Connect with us

እንኳን ዛሬ ጥንትም “ግብፅን ውሃ እናስጠማ “ ያለች ኢትዮጵያ አልነበረችም !!

እንኳን ዛሬ ጥንትም “ግብፅን ውሃ እናስጠማ “ ያለች ኢትዮጵያ አልነበረችም !!
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

እንኳን ዛሬ ጥንትም “ግብፅን ውሃ እናስጠማ “ ያለች ኢትዮጵያ አልነበረችም !!

   እንኳን ዛሬ ጥንትም “ግብፅን ውሃ እናስጠማ “ ያለች ኢትዮጵያ አልነበረችም !!

(ንጉሥ ወዳጅነው~ ድሬቲዩብ)

  ኢትዮጵያ በጥንታዊው ታላቅ ስልጣኔዋ ዘመን የአባይን ውሃ ሙሉ ለሙሉ መዝጋት በምትችልበት ዘመን እንኳ ውሃ ልከልክል ብላ አታውቅም ፡፡ ኢትዮጵያ በሠራዊት ኃይል ጭምር ከግብጽ እጅጉን የበለጠች በነበረችበት ጊዜ ‹‹አባይን ገድቤ የግብጽን ጉሮሮ ልዝጋ›› እንዳላለች ታሪክ ምስክር ነው፡፡ 

 አለቃ ደስታ ተክለወልድ ዘ-ብሔረ ወግዳ ገበታዋርያ በተባለውና በ1928 ዓ.ም. በታተመው መጣፋቸው ገጽ 41 ላይ ይህንኑ የሚያስረግጥ ግጥም እንዳላቸው ማስታወስ ጠቃሚ ነው ፡፡ እንዲህ ይላል፡-

…ያባቶቻችንን ፈረስና ጓዝ

ባህርም አላገደው እንኳን ፈሳሽ ወንዝ

በሰሜን አፍሪቃ ያጤ ዳዊት ጫማ

ሱዳንና ኖባን ሲረግጥ እንደ አውድማ

የግብጽን ጉሮሮ አባይን መዝጋት

በጣታቸው ነበር እንደቀለበት፡፡

 ይህ ከጥንት ጀምሮ ያለው የኢትዮጵያ አቋም ዛሬም ቢሆን የተከበረ ነው፡፡ አገራችን ‹‹አባይን ገድቤ የግብጽን ጉሮሮ እዘጋለሁ›› የሚል ሃሳብ ጥንትም አልነበራትም፣ ዛሬም የላትም ፡፡ ኢትዮጵያ ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጪያ የሚሆን ኃይል እየሰጠ የሚያልፍ ግድብ  ነው እየሰራች ያለችው ፡፡ ይህንንም የታችኛው የተፋሰሱን አገራት አሳምና ፣ መላውን ህዝቧን አነቃንቃ ፣ በሙሉ ቁርጠኝነት ነው የገባችበት ፡፡

 በዚህም ለግብጽ የሚሄደው የውሃ መጠን ትርጉም ባለው ሁኔታ ሳይቀንስ ኃይል አመንጭቶ የሚሄድ ፣ የግብጽን መሰረታዊ ጥቅም የማይነካ፣ ግብፆችን ጉልህ ሥጋት ውስጥ የማይጥል ፕሮጀክት ነው ፡፡ የግብፅ አንዳንድ አጉራዘለል ፖለቲከኞችና አክቲቪስት ተብዬዎች ግን ይህን መሬት ላይ ያለ ሀቅ ሊያምኑ አልቻሉም ፤ አይችሉምም ፡፡

 እርግጥ ነው አባይ ለግብፆች ብቸኛ የውሃ ምንጫቸው ነው፡፡ የከርሰ ምድር ውሃ ሊኖራቸው ቢችል እንኳ ስለእሱ ማሰብ አይፈልጉም ፡፡ አይናቸው፣ ጆሮአቸውና ልባቸው ያለው አባይ ላይ ብቻ ነው፡፡ አባይ ለግብፆች የእለት ጉርሳቸው፣ የአመት ልብሳቸው እንደሆነ የሚረዳው  የኢትዮጵያ አታያይ ግን ትናንትም ሆነ ዛሬ ሊቀዬር አይችልም ፡፡ በፍፁም !!

 የካይሮ ሰዎች ስጋታቸውና  ቅዥታቸው “ ዉሃው ሊነጥፍብን ነው “ ከሚል ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ የቀጠናውን አጠቃላይ የውሃ ሃይል ሚዛን የሚቀይረው ስለሆነ ነው፡፡ አገራችን በተፈጥሮ ሀብቷ በመጠቀም ድህነትን ማዳከም መጀመሯ ፣ ወደ ማያባራ የልማት ፍላጎት ይከታታል ፣ሌሎችንም የተፋሰሱ አገራት ከደበታቸው የድህንት እንቅልፍ ይቀሰቅሳል በሚል ስጋትም ነው ፡፡ 

 እንጂማ አባይ (ናይል) ለግብፃውያን ጌጣቸው፣ ክብራቸው፣ ኩራታቸውና አጠቃላይ ህልውናቸው መሆኑን ብቻ ሳይሆን ፣ የምንሰራው ግድብ ምክነያታዊና ፍታሀዊ አጠቃቀምን ብቻ መሰረት አድርጎ ፣ መሰረታዊ ድርሻቸውን ሳይበድል እየተሰራ መሆኑን ከኢትዮጵያ በላይ በግልፅ ያስረዳ አልነበረም ፡፡ ሳይንሱና ነባራዊ እውነታም ከዚህ ውጭ ድብቅ ነገር እደሌለው የታወቀ ነው፡፡

 ግብፃዊያን የኢፍትሃዊ ፖለቲካ አራማጆችና የቅኝ ግዛት አስተሳሳብ እስረኞች  ግን፣ በብዙ ውሸትና ያልተጋባ ውዥንብር ህዝባቸውን ማደናገር መርጠዋል ፡፡ ኢትዮጵያ ናይልን ልታስቆምብን ነው በሚል ፕሮፖጋዳም አለምን ከማደናገር አልተቆጠቡም ፡፡

ለዚህም ከአሜሪካና አውሮፓ እስከ አረቡ አለም ፣ ከአልም ባንክና የአለም ገንዘብ ድርጅት እስከ አረብ ሊግ ዋትተዋል ፡፡ የአፍሪካ ህብረትና ጎረቤቶቻችንንም አደንቁረዋል ፡፡ እውነት ግን ትመነምናለች እንጂ አትበጠስምና ጠብ ያለላት ነገር የለም ፣አይኖርም ፡፡

 እናም መላው ኢትዮጵያዊያን ፣ በውስጥም በውጭም የለን ሁሉ ከጥንት እስከዛሬ ያለው የማይናወጥ የአገራችን አቋም ሳንጠራጠር መያዝ አለብን ፡፡ በዚያውም ልክም የካይሮ ሰዎችን የማያበራ የተዛባ ትርክት ማጋለጥና ፍርሽ ማድረግ አንዘንጋ፡፡ ያሰብነውን ከማሳካት ግን ከልካይ ሊኖረን አይችልም ፡፡

        በፅናት ታሪካችንን ጠብቀን፣ አዲስ ታሪክ ለስራትም እንትጋ !! 

     

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top