Connect with us

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ለ1442ኛው ዒድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አሕመድ 1442ኛውን የኢድ አል-ፊጥር በዓል በማስመልከት ለመላው ሙስሊም ማኅበረሰብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል
Photo: Social media

ዜና

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ለ1442ኛው ዒድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል

ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ለ1442ኛው ዒድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል

እንኳን ለ1442ኛው ዒድ አል ፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

“ዒድ አል ፈጥር” በቅዱሱ ረመዳን ወር መጨረሻ እና በሻወል ወር የመጀመሪያ ቀን ላይ የሚውል የጾም ወር ማጠናቀቂያ ታላቅ በዓል ነው። ሕዝበ ሙስሊሙ ወሩን ሙሉ በጾምና በስግደት፣ እንዲሁም በመልካም ተግባራት አሳልፎ ከፈጣሪ የመጨረሻውን ምንዳዕ የሚቀበልበት ልዩ ቀን ነው። በዒድ ዕለት ሕዝበ ሙስሊሙ ሰብሰብ ብሎ የዒድ ሶላት ይሰግዳል። 

ይሄም የመሆኑ ምክንያት በመሰባሰብ ውስጥ አንድነት፣ በመሰባሰብ ውስጥ ኅብረት፣ በመሰባሰብ ውስጥ ጥንካሬ መኖሩን ለማመልከት ነው። ለብቻ ከሚሰገደው በላይ በጀምአ መስገድ ከአላህ ብዙ እጥፍ ምንዳዕ እንደሚያስገኝ በእስልምና ይታመናል። “የአላህ እጅ ሰብሰብ ባሉ ሰዎች መሐል ይገኛል” ሲል የእምነቱ አስተምህሮም ያስረዳል።

ሰብሰብ ብሎ ሶላት መስገድ የበዛ በረከት እንደሚያስገኝ ሁሉ፥ ተሰባስቦ ለአንድ ዓላማ መሥራትም በቃላት የማይገልጽ ተአምራዊ ውጤት አለው። በመሰባሰብ ውስጥ መደጋገፍ፣ በመሰባሰብ ውስጥ ብርታት፣ በመሰባሰብ ውስጥ አጋርነት አለና። አንዱ የሌላውን ክፍተት የመሸፈን ዕድል የሚገኘው በዚህ መሰባሰብ ውስጥ ነው። ለብቻ ሶላት ሲሰገድ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ትኩረት ተሰርቆ ለፈጣሪ የሚደርሰው ምስጋና ምሉዕ ስለማይሆን ጭምር ነው የእምነቱ አስተምሮ በመሰባሰብ፣ በጀምአ መስገድን የሚያበረታታው።

የዘንድሮውን ዒድ አል ፈጥር የምናከብረው ሀገራችን ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ በርካታ ፈተናዎች እንደተደቀኑባት እያስታወስን ነው። መዋኛችን ድፍርስ፣ መንገዳችን እሾህ የበዛበት መሆኑን እናውቃለን። በመንገዳችን ላይ እንቅፋቶችን የሚያኖሩ፣ ወደኋላ የሚጎትቱ፣ ተስፋችንን ሳናይ በፊት ተሰብረን እንድንወድቅ መሠረታችንን የሚገዘግዙ ኃይሎች፣ ከውጭም ከሀገር ውስጥም በርትተው የመጡበት ፈታኝ ጊዜ ነው።

ነገር ግን ተገዳዳሪዎቻችን ያልተረዱት አንድ ሐቅ አለ። በፍቅር እንጂ በኃይል እንደማንንበረከክ፣ ለእውነትና ፍትሕ እንጂ ለመደለያ እንደማንገዛ እና ሀገራዊ ክብርና ጥቅምን አሳልፈን እንደማንሰጥ ታሪካችን ምስክር ነው። የማንንም ሐቅ የማንሻ ሕዝቦች፣ የፍቅር እጃችን ብሎ ለሚመጣው እንግዳ አክብረን ተቀባይ፣ ለሚሳደደው መሸሸጊያ ጥላ ስለመሆናችን ከነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) እና ተከታዮቻቸው የተነገረልን የምስክርነት ቃል ከበቂ በላይ ነው። በታሪካችን ውስጥ ያኖርነውን ደማቅ አሻራ ሁሌም ሲያንጸባርቅ ይኖራል። 

እኛ ሌላ ማንም አይደለንም። የእናት አባቶቻችን ልጆች ነን። ቀደምቶቻችን ያቆሙልንን መልካም ስምና ጀግንነት ለማጠንክር እንጂ ለመናድ አልመጣንም። ተገዳዳሪዎቻችን ምንም ያህል ቢለፉ ጸንተን ለመቆም መወሰን አለብን። ክፉውን ጊዜ እንደ ዒድ ሶላት ሰብሰብ ብለን ልንጋፈጠው፣ የአንድነታችንን ልክ አሳይተን ልናልፍ ይገባል። በኅብረታችን የሚገጥሙንን ፈተናዎች እንደ ምንሻገራቸው ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያውያን እድል በእኛው እንጂ በሌላ በማንም እጅ እንዳልሆነ ለዓለም ማሳየት ይኖርብናል።

ውድ ወገኖቼ፣

የእስልምና አስተምህሮ እንደሚገልጸው አንድ ሰው ለራሱ ጥቅም ብቻ ቢኖር ሕይወቱ ትርጉም አይኖረውም። የሚኖርበት ማኅበረሰብ ተርቦ እሱ ጠግቦ ቢውል፤ ጎረቤቶቹ ተረብሸው እሱ ሰላም ቢሆን፣ ሀገሩ ተቸግራ እሱ ቢደላው፣ በዙሪያው ርኩስ ተግባራት በዝተው ስለእሱ ብቻ ቅድስና የሚያስብ ከሆነ ከአላህ ፈጽሞ እዝነትን አያገኝም። 

የእሱ ጻድቅ መሆን ሕዝብና ሀገርን ካላጸደቀ፣ የእሱ ከፍ ማለት ሀገርና ወገንን ከፍ ካላደረገ፣ የእሱ ስኬት ሀገርንና ማኅበረሰብን ስኬታማ ካላደረገ አላህን ማገልገሉ ብቻ ጽድቅ አያስገኝለትም። ይልቁኑም ለራሱ ብቻ የኖረ ሰው ቀድሞውን ባይወለድ እንደሚሻለው የእምነቱ ሊቃውንት ያስቀምጣሉ።

አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታም ለግላችን ሳይሆን ለጋራ ህልውናችን እንድናስብ የሚያስገድደን፣ ከግል ምቾታችን በላይ ለጋራ ደኅንነታችን እንድንተጋ በእጅጉ ግድ የሚልበት ጊዜ ነው። በሕዳሴ ግድብ እና ከፊታችን ባለው ምርጫ ምክንያት ሀገራችን ፈተናዎቿ በዝተው አይተናል። 

እነዚህ ሁለቱን ማሳካት ለእኛ ቀላል የማይባል የስኬት በሮችን እንደሚከፍቱልን እናውቃለን። ምርጫውን በስኬት ማከናወን አዲስ የዴሞክራሲ ምዕራፍ እንደሚከፍትልን ግልጽ ነው። የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅም ግዙፍ የብልጽግና ፋና እንደሚለኩስልን ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ያውቃል። 

ሀገራችን ለዘመናት የተቆለሉባትን ችግሮች ፈቀቅ በማድረግ ከሌሎች ጥገኝነት ነጻ እንደሚያደርገን፣ ብሎም በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ያለንን ተቀባይነት በማሳደግ በኩል ሁለቱ ግዙፍ ፕሮጀክቶቻችን ያላቸው

አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን እኛ ብቻ ሳይሆን የዘመናት ተገዳዳሪዎቻችንም ጠንቅቀው ያውቁታል። ተከታታይ ትንኮሳቸውም ከዚያ የመነጨ ነው።

እነዚህን ትንኮሳዎች በመመከት በኩል ጥቂት የማይባሉ አርቆ አስተዋይ ዜጎቻችን በሀገር ውስጥና በውጭ መድረኮች ትልልቅ ጀብዱዎችን እየፈጸሙ ይገኛሉ። ለጋራ ጥቅማችን ሳይሰስቱ ተሟግተዋል፣ ሐቃችንን ለዓለም ተናግረዋል። 

የእነሱ ትጋት በገንዘብ የማይተመን ጥቅም ለኢትዮጵያ ቢያስገኝም፣ የእነሱ ጥረት ብቻውን ፍሬ እንዲያፈራ ዐውቀን በጉዳዩ ላይ ሌሎቻችንም እንድንረባረብ ይጠበቃል። “ከአንድ ብርቱ ሁለት መድኃኒቱ” እንደሚባለው፣ በሕዳሴ ግድብና በሌሎች ሀገራዊ ጥቅሞቻችን ላይ እንደ ችሎታችን የበኩላችንን ብንታገል ለዘመናት የሀገራችን ችግሮች ፈውስ የሚሆን አቅም መፍጠር እንችላለን።

በቅዱስ ቁርዐን ላይ፣ ‹‹ሁላችሁም በአንድነት ሳትከፋፈሉ እመኑ! አላህ ያደረገላችሁን አስታውሱ፣ ልቦቻችሁን የሰበሩ ጠላቶቻችሁ ቢሆኑም እንኳ በአላህ ፈቃድ ወንድም ሊሆኑዋችሁ ይችላሉ›› በማለት በአማኞች መካከል አንድነትንና ፍቅርን፣ የእርስ በርስ መረዳዳትን እና መደጋገፍን አስፈላጊነት በደማቁ ሠፍሯል። እያንዳንዳችን የተለያየ የፖለቲካ እምነት ሊኖረን ይችላል። 

ያለችን ግን አንድ ሀገር ናት። የተለያየ አመለካከት እናራምድ ይሆናል። ያለን ግን፣ አንድ ሕዝብ ነው። ችግራችንም አንድ ነው – ድህነት እና ኋላ ቀርነት! ምንም ትልቅ ታሪክ ቢኖረን፣ ምንም ትልቅ ሕዝብ ቢኖረን በኢኮኖሚ፣ በዴሞክራሲ፣ በቴክኖሎጂና ጥቂት በማይባሉ ሌሎች የሥልጣኔ ዘርፎች ከኋላ ተከታዮች መካከል የምንመደብ ነን። ይሄንን ኋላ ቀርነታችንን ለማሸነፍ መጀመሪያ እርስ በእርሳችን እንዋደድ፣ ሀገራችንንም እናስቀድም። እርስ በእርስ ስንተሳሰብና ሀገራችንን መውደድ ስንጀምር እምነታችንም የበለጠ ሙሉ ይሆናል። 

ነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) በአንድ ሐዲሳቸው፣ “ለሀገርህ ያለህ ፍቅር፣ የእምነትህ አንድ አካል ነው” ብለው እንደ ነበረ ማስታወስ ተገቢ ነው። በሌላም ጊዜ፣ ነቢዩ ሙሐመድ (ሰዐወ) “ድንበር ላይ እያሉ፣ በእንቅልፍ ሳይሸነፉ ሀገርን አላህ በሚወደው መንገድ መጠበቅ፣ ከሁሉም ምድራዊ ጸጋዎች የላቀ ጸጋ ነው” ስለማለታቸውም፣ የእምነቱ ሊቆች ያስተምራሉ።

በዒድ አል ፈጥር በዓል ዋዜማ ላይ ሆነን ስለ ምሕረት፣ ስለ ይቅርታ እና ስለ ፍቅር እንጂ፣ ስለ ጠብና ጥላቻ ማሰብ ያስቸግራል። ቀጣይ ጊዜያትም ስለ አንድነት እንጂ፣ ስለ መለያየት የምንዘምርባቸው ጊዜያት እንደማይሆኑ ተስፋ አደርጋለሁ። በተቀደሰው የረመዳኑ ወር ለሀገራችሁ ጸጋና በረከት፣ ሰላምና ፍቅር እንደ ጾማችሁና እንደ ጸለያችሁ ሁሉ፥ በክብረ በዓሉም፣ ከዚያ ወዲያ ባሉት ቀናትም ለሀገራችንና

ለሕዝባችን ዱዐ ማድረጋችሁን እንድትቀጥሉ በትሕትና እጠይቃለሁ። በዚህ ጊዜ ክፋትን አርቀን መልካምነትን፣ ጠብና ጥላቻን ንቀን በምትኩ እርቅና እዝነትን በሀገራችን ብናነግሥ ምድራዊ ረድኤቶች ብቻ ሳይሆን ሰማያዊ ምንዳዎች በዝተው እንደሚጠብቁን አልጠራጠርም።

ጠብን ለሚዘሩ፣ ከሌሎች ወንድም እኅቶቻችን ጋር ግጭት ለሚጠነስሱ፣ ቁስላችንን በማከክ ለሚያደሙ ዕድል አንስጣቸው። እኛ ከፍቅር እነርሱ ከጠብ፣ እኛ ከአንድነት እነርሱ ግን ከመለያየት፣ እኛ ከድልድይ እነርሱ ግን ከአጥር፣ እኛ ከሀገር እነርሱ ግን ከመንደር እንደምናተርፍ አንርሳ። ለዛሬ ብለን ነገን ከምናበላሽ፣ ለነገ ስንል ዛሬን እንሠዋ። 

የሰላም፣ የደስታ፣ የተስፋና የበረከት ዒድ እንዲሆን ተመኘሁ።

ዒድ ሙባረክ!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትሩር!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ግንቦት 4፣ 2013 ዓ.ም

 

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top