በኮቪድ የተፈተነውን የቶኪዮ ኦሎምፒክ በቴክኖሎጂ…
የ2020 የቶኪዮ ኦሎምፒክ ይካሄድ ከነበረበት ወቅት አንድ አመት ያክል ዘግይቶ ያለ ተመልካች ሊከናወን ቀናቶች ቀርተውታል፡፡ የቶኪዮ ኦሎምፒክ በተለይ ለሀገራችን ኢትዮጵያ ብሎም ለአህጉራችን አፍሪካ ትልቅ ትዝታ ያለው ነው፡፡ ለዚህም ጀግናው አትሌት ሻምበል አበበ በቂላ ትልቅ ምክንያት ነው፡፡
የኦሎምፒክ ውድድሩ ያለ ተመልካችና በጥቂት የመገናኛ ብዙሃን አማራጮች ብቻ ሊከናወን ቀን ተቆርጦለት ተወዳዳሪዎች ከተለያዩ የአለማችን ክፍሎች ወደ ውድድሩ ስፍራ አምርተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ስፖርታዊ ውድድሮች ያለ ተመልካች ያን ያክል ድምቀት አይኖራቸውም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ተመልካቾች በቤታቸው ሆነው መመልከት ቢችሉም ትክክለኛውን ስሜት ማግኘትና ማጣጣም አይችሉም፡፡ ይህንን ያስተዋሉ የቴክኖሎጂ ሰዎች የውድድሩ ተመልካቾች ከመደበኛ ቴሌቪዥኖች በተሻለ የውድድሩን ድባብና ስሜት ሊያጋቡ የሚችሉ ከፍኛ ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙ ቴሌቪዥኖችን ሰርተው አቅርበዋል፡፡
ከ2008 ጀምሮ የኦሎምፒክ ብሮድካስቲንግ አገልግሎት ውድድሮችን በምስልና ድምጽ በመቅዳት የማሰራጨት ሀላፊነትን ወስዶ እየሰራ ነው፡፡ ነገር ግን በኮቪድ 19 ምክንያት እስካሁን ተጠቅሞት የማያውቀውን የቴክኖሎጂ አማራጭ ለመጠቀም ተገድዷል፡፡
የብሮድካስት ቡድኑ በ2020 የኦሎምፒክ ውድድር 9500 ሰዓታት የሚደርስ የውድድር ቀረጻ ለማድረግ ያቀደ ሲሆን ይህም ከ2016ቱ በ30 በመቶ ከፍ ያለ ነው፡፡ ይህ ቀረጻም የማሰራጨት መብት ለተሰጣቸው በአለም ላሉ የቴሌቪዥን ማሰራጫ ጣቢያዎች ይሰጣል፡፡ የኦሎምፒክ ብሮድካስቲንግ አገልግሎት ስራውን በ1936 በሶስት ካሜራዎች በመታገዝ በቅርብ ርቀት ለሚገኙ ተመልካቾች ብቻ በማሰራጨት ጀምሯል፡፡
የቴሌቪዥን ስርጭት ተቋማት አሁን ላይ ለደንበኞቻቸው ወደ እውነታ የተቃረበ፣ የተሻሻለ የምስልና ድምጽ አቅርቦት (augmented) ስርጭትን ዘመኑ ያፈራውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ለማስተላለፍ እንዳቀዱ ተናግረዋል፡፡ በኦሎምፒክ ብሮድካስት አገልግሎትም በ3ዲ የታገዘ የአትሌቶችን እንቅስቃሴ የሚቀርጽ ቴክኖሎጂን ለመጠቀም ታስቧል፡፡ ይህም በሰው ሰራሽ አስተውሎት የታገዘ በመሆኑ ተመልካቾች ከሁሉም አንግል ምስሎችን እንንመለከቱ ያስችላቸዋል፡፡
የብሮድካስት አገልግሎቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የ4ኬ ምስልን ለመቅዳት ያሰበ ሲሆን ከጃፓን ሆነው ውድድሩን የሚከታተሉ ሰዎች 8ኬ የምስልና ድምጽ ጥራት ባላቸው ቴሌቪዥኖች ውድድሮችን መከታተል የሚችሉበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡
ምንጭ ፡- የኢትዮጽያ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ኢንስቲትዩት