Connect with us

ምርጫ ቦርድ አብንን ጨምሮ ህግና ሥርዓትን እየጣሱ ነው ያላቸውን ፓርቲዎች አስጠነቀቀ

ምርጫ ቦርድ አብንን ጨምሮ ህግና ሥርዓትን እየጣሱ ነው ያላቸውን ፓርቲዎች አስጠነቀቀ (የቦርዱ መግለጫ እነሆ)
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ዜና

ምርጫ ቦርድ አብንን ጨምሮ ህግና ሥርዓትን እየጣሱ ነው ያላቸውን ፓርቲዎች አስጠነቀቀ

ምርጫ ቦርድ አብንን ጨምሮ ህግና ሥርዓትን እየጣሱ ነው ያላቸውን ፓርቲዎች አስጠነቀቀ (የቦርዱ መግለጫ እነሆ)

የምርጫ ህጉን፣ የምርጫ ዘመቻ መመሪያን የሚተላለፉ ንግግሮችን አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተሰጠ መግለጫ

እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ በ6ተኛው አገራዊ ምርጫ ሂደት ተግባራት መካከል ትገኛለች። የምርጫ ሂደት ከፍተኛ እንቅስቃሴ፣ ፉክክር እና ክርክር እንደሚኖረው ይታወቃል። በዚህም መሰረት የፓለቲካ ፓርቲዎች በነጻ የአየር ሰአት፣ በአደባባይ ቅስቀሳዎች እንዲሁም ደግሞ በምርጫ ክርክሮች እየተሳተፉ እንደሆነ ይታወቃል። 

ሰሞኑን በአማራ ብሔራዊ ክልል የተለያዩ ትእይነተ ህዝቦች መከናወናቸው ይታወቃል። የብልጽግና ፓርቲ ለቦርዱ በላከው የቅሬታ ደብዳቤ ሰልፎቹ በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ መጠራታቸውን እና በነዚህም ሰልፎች የብልጽግና ፓርቲ ቢልቦርድ እና ባነሮች መቀደዳቸውን ገልጾ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድለት ጥያቄ አቅርቧል።

ቦርዱም በዚህ አቤቱታ መሰረት በማድረግ ሁኔታውን መርምሯል። ብልጽግና ፓርቲ ባቀረበው አቤቱታ ላይ አብን ለሰልፎቹ ጥሪ ማድረጉን ቢገልጽም በተያያዘው ደብዳቤም ሆነ በቀረቡት ማስረጃዎችም ሆነ ቦርዱ ባከናወነው የሚዲያ እና የማህበራዊ ሚዲያ ማጣራት ሰልፎቹ በአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ መጠራታቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ማግኘት አልቻለም። 

በዚህም የተነሳ ሰልፎቹ ከምርጫ ወይም ከፓለቲካ ፓርቲዎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስላላገኘባቸው በተከናወኑት ሰልፎች ላይ የተንጸባረቁ ሃሳቦች፣ መፈክሮች እና ተያያዥ ጉዳዮችን መመርመር አላስፈለገውም። ነገር ግን ሁነቶቹን አስመልክቶ በሚዲያ እና በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጩ ከሰልፉ ጋር የተያያዙ የፓለቲካ ፓርቲዎች እና እጩዎችን እንቅስቃሴዎችን ክትትል ስራ አከናውኗል።

በዚህም መሰረት

  1. የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሰልፎቹን ተከትሎ ባወጣቸው መግለጫዎች ጥላቻ አዘል ንግግሮችን፣ ግጭትን ሊያባብሱ የሚችሉ አገላለጾችን የሚጠቀሙ ተከታታይ መግለጫዎችን በማውጣት ከምርጫ ፉክክር መንፈስ እና ስነምግባር ውጪ የሆኑ እና በህግ የተቀመጡ በምርጫ ወቅት ተቀባይነት የሌላቸው አገላለጾችን (ንግግር) ተጠቅሟል። ከነዚህም መካከል

ፓርቲው፤

ሚያዝያ 12 ቀን 2013 ዓ.ም

በይፋዊ ፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ

“የኢሕአዴግ አማራ ጠል ትርክት እና የዚሁ ውሉድ የሆኑ የጥላቻ ፖሊሲዎች፣ አሰራሮች፣ ሕግጋትና መዋቅሮች ቀጥተኛ ወራሽ የሆነው ፋሽስታዊ ተረኛ ኃይል በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች….. “  የሚል በተፎካካሪ አካላት ላይ የሚደረግ ጥላቻን ያዘለ፣ ግጭት ቀስቃሽ የሆነ እና ሰብእናን የሚነካ ንግግር፤

ሚያዝያ 11 ቀን 2013 ዓ.ም

“በአጠቃላይ በአማራ ሕዝብ ላይ ባልተቋረጠ መልኩ የሚፈፀሙት መንግስት መራሽ የዘር ፍጅቶች «በገለልተኛ ኮሚሽን» በጥልቀት ተጣርተው ….. “ የሚል ግጭትን የሚያነሳሳ ትክክለኛነቱ ያልተረጋገጠ ክስ 

ሚያዝያ 10 ቀን 2013 ዓ.ም 

“መላው የአማራ ሕዝብም የተከፈተበትን አጠቃላይ የኅልውና አደጋ በመገንዘብ እና ለደኅንነቱ የሚያስብለት መንግስት እንደሌለው በመረዳት ራሱን የመከላከል ተፈጥሯዊ መብቱን እንዲሰራበት አብን በአጽንዖት ያሳስባል።”  የሚል ሃይል መጠቀምን እና ግጭትን የሚያነሳሳ ንግግር  ሲያስተላልፍ ቆይቷል። 

በእነዚህ አገላለጾችም በየኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ስነምግባር አዋጅ 1162/20111 አንቀጽ 132 ንኡስ አንቀጽ 2 ሀ እና ለ ላይ የተቀመጡትን ማንኛውም ውድድር ውስጥ ያለ አካል “ ግጭት ቀስቃሽ የሆነ ወይም የግል ስብዕናን የሚነካ ቋንቋ ማስወገድ አለበት እና “በማንኛውም መልኩ ለአመጽ የሚጋብዝና በግለሰቦች ወይም ቡድኖች ላይ ስጋትን የሚጭር የቋንቋ አጠቃቀም ማስወገድ አለበት “ የሚሉትን ድንጋጌዎች ባወጣቸው መግለጫዎች ጥሷል።

ከዚህም በተጨማሪ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ስላለው የቋንቋ አጠቃቀምን የሚደነግገው የምርጫ ስነምግባር መመሪያ አንቀጽ 20/8  ላይ የተጠቀሰው “ የምርጫ ውድድር ቅስቀሳ በሚያደርግበት ጊዜ በማንኛውም ሰው ላይ ጥላቻን ወይም የሀይል ተግባር እንዲፈጸም የሚያነሳሳ ንግግር ወይም ፅሁፍ በበራሪ ወረቀት፣ በፖስተር ወይም በፎቶግራፍ ከማስተላለፍ መቆጠብ አለበት” የሚለውን ድንጋጌ ተቃራኒ የሆኑ መግለጫዎችንም አውጥቷል። 

በመሆኑም እነዚህ መግለጫዎች በምርጫ ዘመቻ መካከል መደረጋቸው የምርጫውን ሰላማዊነት ከመጉዳቱም ባሻገር ያልሰለጠነ ፉክክርን ያበረታታል ይህም ቦርዱን በእጅጉ አሳስቦታል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፓርቲው ከዚህ አይነት ተግባር አንዲቆጠብ በአጽንኦት እያሳሰበ ተመሳሳይ መልእክቶች ስርጭት የሚቀጥል ከሆነ እጩ አስከመሰረዝ የሚደርስ አስተዳደራዊ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ያሳውቃል።  

  1. በሌላ በኩል በዚሁ ሁነት ዙሪያ ንግግር እና መግለጫ የሰጡ ኢዜማ፣ ብልጽግና፣  ኦፌኮ እና ሌሎች ፓርቲዎችን እና እጩዎች ንግግሮችን ላይ ክትትል አድርጓል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎች በምርጫ ህጉ፣ በምርጫ ዘመቻ ስነምግባር ደንቡ እንደሚገዙ እየታወቀ በይፋዊ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸው ጥላቻን ያዘሉ ንግግሮችን እንዳስተጋቡ ቦርዱ አስተውሏል።  የብልጽግና ፓርቲ እጩ እና ስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ታዬ ደንደአ በሚያዝያ 12 ቀን 2013 ዓ.ም በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በይፋ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን ሲገልጹ

‘’ዋነኛዉ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ካንሰር የሆነዉ አብን ትላንት ባህር ዳር ላይ …” 

በሚል አገላለጽ የተጠቀሙ ሲሆን ፓለቲካ ፓርቲውን

“ …..ወንድማማቾችን ያገዳደለዉ ራሱ አብን መሆኑን በትክክል ይረዳል… “ በማለት ያልተረጋገጠ ክስም አቅርበዋል።   

ይህም ከተወዳዳሪ እጩዎች የሚጠበቀውን “ ግጭት ቀስቃሽ የሆነ ወይም የግል ስብዕናን የሚነካ ቋንቋ ማስወገድ አለበት እና “በማንኛውም መልኩ ለአመጽ የሚጋብዝና በግለሰቦች ወይም ቡድኖች ላይ ስጋትን የሚጭር የቋንቋ አጠቃቀም ማስወገድ አለበት “ የሚሉትን ድንጋጌዎች የጣሰ ነው። በተለይ እጩዎች በመሰል ንግግሮች የምርጫ ሂደቱን ስጋት ላይ መጣል አግባብ አለመሆኑን መረዳት እንደሚገባቸው ቦርዱ በአጽንኦት ለመግለጽ ይፈልጋል።

በመሆኑም እጩዎች በግልም ሆነ በፓርቲ የሚንቀሳቀሱበት ወቅት መከተል ያለባቸውን ስነምግባር ደንቦች ተከታትለው እንዲያስፈጽሙ እያሳሰበ ተመሳሳይ ጥሰት በሚፈጽሙ እጩዎችም ላይ አስተዳደራዊ እርምጃዎቸን እስከመውሰድ ሊደርስ እንደሚችል ያሳውቃል።

  1. በተጨማሪም በማህበራዊ ሚዲያ የተሰራጩ ምስሎች እና ቪዲዮዎች እንደሚያስረዱት በብልጽግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ባነሮች ተቀደዋል። ይህ ተግባር በማንም አካል ቢፈጸም በምርጫ ህጉ 1162/ 2011 መሰረት የምርጫ ወንጀል ነው። ዜጎች በተለያየ መልኩ ሀሳባቸውን በሚገልጹበት ወቅት የምርጫ ሂደቱን ከሚያውኩ የስነምግባር ጥሰቶች እና ተመሳሳይ ወንጀሎች እንዲቆጠቡ፣ ፓርቲዎችም እጩዎቻቸው አባላቶቻቸው እና ደጋፊዎቻቸው በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲንቀሳቀሱ እንዲያስተምሩ እና እንዲያሳስቡ ቦርዱ ያስገነዝባል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ

ሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top