የዓለም ዲፕሎማሲ ማዕከሏ – አዲስአበባ !
(ንጉሥ ወዳጅነው)
በዓለም ላይ ካሉ አስተማማኝ፣ ተመጣጣኝ፣ ተወዳጅና ተመራጭ ከተሞች መካከል ለዲፕሎማሲ ከተማነት በ3ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ከተማ የኛይቱ አዲስ አበባ ናት ፡፡ በዲፕሎማቶች መቀመጫነት፣ በኤምባሲና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች መናኸሪያነት፣ በአንደኛነት የምትመራው ኒውዮርክ የተባለችው አሜሪካዊት ከተማ ስትሆን ሁለተኛዋ ብራሰልስ ናት፡፡
አዲስ አበባ በህዝብ ስብጥሯ ትንሸዋ ኢትዮጵያ ከመባሏ ባሻገር ፣ ኢትዮጵያን በ3ኛ ደረጃ እንድትገኝ አስችላታለች፡፡አዲስ አበባ አጠቃላዩን የኢትዮጵያ ገጽታ ይበልጥ ፈክቶ እንዲታይም አድርጋለች፡፡ የአለም ታላላቅ አገሮች ብቻ ሳይሆኑ ‹ትናንሽ› የሚባሉ አገራትም በአዲስ አበባ ውስጥ ከ116 በላይ ኤምባሲያቸውና ቆንስላ ፅህፍት ቤታቸው አሉ ፡፡
አዲስ አበባ የዲፕሎማቶች መኖሪያ ብቻ ሳትሆን የበርካታ አለምአቀፍ ስብሰባዎች፣ ኮንፈረንሶች፣ ወርክሾፖች የሁለትዮሽና የሶስትዮሽ ግንኙነት፣ ንግግሮች፣ የንግድ፣ የጤና፣ የልማት፣ የኢንቨስትመንት፣ የሰላምና የፀረ-ሽብር ተቋማት መወያያ መድረክ ሆና መቆየቷን አንዘነጋውም ፡፡ መትጋት የሚስፈልገውም ይሄ ጅምር እንዳይዳከም ነው !
በተለይ ካለፉት ሶስት አስርት ወዲህ ጽህፈት ቤታቸውን ሌላ አገር ያደረጉ አህጉራዊ ድርጅቶች ለስብሰባ የሚመርጡት አዲስ አበባን ነው፡፡ ሌላ አፍሪካ አገር ውስጥ ሊካሄድ የነበረ ስብሰባ በማንኛውም ምክንያት የስብሰባ ቦታ ለውጥ ቢያደርግ የሚመጣው ወደ አዲስ አበባ ነው፡፡ የምስራቅ አፍሪካ የሰላም አስከባሪ ኃይል መምሪያና የስልጠና ማዕከል ያለው አዲስ አበባ ነው፡፡ ዛሬ የአፍሪካ ህብረት ጽህፈት ቤት ከአዲስ አበባ እንዲነሳ የሚጠይቅ ድምጽ የለም፡፡
ይህ አለምአቀፍ ድል የተገኘው በመንግስትና ህዝብ የዘመናት የተቀናጀ ጥምር ጥረት ነው፡፡ በቀጣይም መልካም አጋጣሚያችንን አጠናክሮ ለመመንደግ የሰላምና ደህንነት ጥበቃ አስተማማኝነት ቅድሚያ ሊሰጠው ግድ ይላል ፡፡ ሰላም ከሌለንና ራሳችንን ከውጭና ከውስጥ ቀጥተኛና የእጅ አዙር ጥቃት መከላከል ካልቻልን አንድም ዲፕሎማት ፊቱን ወደ እኛ ሊያዞር እንደማይችል መረዳት ይገባል ፡፡ይሄ ደግሞ እንደአገርም ሊታሰብበት የሚገባ ነው!!
ከዚህ ቀደም እንደ አልሸባብ ያሉና በውስጥ ያሉ ሽብርተኞችን አደብ እንዲገዙ (ስርዓት እንዲይዙ) ማድረግ ባያችል ኖሮ አንድም ስብሰባ በአገራችን አይካሄድም ነበር ፡፡ የሆቴል ኢንዱስትሪው ባይስፋፋ፣ የቱሪዝም መዳረሻዎች ባይጠናከሩ፣ባህላችንን ለመላው አለም ለማስተዋወቅ ባይሰራ ማን ዞር ብሎ ያየን ነበር?
አሁንም ትኩረት ሰጥቶ በመረባረብ ከዲፕሎማሲ ማእከሏ መዲናችን የሚገኘውን ቱሩፋት በፍትሃዊነት መካፈል ሲገባ፣በማያስጨንቀን የመንደር ትርክት ልናዋርዳት መፈለጋችን መቋጨት ነው ያለበት ፡፡ ይቺን ታላቅ የዲፕሎማሲ መዲና ባልተገባና በተዛባ ትርክት የእኔነች/ ያንተ አይደለችም እያሉ ጊዜ ማባከን መክሊቷን እንደመጣል ይቆጠራል ፡፡ መዲናዋ የሁላችንም የጋራ አሻራ ያረፈባት፣ ከኢትዮጵያዊያን አልፋ በአለም ዲፕሎማቶች የታጨች ሆና በመንደር መባለት አሳፋሪ እውነት መሆኑ መረዳት ነው ያለበን ፡፡
ትናንትም ቢሆን መዲናችን ከአለም ከተሞች ሁሉ ፀዱና የደመቀች በመሆኗ ሳይሆን ፣ ማንኛውም ዲፕሎማት ያለምንም ስጋት እንደልቡ የሚዘዋወርባት፣አፈናና እገታ የሌለባት፣በአንፃራዊነት ሌባ የማያሰጋባት አዲስ አበባ ስላለችን ነው የተፈለግነው የሚለውን ጭብጥ መዘንጋት አይገባም ፡፡ ስለሆነም ፀጥታዋ ሲደፈርስም ሆነ ቀስ በቀስ እያቆጠቆጠ የመጣው ዘረፋና ውንብድን እንዲገታ ከፖሊስና የፀጥታ ሃይሉ ጋር በመተባበር መስራት ያስፈልጋል ፡፡
የመዲናዋ አስተዳዳር ይችን ታሪካዊት የዲፕሎማሲ ከተማ ነዋሪዎቿና የአገሪቱ ዜጎች በሚጠብቋት ደረጃ በላይ አለም ካስቀመጣት ማማ እንዳትወርድ ጠንክሮ መስራት ይኖርበታል !!