Connect with us

 ድህረ ምርጫ ቀዳሚ ትግባራትን – በነካነካ !

ድህረ ምርጫ ቀዳሚ ትግባራትን - በነካነካ !
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

 ድህረ ምርጫ ቀዳሚ ትግባራትን – በነካነካ !

 ድህረ ምርጫ ቀዳሚ ትግባራትን – በነካነካ !

( ንጉሥ ወዳጅነው – ድሬቲዩብ )

 ስድስተኛው ዙር ብሄራዊ ምርጫ ተስፋ ሰጭ በሆነ ሰላማዊና  አሳታፊ መንገድ ተካሄዶ፣ ድህረ ምርጫ ተግባራት የሚከናወኑበት ወቅት ላይ ነን ፡፡ በብዙዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች የተናጠል ውጤቶች እየታወቁ ሲሆን፣ በቅርቡም ምርጫ ቦርድ በተጠቃለለ አኳኋን መረጃዎችን ጠምሮ አገራዊ አሸናፊዎችን የሚያሳውቅበት ሁኔታም ይጠበቃል ፡፡ 

 በዚህ ጊዚ ነው ማንም ያሸንፍ ማን ፣ ስለአገራችን ፖለቲካዊና ዲሞክራሲያዊ አካሄድ መነጋጋር የሚያስፈልገው ፡፡ ዋስትና ላለውና አስተማማኝ ለሆነ የፖለቲካ መስተጋብር መዘጋጀትም የሚገባው ፡፡ እናም እንደአገር በምንገኝበት ወሳኝ ወቅት ፣ ህጋዊ ውክልና ያለው መንግስት ሲመሰረት የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጣቸውንተግባራት ለመጣቃቀስ እንሞክራለን ፡፡ 

 ከሁሉ ቀድሞ መፍትሄ ማግኘት ያለበት በትግራይ ክልል ከህወሀት መራሹ አማፄ ቡድን ጋር የተጀመረውን ጦርነት የመቆጨት/ማጠናቀቅ ተግባር ሊሆን ይገባል ፡፡ ምክነያቱም በአንድ በኩል ለዘመናት በጦርነትና ሰው ሰራሽ ችግሮች ሲጠበስ የኖረውን የትግራይ ወገን ህዝብ ፈጥኖ ከችግር ማውጣት ያስፈልጋል ፡፡

 በሌላ በኩል በቅርብም ሆነ በሩቅ ያሉ የውጭ ሃይሎች የአገራችንን መንግስት እጅ ለመጠመዘዝና ተፅኖ ለማሳደር የሚሹት በዚሁ ህግ የማስከበር ጦርነት ምክነያት እንደመሆኑ፣ ይህንኑ መከላከል ስለሚያስችል ነው ፡፡ እርግጥ ነው ህግ የማስከበር እርምጃው ያልተፈለገና መስዋእትነት የሚያስከፍል ነው ፡፡ ግን ትግሉ በሰይፍም ፣ በሰላም መድረክም መቋጨት አለበት ፡፡

ሌላቹ ትኩረት የሚሹ ቀዳሚ ጉዳዮች አገር የሚፀናባቸውና  ህዝብም በፍትሃዊነት የሚጠቀምባቸው ህገመንግስታዊ ማሻሻያ ፣ ብሄራዊ ምክክርና እርቅን  …የመሰሉ ተግባራት ናቸው ፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁሉንም የፖለቲካ ሃይሎችና የህዝብ ወኪሎች ባሳተፈ መንገድ ፣ አገርን እያስቀደሙ መምከር ፣ የህግ የበላይነትን ያከበረ የፖለቲካ መስተጋብር መወጠንና የዲሞክራሲ ተቋማትን ይበልጥ ማጠናከር እጅግ አስፈላጊ ናቸው፡፡ 

 በአገሪቱ የተጀመረውን የዲሞክራሲ ምህዳር ማጠናከርና አገረ መንግስቱን በማረጋጋት ወደልማት ተጠናክሮ መግባት ያስፈልጋል ፡፡ ለዚህም የተቋማትን ነፃነትና ገለልተኝነት፣ ብሎም ብቃት ማሰደግ ብቻ ሳይሆን በስብጥራቸው አገራዊ መልክ እንዲኖራቸው ማድረግ መተማመንን ይበልጥ እንደሚያሳድግ መዘንጋት አይገባም ፡፡

መንግስት ለመረጡት ብቻ ሳይሆን ላልመረጡትም የሚያገልግል ፣ አባልና ደጋፊዎቹን ብቻ ሳይሆን ፣ በተቻለ መጠን ተፎካካሪዎችን የሚያካትት ሆደሰፊ መሆንም ይኖርበታል ፡፡

በመንግስት መዋቅር ደረጃ ብዙ ተነግሮላቸው ፣ እስከአሁን እዚህ ግባ የሚባል ስራ ያልሰሩት የእርቅና  ፣ የወሰን ኮሚሽኖች የያዟቸዉ ተግባራት የሚጠብቃቸው ስራ ቀላል አይደለም  ፡፡ በተለይ እንደ ትግራይና አማራ ፣አፋርና አማራ ፣ ሶማሌና አፋር ደቡብና ኦሮሚያ፣ አዲስ አባባና ኦሮሚያ፣ ሐረሬና ኦሮሚያ  … በእንጥልጥል ይዘዋችው ያሉት የወሰንና የባለቤትነት ጥያቄዎች ፈጣን ወይም አዲስ መፍትሄ ማግኘት አለባቸው ፡፡ 

አንዳንዴ እስከ ዞንና ወረዳ እየወረዱ ህዝብ የሚያጋጩ አጀንዳዎችን መድፈን የሚቻልበት አንዱ ጉዳይ ይሄው ነው፡፡

 ሌላውና ወሳኙ ተግባር መልካም አስተዳዳር ማስፈንና ጠንካራ ሲቪል ሰርቪስ የመገንባቱ ስራ ነው፡፡ ከቀድሞ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት እየተንከባለለ የመጣው በየደረጃው ያለ መንግስታዊ መዋቅር አሁንም ብዙ የማያስደስቱ አሰራሮች አሉበት ፡፡ የህዝቡ መንገላታትና ምሬትም ቢሆን ጋብ ብሎ እንደሁ እንጂ ፣ ስርነቀል ለውጥ አልታየበትም ፡፡ 

ለውጥም ተጀምሮ በተለይ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች የመሬት ፣የገቢዎች ፣ የቤትና መሰል ሀብቶች ቅርምት ፣ሙስናና ኢፍትሃዊነት ዜጎችን እያበሳጨ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው ፡፡ አሁን ግን ችግሩን መጋፈጥ ግድ ይላል !!      

 በመሰረቱ ይህን ሰፊና ብዝሀነት የሞላበት አገር ለረጅም ጊዜም ሆነ ለተገደቡ አመታት ለመምራት ፣ በተለይም አሁን ባለው ሁኔታ ወሳኝ የሆኑ የሰላምና የደህንነት ተግባራትን መስቀደምም  የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት የሚሻ ነው ፡፡ 

በመሆኑም መንግስት የታጠቁ ሃይሎችን ትጥቅ ወደ ማስፈታት፣ ብዙሃኑን ህዝብ ወደሰላምና ልማት ፊቱን እንዲያዞር ለማድረግ ዋስትና መስጠት አለበት ፡፡ ለዚህ ሰፊና ትልቅ አደራ እውን መሆን ፣ እንደቀደሙት ጊዜት ፣ በእከክልኝ ልከክልህ እየተሻሹና እየተወሻሹ መቀጠል አይቻልም ፡፡ 

ህዝብ ከትናንት በተሸለ በፍትሃዊነትና በእኩልነት እየተደመጠ ፣ ዘላቂ ጥቅሙ  ሊረጋጋጥ ይገባል ፡፡ ይህ ሲሆን ነው የተደከመበት ምርጫ ፍሬ የሚያፈራው !! 

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top