“ባልተፈቀደ የደረጃ ስያሜ መጠቀም የተከለከለ ነው!”
የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የደረጃ ስያሜ መመሪያ ማክበርን በተመለከተ የኤጀንሲው ማሳሰቢያ እነሆ።
እያንዳንዱ ተቋም የየራሱ የደረጃ ስያሜ ያለው ሲሆን ዩኒቨርሲቲ፣ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ ኮሌጅ እና ኢንስቲትዩት በሚል የሚገለጽ ነው፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ደረጃ ስያሜ እንዲሁ በዘፈቀደ የሚሰጥ አይደለም፤ የራሱ የሆነ መመሪያ እና ዝረዝር የመመዘኛ መስፈርቶች አሉት፡፡
በደረጃ ስያሜ ግምገማ ወቅት ለአብነት ከሚጠቀሱ መመዘኛዎች ውስጥ ተቋሙ ለምርምርና ጥናት እንዲሁም ለማህበረሰብ አገልግሎት ፖሊሲና ስትራቴጂክ እቅድ አዘጋጅቶ በበጀት አስደግፎ የተገበራቸው ተግባራት እና ውጤቶቹ ይገመገማሉ፤ እንዲሁም የእውቅና ፈቃድ እና ሌሎች መመሪያዎችን አክብሮ እየሰራ ስለመሆኑ፤ ለመምህራኖች እድገትና ለማበረታታት ያለው አሰራርና ውጤቱ፤ የጥራት ማጎልበቻ ስርዓቱና ውጤቱ፣ የማስመረቅ አቅም እና ሌሎች ዝርዝር መመዘኛዎች የደረጃ ስያሜ አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ናቸው፡፡
ማንኛውም ተቋም በደረጃ ስያሜ መመሪያው የሚፈልገውን የደረጃ ስያሜ ለማግኘት በመጀመሪያ ለኤጀንሲው ጥያቄ ይጠበቅበታል፤ ለጠየቀው የደረጃ ስያሜ የተቀመጠውን የመመዘኛ መስፈቶችን አሟልቶ ስለመገኘቱ ኤጀንሲው ተገምግሞ በደብዳቤ በሚገልጽለት የደረጃ ስያሜ ብቻ መጠቀም ይኖርበታል፡፡
ከዚህ ውጪ በከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ያልተፈቀደ የተቋም የደረጃ ስያሜ ተቀባይነት አይኖረውም፤ ባልተፈቀደ የደረጃ ስያሜ የተሰጠ የትምህርት ማስረጃም ህጋዊነት አይኖረውም፡፡
ካለፉት 3 ዓመታት በፊት ኤጀንሲው በነበረበት የክትትል ክፍተት ምክንያት አንዳንድ ተቋማት ከደረጃ ስያሜ መመሪያው ውጪ ኤጀንሲው ያልሰጣቸውን የደረጃ ስያሜ በመጠቀም ራሳቸውን በኢንተርኔት አውታሮች እና በሚዲያዎች ሲያስተዋውቁ የቆዩ ቢሆንም ባሁኑ ወቅት ወደ ህጋዊ ስርዓት ለማስገባት በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
በመሆኑም እስከ ሀምሌ 2013 ዓ.ም.የኤጀንሲው መረጃ መሰረት ካሉት የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ዩኒቨርሲቲ፣ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ ኮሌጅ እና ኢንስቲትዩት የሚል የደረጃ ስያሜ ያላቸው እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲ የሚል የደረጃ ስያሜ ያላቸው እስካሁን 5 ሲሆኑ እነርሱም፡-
- ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ
- ቅድስተ-ማርያም ዩኒቨርሲቲ
- ሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ
- ሐራምቤ ዩኒቨርሲቲ እና
- አድማስ ዩኒቨርሲቲ ናቸው፡፡
እንዲሁም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ስያሜ ያላቸው የግል ተቋማት እስካሁን 5 ሲሆኑ እነዚህም፤
- አልፋ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ
- ኒው ጀነሬሽን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ
- ሸባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ
- ሆፕ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ
- ጌጅ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ናቸው፡፡
የተቀሩት የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኮሌጅ ወይም ኢንስቲትዩት የሚል የደረጃ ስያሜ ያላቸው፡፡
እዚህ ላይ ከተጠቀሰው ውጪ ከደረጃ ስያሜ ውጪ ባልተፈቀደ የደረጃ ስያሜ በሚዲያ ማስታወቂያ ማሰራት፣ በተለያዩ ሰነዶች እና ባነሮች ላይ መጠቀም፤ ማዕተም ማሰራት ወዘተ የተከለከለ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ተቋም ማስታወቂያ ማስነገር የሚችለው በፊት በኤጀንሲው በሚታወቅበት የደረጃ ስያሜ ብቻ ነው፤ በምሩቃኖቹ የትምህርት ማስረጃ ላይም መስፈር ያለበት የተፈቀደው የደረጃ ስያሜ ብቻ ነው፤ ነገር ግን ተቋሙ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ሳይሆን ለተመራቂዎች በሚሰጠው የትምህርት ማስረጃ ላይ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የሚል ስያሜ ከተጠቀመ የትምህርት ማስረጃው ተቀባይነት አይኖረውም፤ ያልተፈቀደ የደረጃ ስያሜ የሚጠቀሙ አንዳንድ ተቋማት ለተገልጋዮች መጉላላት ምክንያት እየሆኑ ናቸው፤ የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫ አገልግሎት ለማግኘት ዜጎች ወደ ኤጀንሲው በሚመጡበት ወቅት በትምህርት ማስረጃቸው ላይ ያለው የደረጃ ስያሜ ያልተፈቀደ ሆኖ ሲገኝ የትምህርት ማስረጃቸው ተቀባይነት ያጣል፤ አገልግሎት ሳያገኙ ለተጨማሪ ወጪና መጉላላት የሚዳረጉበት ሁኔታ በተደጋጋሚ ይፈጠራል፡፡
ለአብነት ያህል ለውጭ ሀገር ጉዞ የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫ እንዲሰጣቸው ወደ ኤጀንሲው በሚመጡበት ወቅት በማስረጃው ላይ ዩኒቨርሲቲ ወይም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በማለት ያልፈቀደላቸውን የደረጃ ስያሜ ተጠቅማው ስለሚሰጡ የት/ት ማስረጃቸው ህጋዊ አይሆንም፤ በዚህ ምክንያት አስቸኳይ የጉዞ ያላቸው ተገልጋዮች ጉዳያቸው የሚስተጓጎልበት ሁኔታ እየፈጠረ ነው፤ በተጨማሪም ኮሌጅ ሆነው ሳለ ራሳቸውን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በሚል የት/ት ማስረጃ በመስጠታቸው በስራ ቅጥር አመልካቾች ላይ ችግር መፍጠሩ እና በሙያ ፈቃድ አሰጣጥም ላይ ተመሳሳይ ችግር ይፈጠራል፡፡
በመሆኑም ሁሉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከዚህ በፊት ለምሩቃኖቻቸው በሰጡት የትምህርት ማስረጃ ላይ ያልተፈቀደ የደረጃ ስያሜ ተጠቅመው ከሆነ ተቀባይነት ስለማይኖረው ከወዲሁ ማስተካከያ እንዲያደርጉ፤ ለወደፊቱም ለተመራቂዎቻቸው በሚሰጡት የትምህርት ማስረጃ ላይም ሆነ ማስታወቂያ ላይ የተፈቀደላቸውን የደረጃ ስያሜ ብቻ የመጠቀም ህጋዊ ግዴታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ኤጀንሲው በጥብቅ አሳስቧል፡፡
ተማሪዎችም በሚመረቁበት ወቅት ከተቋሙ የሚሰጣቸው የትምህርት ማስረጃ ላይ የሚሰፍረውን የተቋሙ የደረጃ ስያሜ የተፈቀደ ስለመሆኑ ኤጀንሲው ለተቋማቱ የሚልክላቸውን ወቅታዊ የእውቅና ፈቃድ ደብዳቤ ወይም በደረጃ ስያሜ መመሪያው መሰረት ተገምግሞ የተሰጠበትን የደረጃ ስያሜ ደብዳቤ በማየት ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ ይችላሉ፡፡
በመሆኑ ከዚህ ውጪ ባልተፈቀደ የደረጃ ስያሜ የተሰጠ የትምህርት ማስረጃ ካለ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡
የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ
ሐምሌ/ 2013 ዓ.ም.