#ተራዝሟል!!
የማህበር ቤት ምዝገባ ለተጨማሪ አስር ቀናት መራዘሙን የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ የሚታየውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ በተለያዩ የቤት ልማት ፕሮግራሞች ቤቶችን በመገንባት ለተጠቃሚዎች ያስተላለፈ እና ተጨማሪ ቤቶችንም በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡
የነዋሪዎችን የቤት ፍላጐት ፍላጎትም ለማርካት ሌሎች አማራጮችን መተግበር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ በ2005 ዓ.ም የ20/80 እና የ40/60 ከተመዘገቡት ቤት ፈላጊዎች አቅም እና ፍላጎት ያላቸው በጋራ ሕንፃ መኖሪያ ቤት የህብረት ሥራ ማህበር ተደራጅተው ገንዘባቸውን፣ እውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውን እና ጊዜያቸውን በማቀናጀት የቤት ችግሮቻቸውን በጋራ ጥረት ሊፈቱ የሚችሉበትን መንገድ በማመቻቸት ተጠቃሚ ለማድረግ የፍላጎት ምዝገባ መጀመሩ ይታወቃል፡፡
ምዝገባውም ከመጋቢት 21 ቀን 2013 ዓ.ም ለተከታታይ 15 ቀናት ሲካሄድ የቆየ ሲሆን በዚህም ከ8 ሺህ 500 በላይ የማህበር ቤት ፈላጊዎች ተመዝግበዋል፡፡
የምዝገባ ጊዜው ሚያዝያ 5 ቀን 2013 ዓ.ም የተጠናቀቀ ቢሆንም ከተጠቃሚው ወደ ቢሮው በሚመጡ ጥያቄዎች በመነሳት ምዝገባው ለተጨማሪ 10 ቀናት መራዘሙን ቢሮው አስታውቋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ለመመዝገብ እየፈለጉ በሲስተም መጨናነቅ ምክንያት ላልተመዘገቡ ፤ ከመረጃው መዳረስ አንጻር ተጠቃሚው በቂ ግንዛቤ ባለመያዙ እንዲሁም በተለያዩ ምክንያት ያልሰሙ የአማራጭ ቤት ልማት ፕሮግራሙን ፈላጊዎች በመኖራቸው ተጨማሪ እድል ለመስጠት ሲባል የምዝገባ ጊዜውን ማራዘም ቢሮው ገልጿል ፡፡
በመሆኑም መመዝገብ እየፈለጉ በተለያየ ምክንያት ቀኑ ያለፋቸው ተጠቃሚዎች የምዝገባ ጊዜው ከሚያዚያ 6 እስከ ሚያዚያ 15/ 2013 ዓ.ም ድረስ የተራዘመ መሆኑን አውቀው በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ተመዝጋቢዎች ወደ ቢሮ መምጣት ሳያስፈልጋቸው በቀጥታ /Online/ በቢሮው አድራሻ WWW.aahdab.gov.et አማካኝነት ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ መመዝገብ የሚችሉ መሆኑን ቢሮው ያሳውቃል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በምዝገባ ወቅት ችግር የገጠማቸውን የማህበር ቤት ፈላጊዎች ምዝገባው ከተጠናቀቀ በኃላ ከሚያዚያ 18-20/2013ዓ.ም ባሉት ተከታታይ ሶስት ቀናት በቢሮው ቀርበው ቅሬታችውን ማቅረብ የሚችሉ ሲሆን ነገር ግን በማህበር ቤት ፕሮግራሙ መካተት አቅሙ እና ፍላጎቱ ለሌላችው ደግሞ ነባሩ የ20/80 እና የ40/60 የቤት ልማት ፕሮግራም ግንባታ ስራ በተለመደው አሰራር የሚቀጥል መሆኑን ቢሮው አመልክቷል ፡፡