Connect with us

ሾኬላ ዋሻና ፏፏቴ፤ ምድረ ገነት ኮንታ!

ሄኖክ ስዩም

ባህልና ታሪክ

ሾኬላ ዋሻና ፏፏቴ፤ ምድረ ገነት ኮንታ!

ሾኬላ ዋሻና ፏፏቴ፤ ምድረ ገነት ኮንታ!

(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በኮንታ ያደረገውን ቆይታ እየተረከልን ነው፡፡ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ተጉዞ አመያ ከተማ አቅራቢያ የሚገኘውን የሾኬላ ዋሻና ፏፏቴ ያስደምማል ይለናል በተከታዮ ዘገባው፡፡)
(ሄኖክ ስዩም ~ድሬ ቲዩብ)

ወደምሰማው ድምጽ ተጠጋሁ፡፡ ጥቅጥቅ ደኖች ሸለቆ ውስጥ መሽገዋል፡፡ እዚያ ውስጥ ድምጹን እያሰማ ኑልኝ የሚል የውሃ ዜማ ይደመጣል፡፡ መንገዱ ግን ዋዛ አይደለም፡፡ ክረምት ሲሆንና ሲዘንብ ራስን መጠበቅ ግድ ይላል፡፡ አልያ እንደ ወራጁ ውሃ መውረድ ነው፡፡

ስጠጋው ድምጹ ጎልቶ መሰማት ጀመረ፡፡ አሁን ሰማዩ አይታይም፡፡ ደኑ ጥቅጥቅ ብሎ ዋሻ ሰርቷል፡፡ እዚህ የተፈጥሮ ውሻ ውስጥ ሌላ ዋሻ መሆን ይገርማል፡፡ በጥንቃቄ መራመዴን ቀጥያለሁ፡፡ ከፊት የሚቀድሙ የመንደሯ ሰዎች በቆንጨራ መሬት እየጫሩ ደረጃ ቢጤ መቆናጠጫ ያበጁልናል፡፡

በጣም ተጠጋን፡፡ አሁን ድምጹ ጎላ፡፡ መልኩን የከለለን አንድ ግዙፍ ሾላ ዛፍ ነው፡፡ ዛፉን ዞርነው፡፡ ሾኬላ ታየ፡፡ አቤት ውበት፡፡

ሃምሳ ሜትር ከሚሆን ከፍታ ወደ ታች ይወረወራል፡፡ ምስሉ ትዕይንት ነው፡፡ ድምጹ ዜማ፡፡ ቀና ብዬ መምጫውን አየሁ፡፡ ዛፉ ጥቅጥቅ ብሏል፡፡ አንዳች ተአምር ከሰማይ የሚወርድ ይስላል፡፡ ኩልል ያለ ውሃ ነው፡፡ ኮንታ አፈሩን ከጉዞ አድኗል፡፡ ተራሮቹ አረንጓዴ መልበሳቸው ጥቅሙ ወንዞቹ ነጭ ናቸው፡፡ ከከተማ ቧንቧ የጠሩ፡፡

አካባቢው ራሱ ሌላ ተአምር ሆኖብኛል፡፡ ዙሪያውን የተንዠረገጉት ዛፎች ወንዙን ደጀን ሆነውታል፡፡ የሸበቱ ዛፎች ብዙ ዘመን ቆመው ይሄንን ተአምር እንዳዩ ማየት ሳያስፈልግ መረዳት ይቻላል፡፡ ኮንታ ምድረ ገነት፡፡

ከስር ዋሻው አለ፡፡ የፏፏቴ ዜማ ሲያደምጥ የኖረ፡፡ በሚጎን የፏፏቴ ጢስ ራሱን ሰውሮ ዘመኑን የገፋ፡፡ ሾኬላ ዋሻ ይባላል፡፡ የፏፏቴው ስም መጠሪያ ከዋሻው ስም የመጣ ነው፡፡

ዋሻው ፏፏቴውን በሩ ላይ እንደ መጋረጃ ያንዠረገገው መሰለኝ፡፡ ነጭ መጋረጃ፡፡ ግራና ቀኙ ሰፊ ነው፡፡ ፏፏቴው መካከሉ ላይ ይወርዳል፡፡ የውሃው ጢስ ወደ ውጪ እንጂ ወደ ውስጥ አይገባም።

ሁለት ዋሻ እንደሆነ ነገሩኝ፡፡ አንዱ ከሌላው ጋር እስከ 100 ሜትር ርቀት አለው፡፡ የምመለከተው ዋሻ ሦስት ትላልቅና ስድስት ትንንሽ ክፍሎች አሉት፡፡ ስለ ተፈጥሯዊ ዋሻ እያወራኋችሁ ነው፡፡ የዋሻውን ስፋት በተመለከተ የወረዳው ባህል ቱሪዝም መረጃ ግምቱን አስቀምጧል፡፡ ሰማኒያ ሜትር በስድሳ ሜትር እንደሆነ፡፡ ትልቅ ነው፡፡

በራፉ ሦስት ሜትር ይደርሳል፡፡ ከቆምኩበት እስከ ዋሻው አፍ ያለው መንገድ ከበድ ይላል፡፡ በዋሻው የሚገኘው ሦስተኛ ክፍል ሰፊ እና በውስጡም የተለያየ ቅርጽ ያላቸው ትክል ድንጋዮች ይገኙበታል ብለውኛል፡፡ ድንጋዮቹ የተፈጠሩት በውሃ ጠብታ ነው፡፡ የውሃ ጠብታው ተጠራቅሞ ድንቅ ዐለት ሰርቷል፡፡ የዚያን አለት ቅርጽ ተአምር ተርከው አይጠግቡም፡፡
የሾኬላ ዋሻን የተመለከቱ ሳይንሳዊ ጥናቶች ገና ከሀገር ልጅ ባለሙያ ክፍት ናቸው፡፡ ለምሳሌ የተፈጠረበት ዘመን ላይ የታወቀ ነገር የለም፡፡ በንጉሣዊ የአስተዳደር ዘመን የባሪያ ማኖሪያ ነበር የሚለውም ታሪኩ ብዙ ጥናት ይፈልጋል፡፡
ስንመለስ ዳገት ነው የምንወጣው፡፡ ከዚያ ደግሞ ወደ ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ እንሄዳለን፡፡ ጨበራ ለማደር በጊዜ እንመለስ፤

Click to comment

More in ባህልና ታሪክ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top