Connect with us

የፖለቲካ ደህንነቱ ጋሻ አይውሸልሸል  !

የፖለቲካ ደህንነቱ ጋሻ አይውሸልሸል !
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

የፖለቲካ ደህንነቱ ጋሻ አይውሸልሸል  !

የፖለቲካ ደህንነቱ ጋሻ አይውሸልሸል  !

(ንጉሥ ወዳጅነው ~ድሬቲዩብ)

   ታላቋ አገር አሜሪካ ከራሷ አልፋ ለአለም የተረፈችው ወይም በቀላሉ አትሸነፍም ፣ አትደፈርም የምትባለው የዳበረ ኢኮኖሚ ስላላት ብቻ አይደለም ፡፡ ወይም በተፅኖ ፈጣሪው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ ፣ በምርምርና እውቀት ልህቀቷ ፣ አልያም በህዝብ ብዛቷ አይደለም ፡፡ 

ከዚያ ይልቅ ጠንካራ የመከላከያ ፣የደህንነትና የፖሊስ መዋቅር ብቃትና ተመጋጋቢ የእዝ ሰንሰለት መገንባቷ፣ ብሎም በአገር ህልውና መደራደር ስለሌለ ነው ይላል፡፡  የDaniel Chernilo ፣ “A Social Theory of the Nation-State The political forms of modernity beyond methodological nationalism”  የሚለው መፅሃፍ ፡፡ 

 በአንድ አገር ውስጥ የፖለቲካ ደህንነት  /Political Security/ የሚገነባው አንድም ህዝቡ በእኔነት ስሜት የተቀበለውና በጋራ የሚጠብቀው መንግስታዊ ስረአት ሲኖር እና/ወይም የተጠናከረ የህግ የበላይነትን ማረጋጋጥ የሚችል የፀጥታና የፍትህ መዋቅር ሲገነባ ነው ፡፡ በመሰረቱ የፖለቲካ ደህንነት ከወታደራዊ፣ኢኮኖሚዊና ማህበራዊ ደህንነት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው ፡፡ ከገለልተኛ፣ ተአማኒትና ብቃት ያለው የፍትህ መዋቅር ጋርም ይያያዛል  ፡፡

 ብሄራዊ /ማዕከላዊ/ መንግስትን፣የክልል መስተዳዳሮችን፣ብሄር- ብሄረሰብና ህዝቦችን፣ የሃይማኖት ተቋማትን፣ የመንግስታት ስርዓት አደረጃጀቶችን ፣የፖለቲካ ጠቀሜታ ወይም አስፈላጊነት ያላቸው ቡድኖችን ሁሉ የሚመለከት ዘርፍ መሆኑም የሚዘነጋ አይደለም ፡፡ 

በአገራችን በተለይም ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ የአገረ መንግስቱን የፖለቲካ ደህንነት እያናጋ፣ህዝብ እያተራመሰ በቀውስ ላይ ቀውስ እየደቀነ ያለው ችግር የሚመነጨው ከዚህ የተቀናጀና ጠንካራ የፀጥታ ሃይል ስምሪት መታጣትና የህግ የበላይነት አለመረጋጋጥ ጋር ይያያዛል የሚሉ ብዙዎች ናቸው ፡፡ ስለሆነም የችግሩን መንስኤ በፀረ ሰላም ሃይሎች ሴራ ብቻ ማሳበብ አያወጣም፡፡ 

 የፖለቲካ ደህንነት ዋስትናውም ሆነ የአገር ሉአላዊነት ምሰሶና ጋሻው የፀጥታ፣ መከላከያና ደህንነት ሃይሉ ነው ፡፡ ህዝቡንም ቢሆን አደራጅቶ በነቃ መንገድ ለሰላምና ደህንነት ዘብ ማድረግ የሚችለው ይሄው ነው ፡፡ አሁን ባለው የአገራችን ሁኔታ ግን ይህን ተግባር በተቀናጀና ማእከላዊ በሆነ የእዝ ጠገግ ፣አፍ ከልብ ሆኖ የሚያከናውን አሰራር አልታዬም ፡፡ 

ያማ ቢሆን በጠራራ ፀሃይ የታጠቀ ሃይል አንዴ ሳይሆን በተደጋጋሚ ንፅሁንን እየፈጀና የአገር ሀብት እያወደመ ሊንቀሳቀስ ባልቻለ ነበር ፡፡ የትኛውም ጥፋት ከመድረሱ በፊት የደህንነት ትንበያና ፈጥኖ የመድረስ ሙከራው ህዝብን በታደገም ነበር ፡፡ የክልሎች ትከሻ መለካካትም አደብ እየያዘ በመጣ ነበር ፡፡ 

 በእርግጥ አገራችን ጦርነትንና ግጭትን ማስቀረት የሚችል፣ የአገር ሉአላዊነት የሚጠብቅ ፣ከራሳችን አልፎ ለጎረቤት አገሮች አጋርነት ያለው ፣ በህዝብ የታመነና በዲሲፒሊን የሚመራ ጠንካራ መከላከያ ሰራዊት አላት ፡፡ በፌደራል ደረጃ ያለው የፖሊስ ሃይልም በሰላምና ደህንነት ተልእኮው ብዙ ግዳጆችን እየተወጣ ያለ ነው ፡፡ 

በየክልሉ ያሉ የፖሊስ ሃይሎቻችንን (በተለይም የልዩ ሃይሎች) አደረጃጃት ግን ከዘውግ ፖለቲካ አዙሪት ተላቆ ፣ለአንድ ሉአላዊት አገርና ለመላው ህዝብ የወገነ መሆኑ በጥብቅ መረጋጋጥ አለበት ፡፡ይህ ካልሆነ መከላከያና ፌደራል ፖሊስ በስንቱ ጉራንጉር ሁሉ እየገቡ  ወንጀለኞችን ሊከላከሉ ይችላሉ !?

 ሲተች በቆየውና ከለውጡ በፊት በነበረው የኢህአዴግ መንግስት እንኳን የአሁኑ አይነት አሰቸጋሪ የሰላም መደፍረስና የህዝብ ዋስትና ማጣት ጎልቶ አልታየም ፡፡ 

ለዚህ ደግሞ  የፀጥታና የደህንነት ሃይሎች ከፌደራል እስከ ክልል በጠንካራ ዲሲፕሊንና ከክልል አጥር በወጣ መንገድ አገረ መንግስቱን እያገለገሉ ስለነበር ነው፡፡ ህዝቡም ቢሆን በአንፃራዊነት  በተሟላ መንገድና በአንድ ልብ ለአካባቢው ሰላምና ደህንነት  የሚቆምበት የተሳትፎ ጅምር ነበር ፡፡ ቢያንስ እሱን እውን ማድረግ እንዴት አይቻልም!! 

 አሁንም ባለተረጋጋውና ባልሰከነው የአገራችን ፖለቲካ ላይ ፣ የፖለቲካ ደህንነቱ ዋስትና የተባለው መንግስታዊ ክንፍ (ፀጥታና የፍትህ መዋቅር) ከመውሸልሸል ሊወጣ ይገባል፡፡ በጠንካራ ማእከላዊ እዝና መደማማጥ አገርን ከስጋት እንዲያወጣም  አደራ አለበት ፡፡ 

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top