ክምችት የዳበሩ መሆናቸው አመላካች መረጃዎች አሉ፡፡
በ1995 መባቻ በትልቁ የሀኒሽ ደሴት የመን-ጀርመን ኩባንያ ጠላቂ ዋናተኞችን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ከፍቶ እንዲያሰለጥን ፍቃድ ተሰጠው፡፡ ኩባንያውን መሳሪያዎች ለመጠበቅ የየመን ወታደሮች መመደባቸውን ተከትሎ፤የየመንን እርምጃ ኤርትራ ተቃውመች፡፡ እ.ኤ.አ በታህሳስ 1995 አመተምህረት በሰሜን ባብኤል መንደብ የመን ከኤርትራ ጋር በትልቁ ሀኒሽ ደሴት ለአጭር ጊዜ ውጊያ አካሄደች፡፡
በሦስት ቀናት ውጊያ ውስጥ የየመን ጦር በኤርትራ ጦር ተሸነፈ፡፡ ወዲያው ወደ ከፍተኛ ቀውስ ያመራው የሁለቱ ሀገራት ጦርነት በባህርና በአየር ኃይሎች የተካሄደ ነበር፡፡ 12 ኤርትራውያንና 15 የመናውያን የተገደሉ ሲሆን፤ኤርትራ 185 የየመን ወታደሮችን በመማረክ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ወዲያው ለቀቀቻቸው፡፡
ኤርትራ በሀኒሽን ደሴቶች ላይ ጥቃት ስትከፍት፤ ኤርትራ በእስራኤል እንደተደገፈች የመን ትከስ ነበር፡፡ የኤርትራ ጦር ኦፕሬሽን በእስራኤል ወታደራዊ መኮንኖች የታገዘ እንደሆነ የመን ስትወተውት ነበር፡፡ የቀድሞ የመን ፕሬዚዳንት አሊ አብደላህ ሳላ ቅርብ ሰዎች እንደተናገሩት ሌተና ኮሎኔል ማይክል ዱማ ጨምሮ ”በርካታ እስራኤላውያን” በጦርነቱ ተሳትፈዋል፡፡
ይህ የየመን ክስ መነሻ በወቅቱ በርካታ በሂብሪው ቋንቋ የተላለፉ ሚስጥራዊ መልእክቶች መጠለፋቸውን ዋቢ አድርገው ነበር፡፡ የመን ይህንን ውንጀላ ግን መደበኛ በሆነ መልኩ ለእስራኤል አላቀረበችም፡፡
የአረብ ሊግ እስራኤል ወታደራዊ ድጋፍ መነሻ እስራኤል ደሴቶቹ ላይ የጦር ሰፈር ለመገንባት ፍላጎት አላት በሚል አውግዞ ነበር፡፡
ሌላው ምክንያት ደግሞ እስራኤል በበኩሏ የመን ይህን ውንጀላ በእስራኤል ላይ ማቅረቧ ወታደራዊ ሽንፈቷን ለመሸፋፈን ወይም የአረብ ሀገራት እንዲያግዟት ብላ መሆኑን በመጥቀስ አጣጥላዋለች፡ ፡ አረብ ሊግ በወቅቱ ኤርትራ በሀኒሽ ደሴቶች ላይ ጥቃት የከፈተችውና የይገባኛል መብት ያነሳቸው በቀይ ባህር ወለል የነዳጅ ዘይት በመኖሩ ይህንን ለመቆጣጠር እንደሆነ ግምቱን አስቀምጦ ነበር፡፡
ኤርትራ ሀኒሽ ደሴትቶችን ለመቆጣጠር ባደረገችው ጦርነት የኢትዮጵያ ስውር እገዛ እንደነበረበት የሚናገሩ አሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በወቅቱ በኤርትራ ላይ የሚደረግ ማናቸውንም ጥቃት በጋራ ለመመከት ዝግጁ መሆኑን የሚጠቁሙ መረጃዎች ይወጡ ነበር፡፡ ይህም ሀገራቱ እንደ ኮንፌደሬሽን አይነት ትብብር ለመፍጠር ውጥን አላቸው የሚሉ ጭምጭምታዎች መነሻ ነበሩ፡፡
ኤርትራ በሀኒሽ ደሴቶች ተዋጊ ጄቶችና ሄሊኮፕተሮች መጠቀሟ ፤ የኢትዮጵያን የአየር ኃይል ንብረቶችና በተወሰነ ደረጃ የቀድሞ የአየር ኃይል አብራሪዎችን ሳትጠቀም አልቀረችም ይባለል፡፡
በነገራችን ላይ የኤርትራ መከላከያ ኃይሎች የኤርትራ አየር ኃይል በቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባል ኮማንደር ሀብተጽዮን ሀደጉ አዛዥነት ኤርትራ ነጻነት በኋላ እ.ኤ.አ በ1994 ዓ.ም እንዲመሰረት መሆኑ ይነገራል፡፡ ሀገሪቱ የሀኒሽ ደሴቶች ጦርነት ባካሄደችበት ወቅት የአየር ኃይሏ ከተመሰረተ አመት አልሞላውም ነበር፡፡
በወቅቱ ኢትዮጵያ በግልጽ ባይሆንም ፤ከኤርትራ ጦር በማገዝ ለወታደራዊ ድሉ አስተዋጽኦ እንደነበራት ይነገራል፡፡ በዚህ ወቅት ኤርትራና ኢትዮጵያ በኮንፌደሬሽን ስለመዋህድ ይደመጥ ነበር፡፡በሀኒሽ ደሴቶች ጦርነት እንዲቆምና ሁለቱ ሀገራት ወደ ድርድር እንዲመጡ በተደረገው መሰረት ታላቁ የሀኒሽ ደሴት ለየመን የተፈረደ ሲሆን፤ በደቡብምእራብ የሚገኙትን የደሴቶቹ አካል እንዲሰጣት ተወስኗል፡፡
ሁሉም ደሴቶች ዋና የነዳጅ ዘይት ማጓጓዣ መርከቦች ቁልፍ መንገድ ላይ ይገኛሉ፡፡ በደሴቶቹ አቅራቢያ የባህርዳርቻዎች የውጭ የነዳጅ ኩባንያዎች እንደ አሜሪካ የሚገኘው አንዳርኮ ፔትሮሊየም ፍላጋ መገኛ ናቸው፡፡ ወደ ምእራብ የሚጓጓዝ ድፍድፍ የነዳጅ ዘይት በነዳጅ ጫኝ ታንከር ወይም ግብጽን ጨምሮ አምስት አረብ ሀገራት በጋራ አዋጥተው ከፐርሺያ ባህረሰላጤ ወደ ሲዊዝ ቦይ ድረስ ያስገነቡት የውስጥ ለውስጥ የነዳጅ ማጓጓዣ ቱቦዎች በደሴቶቹ አካባቢ የተዘረጋባቸው መሆናቸው ቁልፍ ያደረጋቸዋል፡፡
የነዳጅ ቱቦዎች በቀን 2 ነጥብ 5 ሚሊየን በርሜል የነዳጅ ዘይት ያስተላልፋሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት ኤርትራና ኢትዮጵያ የተለያዩ ሀገራት ቢሆኑም፤ ከተለመዱት የምጽዋና የአሰብ ወደቦች ባሻገር ቀድሞ የኢትዮጵያ ይዞታ ስር የነበሩ ስትራቴጂክ ደሴቶች የሚሰፍር የጋራ ጦር ማስፈር የሚያስፈልጋቸው ጊዜ ነው፡፡ በሀኒሽና በራስ ዱሜራ ደሴቶች ኢትዮ-ኤርትራ የጋራ የባህርና የአየር ሀይሎች መገንባት ፤የአፍሪካ ቀንድን ለመቀራመት የሚፈልጉ ኃያላን ሀገራትን መግታት ይችላሉ፡፡ ግብጽን ለሲዊዝ ቦይ የሚመርጧት ምእራባውያን፤ የሀኒሽና የራስ ዱሜራ ደሴቶችን የምትቆጣጠረው ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በጸጥታና በወታደራዊ ትብብር መስራቷ ለህልውናዋ ያስፈልጋታል፡፡
ከአሁን በኋላ ኤርትራና ኢትዮጵያ በቀጠናው ከመቼውም በላይ በትብብር ካልሰሩ በተናጥል ሊጥሏቸው የሚፈልጉ ጠላቶቻቸው በቀላሉ የሚጋለጡበት ዘመን ላይ ደርሰዋል፡፡ የሀኒሽ ደሴቶች ኤርትራ ከየመን ጋር እንድትካፈላቸው ያደረጋት ከኢትዮጵያ ጋር መለያየቷ ሊሆን ይችላል፡፡ በቀድሞ መንግስት የኢትዮጵያ ባህር ኃይል የሚናኝበት ይህ ስትራቴጂክ ስፍራ ኤርትራ የባለቤትነት ጥያቄ ያነሳችው ነባር ይዞታነቱ የኢትዮጵያ ስለነበር መሆኑ አይካድም፡፡
በነገራችን ላይ ብዙ ጊዜ ስለ ኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር ሲነገር ወዲያው የሚመጣው የምጽዋና የአሰብ ወደቦች ማጣትና ማግኘት በኋላ ደግሞ የባድመ ጉዳይ ይሆናል፡፡ የአልጀርሱን ስምምነት መሬት ላይ ለመተግበር ቢሞከር በስም ያልተገለጹ ስትራቴጂክ ስፋራዎችን ሰጥቶ መቀበል ሊፈጥር ይችላል፡፡
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ዳግም በአውሮፓ ጦርነት ለማስቀረት ፈረንሳይና ጀርመን ”ኮል ኤንድ ስቲል ኮሙኒቲ ” ( የብረትና የድንጋይ የጋራ ማህበረሰብ) የፈጠሩበትን ብሎም በሂደት የአውሮፓ ህብረት የተመሰረተበትን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ትብብርና ውህደት ማጤን ያስፈልጋል፡፡
በአፍሪካ ቀንድ ኢትዮጵያና ኤርትራ ዘላቂ ሰላም፣ደህንነትና የኢኮኖሚ ልማት የሚፈጥረው በጋራ ያላቸውን የሰው ሀብት ፣ የተፈጥሮ ሀብቶችና ጆግራፊካዊ ጠቀሜታ ለላቀ የጋራ ጠቀሜታ የሚጋሩበት ሚዛናዊ አካሄድ መከተል ሲችሉ ነው፡፡
በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በህግ ማስከበሩ ዘመቻ ወታደራዊ ትብብር ማድረጋቸው ፤ሁለቱን ሀገራት ለ30 አመታት እንዲዋጉና እንዲለያዩ ላደረጓቸው ባእዳን ” ጥርስ” ውስጥ ገብተዋል፡፡ ሁለቱ በመተባበራቸው በጋራ ቢድኑም፤ ሀይለኛ ጠላቶች የገዙበት ጊዜ ነው፡፡
ከእንግዲህ ወዲያ ኤርትራን ነጥለው ለመምታ የሚነሱትን ኢትዮጵያ በንቃት ካልጠበቀች ፤ ኢትዮጵያን ለማደካም ከውስጥ ኃይሎች ግጭቶች በመቀስቀስ ጦርነቱን እንዲቀጥል መሆኑን ኤርትራን አሳስቧት የበኩሏን ካልሰራች አንድ ላይ ይንኮታኮታሉ፡፡
የዴሞክራሲያዊ ወይም የአምባገነንነት ንጽጽሩ አይጠቅምም፡፡ መንግስታቱ በምርጫ ሆነ ያለምርጫ ስልጣኑን ይቆጣጠሩት ለኃያላኑ ያልተመቸ መንግስትን የ”ሽግግር መንግስት” ብለው የሚጠፈጥፉለት ኃይል መፍጠር አይሳናቸውም፡፡
ያምሆነይህ በኬሚስትሪ ሳይንስ ውስጥ የሁለት ወይም ከዛ በላይ የሆኑ የብረት አይነቶች ቅይጥ (Alloy) የሚፈጥሩት የበለጠ ጥንካሬ መፍጠር ወይም ዝገትን ለመከላከል ነው፡፡ የሁለቱ ሀገራት የተናጥል የህዝብ ቁጥር ፣ የተፈጥሮ ሀብቶች ፣ የሰው ሀብት አቅም፣ ጆግራፊያዊ አቀማመጥ ወዘተ ፍትሃዊ፣ሚዛናዊና በትብብር ቀመር ሳይዋዋጡ በጥንቃቄ አዋህደው ቢጠቀሙበት፤የቀጠናው መሪዎች መሆናቸው አይቀርም፡፡
ሁለቱ ሀገራት የአፍሪካ ቀንድ አዲስ የቀዝቀዛ ጦርነት ፉክክር በጋራና በጥንቃቄ ለራሳቸው ሚጠቅም መልኩ የሚገሩበት ብልህ አመራር መከተል ቀጣዩ ፈታኝ ስራቸው ይሆናል፡፡