የሳዑዲ አረቢያ የፀጥታ ሃይሎች ውለታን የመርሳት ልክፍት!!
(ገለታ ገ/ወልድ – ድሬ ቲዩብ )
ያቺ ሰፊ አረባዊት ምድር ሳዑዲ አረቢያ ተብላ መጠራት ከጀመረች እንኳን ገና መቶ አምስት አመቷ ነው ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ አሏህ ነብዩን (ሰዐወ) በመሪነት ባያስነሳላትና ቁርአን አልከሪምን ባያወርድላት ኖሮ ሳዑዲ አረቢያ እንኳን ሊኖሩባት ቀርቶ በአጠገቧ የማያልፉባት ለምንም የማትሆንና ለማንም የማትመች ምድረ በዳ እንደነበረች ነው መረጃዎች የሚያሳዩት ፡፡ ነጋ ጠባ በጎሳ ጦርነት እርስ በርሱ ሲዋጋና ሲገዳደል የሚኖር ዘላን ህዝብ መፈንጫም ነበረች፡፡
የሳዑዲ አረቢያ ምድር ህዝቦች ከዛሬ 75 አመት በፊት ነዳጅ እስከአገኙበት ጊዜ ድረስ በአስከፊ ድህነት ውስጥ የሚማቅቁም ነበሩ፡፡ በየአገሩ ተበታትነው የእለት ጉርስ ፍለጋ መከራቸውን ሲያዩ ኖረዋል፡፡ ለችግረኞቹ የአረብ ህዝቦች አንዷ መዳረሻ ይቺው የአበሻ አገር ኢትዮጵያ ነበረች፡፡
አረቦች በኢትዮጵያ በተሸካሚነት (በኩሊነት)፣ በጋሪ ገፊነት፣ በዳቦ ጋጋሪነት፤ በፓስቲ ጠባሽነትና በሻይ ቤትነት እንዲሁም እስከገጠር ድረስ ዘልቀው ገብተው ሱቅ እያበጁ በቸርቻሪነትና በሚዛን ቀሻቢነት ተሰማርተው ተዳድረዋል፡፡
ከአገራችንም ሲወጡ ከዚህ ያገቧቸውን የእኛን ሴቶችና ልጆቻቸውን እንዲሁም ያፈሩትን ሀብት ይዘው በክብር መሄዳቸውን እናውቃለን፡፡ በዚያን ጊዜ አንድም አረብ የመኖሪያ ፈቃድ አልነበረውም፡፡ ዝም ብሎ መጥቶ ዝም ብሎ ይኖራል፡፡ ባዶ እጁን መጥቶ እዚህ ይከብራል፡፡
ይዳራል ልጅና ሀብት ያፈራል፡፡ የሚጠይቀው የለም፡፡ የሚሠራው ለራሱ ነበር እንጂ ለአበሾች ተቀጥሮ አልነበረም፡፡ታዲያ የትኛውም አረብ ቢሆን በኢትዮጵያ ምድ የደረሰበት ግፍም ሆነ በደል አልነበረም ፡፡
እውነት ለመናገር የኢትዮጵያና የሳዑዲ ግንኙነት የጀመረው ፣ ከቅርብ አስርታት ወዲህ ብቻ ሳይሆን ከጥንት ዘመን አንስቶ ነበር ፡፡ ከሁሉም እስላማዊ የታሪክ ክንውኖች በፊት የሚመዘዝም ነው ፡፡ እስልምና ‹‹ሱኒ›› እና ‹‹ሺአ›› ተብሎ ከመከፋፈሉ በጣም በፊት ፡፡አራቱ ታላላቅ የህዝበ ሙስሊሙ (ኡማ) መሪዎች (አቡከር፣ ዑመር፣ ዑስማን፣ አሊ) እንደመሪ ከመከሰታቸውም በፊት ነው፡፡
እነዚህ ሰዎች እውነታውን እየረሱና ውለታን እየካዱ እንጂ፣ በእስልምና ታሪክ የመጀመሪያው የመስጊድ የሶላት ጥሪ አዋጅ (አዛን) ነጋሪና የነብዩ (ሰዐወ) በጣም የቅርብ ወዳጅ የነበረው ቢላል አበሻ ነበር ፡፡ ‹‹አዛን›› ማለት በጥሩ የድምጽ አወራረድና በርጋታ የሚከተሉትን ቃላት ማወጅ ነው፡፡
የነብዩ (ሰዐወ) ሰሃባዎች (ጓዶች) የነበሩት በትዕዛዙ መሠረት ወደአበሻ ምድር (ወደኛ አገር) ሲመጡ የአበሻው ንጉስ በክብር ተቀብሎ ስለሃይማኖታቸው (እስልምና) ይዘት ጠይቆና ተረድቶ እውነትነቱንም አረጋግጦና ተደስቶ በአገሩ እንደማንኛውም ዜጋ እንዲኖሩ ሊያጠቃቸው የሚነሳ ኃይል ቢኖር እንደሚከላከልላቸው ቃል ገብቶ ያስቀመጣችው እዚሁ እኛው ምድር አልነበረምን ፡፡
ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን ከእኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን ከሌላውም አካባቢ ወደ ሳዑዲ የሚሄዱ ስደተኞችን መግፋት ጀምረዋል ፡፡ እርግጥ ነው አንዳንድ ህገወጥ ስደተኞች የሚጥሱት ህግና ስረአት ሊኖር ይችላል ፡፡ ህጋዊ መንገድ ተከትለው እየሄዱ ያሉ ሰደተኞችንም ጀምሎ ማንገላታትና መግፋት ግን ማንነትን መርሳትና ውለታቢስነት ነው ፡፡
በተለይ በራሳቸው ተፅኖና ጫና በደል የሚያደርሱ ፖሊሶችና አደረጃጀቶቻቸው የተጠናወታቸው ሰድተኛ ጠል ብቻ ሳይሆን ሀበሻ ገፊ አስተሳሳብ ከጊዜ ወደጊዜ መባባሱ ያበሳጫል ፡፡
ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን መኖራቸው ደግሞ ዋነኛ የችግሩ ሰለባዎች የእኛ ወገኖች እንዲሆኑ አድርጎል ፡፡
ተደጋግሞ እንደታዬውም በሳዑዲ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ፣ ህይወታቸው በውጣ ውረድና በእንግልት የተሞላ ሆኗል ፡፡
አንድ ጊዜ ያዝ ፣ሌላ ጊዜ ለቀቅ እያለ ቢሆንም በህገወጥ ስደተኞች መቆጣጣር ስም በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰትና ግፍ የተፈፀመባቸው ኢትዮጵያዊያን ለዚህ አብነት ናቸው ፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ በህጋዊ መንገድ የሄዱና የመኖሪያ ፍቀድ ያላቸው ሳይቀሩ እየተንገላቱና ንብረታቸው እየተዘረፈ መሆኑን ሰምተናል ፡፡ ያሳዝናል!!
ከፖለቲካ ፣ዲፕሎማሲ ግንኙነትና ውቅታዊ የማህበረ -ኢኮኖሚም በላይ ታሪካዊ ዳራ፣ ሃይማኖታዊ ወገንነትን መርሳት ግን መታረም ያለበት ፣ በምድርም ፣በሰማይም ዋጋ የሚያሳጣ ተግባር ነው ከማለት ዝም አንልም ፡፡