Connect with us

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በማይካድራ የደረሰውን ጅምላ ጭፍጨፋ የተመለከተ ተጨባጭ ማስረጃ አደራጅቻለሁ አለ

ኢዜአ

ዜና

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በማይካድራ የደረሰውን ጅምላ ጭፍጨፋ የተመለከተ ተጨባጭ ማስረጃ አደራጅቻለሁ አለ

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በማይካድራ የደረሰውን ጅምላ ጭፍጨፋ የተመለከተ ተጨባጭ ማስረጃ አደራጅቻለሁ አለ

~ 1 ሺህ 563 ሰዎች በማንነታቸው ምክንያት ሲገደሉ 81 ሰዎች ደግሞ ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፣

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በማይካድራ የደረሰውን ጅምላ የዘር ጭፍጨፋ የሚያጋልጥና ለዓለም አቀፍ መንግስታትና ለሰብአዊ መብት ተሟጋቾች የሚቀርብ ተጨባጭ ማስረጃ ማደራጀቱን ገለጸ።

ዩኒቨርሲቲው ለአምስት ወራት ባካሄደው ጥናትና ምርምር ማስረጃውን እንዳደራጀ አመልክቷል።

በዘር ጭፍጨፋው 1 ሺህ 563 ሰዎች በማንነታቸው ምክንያት ሲገደሉ 81 ሰዎች ደግሞ ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን አረጋግጧል።
የጥናትና ምርምር ቡድኑ መሪ ረዳት ፕሮፌሰር ጌታ አስራደ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የጥናቱ ውጤት ጅምላ የዘር ጭፍጨፋው በማን፣ እንዴት፣ መቼና ለምን አላማና ግብ እንደተፈጸመ በሰውና በሰነድ ማስረጃ ተረጋግጧል።
አሸባሪው ህወሃት በማይካድራና አካባቢው ገዳይ ቡድን በህቡ አደራጅቶ፣ አሰልጥኖ፣ ገንዘብና መሳሪያ አሟልቶ ጅምላ የዘር ጭፍጨፋ ማካሄዱን በጥናቱ እንደተደረሰበት ተናግረዋል።
የጥናት ቡድኑ ባሰባሰበው መረጃ መሰረት የጭፍጨፋው ሰለባ የሆኑ ሰዎች መኖሪያ ቤታቸው ተለይቶ ምልክት እንደተደረገበት፣ መታወቂያቸው እንደተሰበሰበና ስልካቸው ጭምር በግዳጅ እንደተወሰደባቸው ማወቅ ተችሏል።
ከሽብር ቡድኑ ተልእኮ የተሰጠው ገዳይ ቡድን በህቡዕ እርስ በርስ መልእክትና ትእዛዝ የሚቀበልበት የምስጢር ኮድ እንዳለውና መቼ፣ እንዴትና የት ቦታ ላይ የጅምላ ጭፍጨፋውን መፈፀም እንዳለበት መመሪያ የሚቀባበሉባቸው የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች መገኘታቸውን አብራርተዋል፡፡
ገዳይ ቡድኑ ጅምላ የዘር ጭፍጨፋውን የፈፀመው በገጀራና ስለት ባላቸው መሳሪያዎች ቤት ለቤትና በአደባባይ ጭምር መሆኑን ጉዳት ደርሶባቸው በህይወት የተረፉ ተጎጂዎች በሰጡት እማኝነት ማረጋገጥ መቻሉን ገልፀዋል፡፡
በጥናቱ በማይካድራና አካባቢው የቅድመና የድህረ ጅምላ የዘር ጭፍጨፋዎች ዝግጅቶችና ስትራቴጂዎች ምን እንደሚመስሉ እንዲሁም ግንባር ቀደም ተዋናዮችን የሚገልጹ መረጃዎች መሰባሰባቸውን ተናግረዋል።
ከዘር ጭፍጨፋው ባሻገር በአካባቢው በሚኖሩ ብሄር ብሄረሰቦች ላይ ይፈጸሙ የነበሩ የቋንቋ፣ የባሕል፣ የኢኮኖሚና የስነ-ልቦና ተጽእኖዎችና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በጥናቱ ተዳሰዋል።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን ዩኒቨርሲቲው የዘር ጭፍጨፋው ዓለም አቀፍ ወንጀል በመሆኑ ከተለያዩ የትምህርት ክፍሎች የተውጣጡ ምሁራን የተሳተፉበት አንድ የጥናትና ምርምር ቡድን አቋቁሞ ወደ ስፍራው መላኩን ገልጸዋል።
ባላፉት 30 አመታት የአካባቢው ነዋሪዎች ባህልና ቋንቋ እንዲጠፋ የተደረገውን ሴራና እንዲሁም መሰረታዊ የኢኮኖሚ አሻጥሮች በጥናቱ እንዲዳሰሱ መደረጉን አስረድተዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የጥናቱን ውጤት የፌደራል፣ የክልል፣ የዞንና የወረዳ ባለድርሻ አካላትና ማህበረሰቡ እንዲያውቀው ለማድረግ በቅርቡ ብሄራዊ አውደ ጥናት ለማካሄድ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡
አዲስ አበባ ላይ ለዓለም አቀፉ ማህብረሰብና ድርጅቶች፣ ለዲፕሎማቶች ለመገናኛ ብዙሀን አካላትና ለሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎች ዓለም አቀፍ ጉባኤ በማዘጋጀት እውነታውን በመረጃ አስደግፎ ለማቅረብ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡
“ጅምላ የዘር ጭፍጨፋው የሀገር ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ዘር ለይቶ እልቂትና ግፍ የተፈጸመበት ዓለም አቀፍ ወንጀል በመሆኑ የጥናቱን ውጤት በመጽሐፍ መልክ እንዲታተም ይደረጋል” ብለዋል፡፡
በታዋቂና ዓለም አቀፍ ጆርናሎች ጭምር ለህትመት በማብቃት በዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ዘንድ እውነታው እንዲታወቅ ጥረቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡
ድርጊቱ መጥፎ የታሪክ አሻራ በመሆኑ መጪው ትውልድ ትምህርት እንዲቀስምበት ለማስቻል በሙዚየሞች ውስጥ በታሪክነት ተሰንዶ የሚቀመጥበት ሁኔታ እንደሚመቻች ፕሬዚዳንቱ ለኢዜአ ገልጸዋል።

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top