ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች አስመልክቶ የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ (Press Release)
“መንግስት የህግ የበላይነትን ከማስከበር እና ከማረጋገጥ በላይ ቀዳሚ አጀንዳ ሊኖረው አይገባም!”
~ መንግስት የሰላም ሚኒስቴርን አደረጃጀት ሊከልስ ይገባል፣
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዜጎች በህገ- መንግስቱ የተሰጧቸው መበቶች መከበራቸዉን እና መንግሰት በህግ የተሰጠውን ስልጣንና ተግባር በአግባቡ መወጣቱን የመከታተልና የመቆጣጠር ስልጣንና ተግባር ተሰጥቶታል፡፡ በዚህ መሰረት ላለፉት ዓመታት የነበረዉ አሁንም ተባብሶ የቀጠለዉ ሀገራዊ ችግር በተለይም የንጹሀን ዜጎች ሞትና መፈናቀል በአጠቃላይ የህግ የበላይነት አለመከበር በእጅጉ ያሳስበናል፡፡
ስለዚህ በኦሮሚያ ክልል በምእራብ ወለጋ ዞን፣ በአማራ ክልል በኦሮሚያ ልዩ ዞን እና በሰሜን ሸዋ ዞን እንዲሁም በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በመተከል ዞን፣ በአፋር ክልል እና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ ድንበር አካባቢ በንጹሀን ዜጎች ላይ በደረሰውና እየደረሰ ባለው ሞትና መፈናቀል አስመልክቶ
- ለምን መንግሰት በተለይ የጸጥታ መዋቅሩ መከላከል አልቻለም ?
- በዜጎች ሞትና መፈናቀል ላይ ተሳትፎ የነበራቸው አካላት
ተጠያቂነት እና
- በህይወት ለተረፉ እና ለተፈናቀሉ ዜጎች እየተደረገላቸው ባለው ድጋፍ እና እርዳታን በተመለከተ ባደረግነው ቁጥጥርና በደረሰው ሪፖርት መሰረት የሚከተሉትን ግኝቶችና ምክረ- ሃሳቦች እናቀርባለን፡-
በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሰት የሰሜን ሸዋ እና ኦሮሚያ ልዩ ዞኖችን በተመለከተ:-
በአማራ ብሄራዊ ክልል ውስጥ የሚገኙ የአማራ እና የኦሮሞ ብሄረሰብ ለዘመናት ተጋብቶና ተጋምዶ የሚኖር ህዝብ ሲሆን በዘልማድ በግጦሽ እና በድንበር አካባቢ ከሚፈጠር ግጭት ባለፈ የከፋ ችግር ውስጥ ገብተው አያውቁም፡፡
ሆኖም ግን ከባለፉት ሶሰት አመታት ወዲህ ግጭቱ ቅርጽና ይዘቱን እየቀየረ የብሄር እና የሃይማኖት መልክ እየያዘ መምጣቱን የአካባቢው ህብረተሰብ ይመሰክራል፡፡ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላትም በአጽንኦት ሲከታተሉት የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም ግን መጋቢት 10/2013 በሰሜን ሸዋ ዞን በአጣዬ ከተማ በተከሰተው ግጭት በሰሜን ሸዋ ዞን እና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚገኙ አመራሮች የችግሩን መንስኤ አስመልክቶ የተለያየ መረጃ ቢሰጡም በአከባቢው ከሚገኙ የመከላከያ እና የፌደራል ፖሊስ በተገኘው መረጃ መሰረት ግጭቱ በታጠቀ ሀይል እና በዘመናዊ መሳሪያ የተደገፈ እንደነበር ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ችግሩ የከፋ እንዲሆን የማህበራዊ ሚዲያ ጉልህ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ በአንጻሩም በአካባቢው የነበረው የፀጥታ ሀይል መነሳትና በወቅቱ አለመድረስ ችግሩን የከፋ አድርጎታል፡፡ ያለዉን ሀይል ማንሳት ለምን አስፈለገ?፣ማን አነሳዉ?፣ ሌላ የፀጥታ ሀይልስ በጊዜዉ ለምን አልደረሰም? በሚሉ መሰረታዊ ጥያቄዎች ዙሪያ መንግስት አጣርቶ ለህዝቡ ሊያሳዉቅና አጥፊዎችም ካሉ አርምጅ ሊወስድ ይገባል፡፡
በግጭቱም የተጎዱ ዜጎችን በተመለከተ የሞቱ ንጹሀን ዜጎች 303፣ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው 369 የተፈናቀሉት ደግሞ 91,756 ናቸዉ፡፡ ለተፋናቀሉ ዜጎች በሰሜን ሸዋ ዞን በተደራጀ መንገድ የእለት እርዳታ እና ድጋፍ እየተደረገ ሲሆን በኦሮሚያ ልዩ ዞን ግን እየተደረገ ያለው ድጋፍ ዝቅተኛ ነው፡፡ ሆኖም ግን በአቅርቦት ደረጃ በሁለቱም ዞኖች በቂ አይደለም፡፡
የችግሩን ባለቤት መለየትና ተጠያቂ በማደረግ ረገድ 81 ተጠርጣሪ ግለሰቦች እንዲያዙ ቢደረግም ከመከላከያ በተሰጠ ትእዛዝና ምክንያቱ ባልታወቀ መንገድ እንዲለቀቁ ተደርገዋል፡፡ ስለዚህ ተቋማችን ግጭቱ ህዝብ ለህዝብ ነበር የሚል ግምገማ የለንም፡፡ በመሆኑም በግጭቱ ተሳትፎ የነበራቸው ከመንግስት አስፈጻሚ አካላት እስክ ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበራቸው አካላት በህግ ሊጠየቁ ይገባል፡፡
በአጠቃላይ በአማራ ብ/ክ/መንግሰት በሰሜን ሸዋ ዞን እና በኦሮሚያ ልዩ ዞን የተከሰተውን ግጭት ለመፍታት ከአከባቢው ህብረተሰብ የበለጠ ባለቤት ስለሌለው የማይመለከታቸው አካላት ከጣልቃ ገብነት ራሳቸውን ቆጥበው ከብሄር አስተሳሰብ በመወጣት ኦሮሞም ይሁን አማራ ትግሬም ይሁን አኙዋክ የሚሞቱት ኢትዮጵያዊያን ናቸው የሚል አሰተሳስብ በመያዝ ችግሩ በዘላቂነት ሊፈታ ይገባል፡፡ በአንጻሩ የአንዱ ብሄር መፈናቀልና ሞት የእኔም ነዉ የማይሉና እንደራሳቸዉ ቆጥረዉ የማይጠይቁ ለራሳቸዉም ብሄር አይጠቅሙምና ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል፡፡
በቤንሻንጉል ክልል በመተከል ዞን እና በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ወለጋ እየደረሰ ባለው ሞትና መፈናቀልን በተመለከተ
ተቋማችን ከዚህ በፊት ባወጣው ሪፖርት በየትኛውም ሀገር አካባቢውን በባሌቤትነት መጠበቅ ያለበት ህብረተሰቡ በመሆኑ ህብረተሰቡን ማደራጀትና ማሰልጠን (empowerment) እንደሚገባ ምክረ-ሃሳብ አቅርበን ነበር፡፡ ሆኖም ግን በሁለቱም ቦታዎች ለሚደርሱ ጥፋቶች የመንግሰት ቸልተኝነት ወይም ትኩረት ማነስ ውጤት ነው ብሎ ተቋማችን ያምናል፡፡
ምክንያቱም በመተከል ዞን ሽፍቶች ትጥቅ ሳይፈቱ ድርድረ መደረጉ እና ወደ ተሃድሶ እንዲገቡ የተደረገበት አግባብ ስህተት ነበር፡፡ በተመሳሳይ በዞኑ ከ10000 በላይ ታጣቂዎች እንዲሰለጥኑ ከተደረጉ በኋላ አልፎ አልፎ ጣል ጣል ከተደረገ ትጥቅ በስተቀር ራሳቸውን ለመከላከል የሚያስችላቸው ትጥቅ አልነበራቸውም፡፡
በተመሳሳይ በኦሮሚያ ብ/ክ መንግሰት በወለጋ ቀጠና የጸጥታ የስጋት አካባቢ መሆኑ እየታወቀ እና ተደጋጋሚ ችግሮች እየተከሰቱ ባለበት ሁኔታ የጸጥታ የስጋት አካባቢ አድርጎ መሰራት ሲገባው ንጹሀን ዜጎች ከሞቱ በኋላ ጉዳት አድራሾች ተደመሰሱ የሚል ዜና ከማግስቱ ጀምሮ መቅረቡ አግባብነት የለውም፡፡ ምንም እንኳን የኦሮሚያ ብ/ክ/መ ካለው የቆዳ ስፋትና ካለው የሰው ሀይል ብዛት አንጻር ሁሉንም የክልል አካባቢዎች ለመሸፈን እንደሚቸገር ቢታወቅም አዲስ ክስተት ባለመሆኑና የተለየ ቦታ በመሆኑ ተገቢዉ ትኩረትና ቅድመ መከላከል ሊሰራበት ይገባ ነበር አሁንም ይገባል፡፡
በሶማሌ ብ/ክ/መ እና በአፋር ድንበር አካባቢ በአፋር እና በኢሳ ጎሳዎች በአዳይቱ በገዳማይቱ በሃርንኮ እና ገላ አሎ አካባቢዎች በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የአስተዳደራዊ ወሰን ውዝግብ መፍታት ባለመቻሉ ዛሬም ድረስ ንፁሃን ዜጎች የመንግስት ሰራተኞች እና የክልሉ የፖሊስ አባላት እየተገደሉ ይገኛሉ፡፡
ሆኖም ግን በአካባቢው የሚገኝ የፌደራል ፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት ትእዛዝ አልደረሰንም በሚል ምክንያት ጣልቃ በመግባት የዜጎችን ሞት መታዳግ አልቻሉም፡፡ ስለዚህ የሚመለከታቸው የፌደራልና የክልል መንግስታት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው የከፋ እልቂትና መፈናቀል ከማሰከተሉ በፊት እርምጃ ሊወስዱ ይገባል፡፡
የቀጣይ የመፍትሄ ሃሳቦች
1ኛ- የክልል ከፍተኛ አመራሮች ከብሄር አስተሳሰብ በመውጣት በመርህ ሀገሪቷን ብሎም ክልላቸውን ሊመሩ ይገባል፡፡ ከሰሞኑ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በሰሜን ሸዋ ዞን እና ኦሮሞ ብሄረሰብ በተከሰተው ግጭት የዜጎችን ሞትና መፈናቀል በጋራ ሁሉም የክልል አመራሮች ከማውገዝና ችግሩን ቁጭ ብሎ ለመፍታት ጥረት ከማድረግ ይልቅ የግጭቱን መንስኤ በመግለጫ ውጫዊ ለማድረግ ጥረት ሲደረግ ተስተውሏል፡፡ ወደ ዞን እና ወረዳዎች ሲወረድም አንደኛው ሌላኛውን አመራር የችግሩ መንስኤ ወይም ባለቤት ለማድረግ ይሞከራል፡፡
ስለዚህ የመንግስት አስፈጻሚ አካላት አንድም ንጹህ ዜጋ መሞት የለበትም የሚል አቋም በመያዝ ለህግ የበላይነት መርህ መገዛት እና መስራት ይኖርባቸዋል፡፡ መንግስትም ቢያንስ በጉያዉ ስር ያሉ ለችግሮች መፈጠርና መባባስ ምክንያት የሆኑትን አመራሮቹን ሊያጠራና እርምጃ ሊወስድ ይገባል፡፡
2ኛ- መንግስት የሰላም ሚኒስቴርን አደረጃጀት ሊከልስ ይገባል
ባለፉት ሶስት አመታት የዴሞክራሲ ተቋማት ተግባራቸውን ነጻ እና ገለልተኛ ሆነው ለመስራት ምቹ ሁኔታ የተፈጠረላቸው ቢሆንም በተቋማቱ የሚቀርቡ የመፍትሄ ሃሳባችን ለመተግበርም ይሁን ለመጠየቅ ሲሞክሩ አይስተዋሉም፡፡
ለምሳሌ ጥቅምት 24 የህወሓት ጁንታ ቡድን በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ኢ-ሰብኣዊ ድርጊት ከመፈጸሙ ስምንት ወራት በፊት የክልል ልዩ ሀይሎችን አደረጃጀት መንግስት ሊያጤነው እንደሚገባ እንዲሁም በአማራ ብ/ክ/መ አዊ ብሄረሰብ ዞን ቻግኒ ከተማ የእርዳታ እህል ክምችት በመኖሩ እንዲሰራጭና በቂ ጥበቃ እየተደረገለት እንዳለሆነ ለሚመለከተው አካል ሪፖረት አድርገን ባለመፈጸሙ ለቃጠሎ መዳረጉን ለአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡
አሁንም የዜጎችን ሞትና መፈናቀል እንዲሁም የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ መንግሰት ቆፍጠን ያለ አመራር ሊሰጥ ይገባል፡፡
በተጨማሪም የሰላም ሚኒሰቴር ሁለት ተቃራኒ ተግባራትን ማለትም የሰላም ግንባታ እና የጸጥታ ማስከበር ሃላፊነት የተሠጠው ሲሆን የሰላም ግንባታ በሂደት እና በተራዘመ ትምህርት እና ግንዛቤ ስራ የሚከናወን ሲሆን በአንጻሩ የጸጥታ መዋቅሩ ግን በቅጽበት በሚወሰኑ ውሳኔዎች እና እርምጃዎች የሚከናወን ነው፡፡ ስለዚህ የጸጥታ መዋቅሩ እና የብሄራዊ መረጃ ደህንነት ራሱን በቻለ ተቋም ሊመራ ይገባል፡፡
አሊያ በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ ሊሆኑ ይገባል፡፡: በጊዚያዊነትም 6ኛው ብሄራዊ እና ክልላዊ ምርጫ ተከናውኖ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እስከሚያደርግ ድረስ የሀገሪቷ የጸጥታ ተግባር በተማከለ ኮማንድ እዝ ሊመራ ይገባል፡፡ እንዲሁም ትላልቅ ከተሞች የተለያየ ህብረተሰብ ክፍል ተሰባጥሮ በሚኖርበት እና የአስተዳደራዊ ወሰን ውዝግብ ባለባቸው ቦታዎች በፌደራል ፖሊስ ጥላ ስር ከሁሉም ክልሎች በተውጣጣ የልዩ ፖሊስ ሀይል የዜጎችን ሰላም እና ጸጥታ እንዲጠበቅ ምክረ-ሃሳባችንን እናቀርባለን፡፡
3ኛ- በሁሉም ክልሎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች የእለት ደራሽ እርዳታ እና በዘላቂነት የማቋቋም ስራ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ ይገባል፡፡ በተለይ በአማራ ክልል የሚገኙ የኦሮሞ ብሄረሰቦች ህወታቸው በሸዋ ሮቢት እና አጣዬ ገበያ ላይ የተመሰረቱ በመሆናቸው የክልሉ መንግሰት ትኩረት ሊያደርግላቸው ይገባል፡፡ ምክንያቱም አብዛኛው በተጠቀሱት አካባቢዎች የሚኖሩት በእንጨት ሽያጭ እና በምግብ ዋስትና የሚኖሩ ናቸውና፡፡
መጋቢት 29 ቀን 2013 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም