Connect with us

የሁለቱ መደመሮች የመጽሃፍት ዳሰሳ።  ክፍል 1

የሁለቱ መደመሮች የመጽሃፍት ዳሰሳ። ክፍል 1
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

የሁለቱ መደመሮች የመጽሃፍት ዳሰሳ።  ክፍል 1

የሁለቱ መደመሮች የመጽሃፍት ዳሰሳ።  ክፍል 1

(አንዳርጋቸው ፅጌ)

ማሳሰቢያ:-  ይህ ጽሁፍ፤ ቅዳሜ መጋቢት 25 ቀን  2013 ሆሄ የስነ ጽሁፍ ሽልማት ድርጅት፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ባዘጋጀው የዶ/ር አብይ አህመድን “የመደመር መንገድ” (2013) የተሰኘውን መጽሃፍ ለመዳሰስ በከፊል የተዘጋጀ ነው። ጽሁፉ ረጅም በመሆኑ በዝግጅቱ ላይ ያቀረብኩት በጣም አነስተኛውን እና ወሳኙን ክፍል ብቻ ነው። 

ረዘም ያለ ጽሁፍ የማንበብ ልምድ እየጠፋ መሆኑን አውቃለሁ። ትልልቅ ሃገራዊ ጉዳዮችን በአንድ መስመር የትዊተር ወይም የፌስ ቡክ መስመሮች ማቅረብ ግን አይቻልም። ይህን ተረድታችሁ በትእግስት እንድታነቡ በአክብሮት እጋብዛችኋለሁ። ጽሁፉ ለፌስ ቡክ ስለረዘመ በሶስት ከፍየዋለሁ። የመጀመሪያው ክፍል ከይዘት ውጭ ያለውን የሁለቱን መጽሃፎች ዳሰሳ የያዘ ነው። ክፍል ሁለትና ሶስት የይዘት ዳሰሳ የያዙት ናቸው።

“የሁለቱ መደመሮች” መጽሃፍት ዳሰሳ

  1. መንደርደሪያ

“መደመር” የሚል ርእስ የተሰጠው የጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ መጽሃፍ 2012 ላይ ይፋ ሲሆን በሃገር ውስጥ አልነበርኩም። ወደ ኢትዮጵያ ስመለስ የመጽሃፉ መታተምና መሰራጨት የቀሰቀሰው መቁነጥነጥ ረግቦ ነበር።  የመጽሃፉ ግምገማና ዳሰሳም አልቆ ነበር። እኔም ይህን መጽሃፍ በወጉ ለመዳሰስ ፍላጎቱ ቢኖረኝም የዳሰሳው ወቅት ያለፈ ስለመሰለኝ ፍላጎቴን መግታት ነበረብኝ።

ሆኖም ግን በወቅቱ በመጽሃፉ ዙሪያ የተሰጡ አስተያየቶችን፣ ዳሰሳዎችንና ግምገማዎችን ከማዳመጥና ከማንበበብ አልቦዘንኩም። በርካታ ዳሰሳዎች ወይም አስተያየቶች በአድርባይነት የተሞሉ፣ የማይተናነሱት በጋጠወጥነት፣ ከዛ የተረፈው በገምጋሚዎች የእውቀት ልኬት የተወሰኑ እንደሆነ ለመታዘብ ችያለሁ።

በኢትዮጵያ መጽሃፍትን በአድርባይነትና በግብዝነት መገምገም፣ ከዛም አልፎ ፈጽሞ አንድም መስመር ሳያነቡ ወይም ከአንድ ትልቅ መጽሃፍ ሁለት መስመሮችን ወስደው የመጽሃፍ ዳሰሳና ትችት ለማቅረብ በየትኛውም መድረክ ላይ በድፍረት መቅረብ የማያሳፍራቸው ሰዎችን እያየሁ ነው። የመደመር መጽሃፍ ዳሰሳም ከዚህ የተለየ እጣ አላጋጠመውም። ይህ የግል ግንዛቤዬ ነው።

“መደመር” ሰፊ አንባቢ የማግኘት እድል ያለው መጽሃፍ ነው። በተጽእኖ አሳዳሪነቱ ግዙፍ እንደሚሆን አያጠያይቅም። መጽሃፉ በወጉ ሳይዳሰስ ቀረ የሚል ቁጭት እንዲያድርብኝ ያደረገውም ይህ ነጥብ ነበር። ሰሞኑን ግን ከዚህ ቁጭት የሚገላግለኝ አጋጣሚ ተፈጠረ።

ይህ አጋጣሚ የሁለተኛው እና ከመደመር ጋር ግንኙነት ያለው የጠቅላይ ሚኒስትሩ “የመደመር መንገድ” የሚለው መጽሃፍ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ይፋ መሆኑ ነው። ሁለቱ መጽሃፎች ተያያዥነትና ተደጋጋፊነት ስላላቸው  እግረ መንገዴን የመጀመሪያውን ጭምር ብዳስሰው አግባብነት ያለው መሰለኝ። በመሆኑም ይህን “የሁለቱ መደመሮች” የተሰኘውን ዳሰሳ አቀረብኩ።

  1. የመጽሃፎቹ ተመሳሳይነትና ልዩነት

መጽሃፎቹ በጣም ተደጋጋፊ ሃሳቦችን የሚያነሱ ናቸው። ይህን ስል ልዩነት የላቸውም ማለት አይደለም። አላቸው። ልዩነታቸው ግን ከኔ ዋንኛ የዳሰሳ ቅኝት አኳያ አይደለም።

የመጀመሪያው “መደመር” ትኩረት፣ መደምር ለሚለው ቃል ትርጉም በመስጠትና በዚህ ትርጉም አማካይነት የሃገሪቱን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣  የባህላዊና የሌሎችንም ስብራቶቿን መፈተሽና የመጠገኛውን መንገድ ማመላከት ነው። ሁለተኛው “የመደመር መንገድ” መደመር የሚለውን ቃል በተለያዩ ትረካዎች አማካይነት የበለጠ ማብራራትና ማጎልበት እንዲሁም ተጨማሪ ትርጉም መስጠት ነው። ሁለተኛው መጽሃፍ “መደመርን” በተመለከተ በመጀመሪያው መጽሃፍ ላይ ያልተካተቱ ነገሮችን አካቷል። የመጽሃፉ ዋና ትኩረት ግን እዚህ ላይ አይደለም።

“የመደመር መንገድ” አብዛኛዎቹ ገጾች የጠፉት በማሰላሰል ጉዳዮች ላይ ሳይሆን በሚተረኩ ጉዳዮች ላይ ነው። ትረካው የመደመር ሃሳብ በአብይ አእምሮ ውስጥ እንዴት እያደገ እንደመጣ ከልጅነቱ እስከ ጎላማሳነቱ ካላፈባቸው የህይወትና የስራ ተሞክሮዎች ጋር እያዛምደ የሚያቀርበበት ነው። እነዚህ ጉዳዮች በመጀመሪያ መደመር ነካ የተደረጉ ቢሆንም በሁለተኛው መደመር ሰፋ ተደርገው ቀርበዋል።

በ “የመደመር መንገድ” ውስጥ ሌሎች የተለያዩ በርካታ ትረካዎች አሉ።  ኢህአዴግ ውስጥ ህይወት ምን ይመስል እንደነበር፣ ኢህአዴግን ለመቀየር ስለተደረገው ትግል፣ ከሶስት አመት በፊት ስለመጣው ለውጥ፣ ፈተና እና ድሎቹ፤ ከለወጡ በኋላም ስለተደረጉ ትግሎችና ድሎች ይተርካል። ስለተከናወኑ ስራዎች፣ ሌሎች የመደመርን ሃሳብ ስላበለጸጉት የዶ/ር አብይ ግላዊ ገጠመኞች፣ ስለወደፊት ህልሞችና ስለሌሎችም ጉዳዮች ተተርኳል። በነዚህ ትረካዎች መሃልም የመደመር ሃሳብ በተደጋጋሚ ይነሳል። 

ሆኖም ግን እነዚህ ትረካዎች በመደመር ላይ ከሚሰጡን ተጨማሪ ማብራሪያ ወይም መግለጫ  ይልቅ በሚሰጡን አዳዲስ መረጃዎች የላቀ ፋይዳ አላቸው። እነዚህ ትረካዎች ጸሃፊው ምን አይነት ሰው? ምን አይነት እውቀትና ክህሎት አለው? ምን ያልማል? ህልሙን ለማሳካት ምን ያህል እልህና ቁርጠኛነት አለው? የሚሉ ጥያቄዎች ለሚያነሱ በቂ መልስ የሚሰጡ ናቸው።

ሃገራችን ውስጥ መጽሃፍ በገለልተኛነት የሚያነቡ ብዙ ዜጎች መኖራቸውን ብጠራጠርም ከተገኙ ግን በአብይ ነገሮችን እርስ በርሳቸው አጎናጉኖ ለአንባቢ በሚጥም ለዛ እና ውበት ደረቅ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ጉዳዮችን ማቅረብ በመቻሉ መገረማቸው አይቀርም የሚል እምነት አለኝ። 

እነዚህ ትረካዎች  በ “የመደመር መንገድ” ሲመረቅ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ በማህበረሰባችን ውስጥ አንዳንዶች እያነሱት ነው በማለት ላነሳው ጥያቄ መልስ ይሰጣሉ። ዳኛቸው ጥያቄውን “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስራ የላቸውም ወይ በዚህ አይነት አስቸጋሪ ወቅት መጽሃፍ የሚጽፉት እያሉ ነው” በማለት ነበር ያቀረበው።  እነዚህን ትረካዎች የሚያነብ ሰው የሚያነሳው ጥያቄ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምን ይጽፋሉ” የሚል ሳይሆን “ባይጽፉ ምን ይሆኑ ነበር” የሚል ይሆናል። ጉዳዩን በደንብ የተረዳው “ባይጽፉ ሊያብዱም ይችሉ ነበር” ሊል ይቻላል። ቀልዴን አይደለም።

አብይ በሁለቱ መጽሃፎች ውስጥ ያሰፈራቸውን ከጭንቀት፣ ከቁጭት፣ ከእልህ፣ ከቁጣ፣ ከምኞት፣ ከፍላጎት፣ ከህልም፣ ከትልም እና ከሌሎች ነገሮችና ስሜቶቹ ጋር የተያያዙ ህልቆ መሳፍርት የሌላቸውን ሃሳቦቹን በጭንቅላቱ ይዞ በምንም አይነት ጤነኛ ሆኖ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ስራ ሊሰራ እንደማይችል እነዚህ ትረካዎች ማስረጃ ናቸው። ሃሳቡን በማጋራቱ ከሚያገኘው ጥቅም ባሻገር ጽሁፎቹ አብይ ለራሱ የሰጠው የስነ አይምሮ ቴራፒ ተደርገው መወሰድ የሚችሉ ናቸው። ይህ ቴራፒ የአብይን የጠቅላይ ሚኒስቴርነት ስራ ያቀለለው እንጂ ያከበደው እንደማይሆን እምነቴ ነው።

  1. የዳሰሳው ዳራ

የአብይ መጽሃፎች ከበርካታ የዳሰሳ አቅጣጫዎች ሊታዩ የሚችሉ እጅግ በርካታ ጉዳዮች አጭቀው የያዙ ናቸው። አጭቀው ስል በቀላሉ መወሰድ የለበትም። የኔ የዳሰሳ ትኩረት በሁለቱም መጽሃፎች ርእስና በውስጥ ገጻቸው አብይ ትልቅ ትርጉም በሰጠው “መደመር” በሚለው ጉዳይ ላይ ብቻ ያተኮረ ነው። ይህን የማደርገው በሁለቱ መጽሃፎች ውስጥ አብይ በሚያነሳቸው በሁሉም ጉዳዮች ላይ ዳሰሳ ማድረግ ከዳሰሳ ክልል አውጥቶ ሌላ መጽሃፍ የሚያጽፍ ሆኖ ስላገኘሁት ነው።

ክዚህ በመነሳት የዳሰሳዬን ዳራ እንደሚቀጥለው በሁለት ርእስ ከፍዬ አቀርባዋለሁ። የመጀመሪያው ከይዘት ባሻገር የሁለቱ  መጽሃፎች ጥንካሬና ድክመት የምዳስስበት ይሆናል። ሁለተኛው  የሁለቱንም መጽሃፎች የይዘት ዳሰሳ የማቀርብበት ክፍል ነው። አስፈላጊ ሆኖ ሳገኘው በሁለቱም የዳሰሳ ክፍሎች ሁለቱንም በአንድ ላይ፣ አስፈላጊ ሆኖ ሳይገኝ በተናጠል የምዳስስበት አግባብ እንደምከተል አስቀድሜ መግለጽ እሻለሁ።

  1. “መደመር” 2012 እና “የመደመር መንገድ” 2013 ዐብይ አህመድ፤ ከይዘት ባሻገር “የመደመሮቹ ” ጥንካሬና ድክመቶች፤

ወደ ይዘቱ ሳልገባ ሁለቱም መጽሃፎች በበርካታ ጥንካሬዎች የታደሉ መጽሃፎች ሆነው አግኝቸዋለሁ። እነዚህን አጠር አጠር አድርጌ ላቅርባቸው።

– ጉዳዩ የገንዘብ አቅም እንደሆነ ቢገባኝም፣ ለህትመት ጥራት የተሰጠው ትኩረት በከፍተኛ የጥራት ልቀት የተዘጋጁ መጽሃፎች እንዲሆኑ አድርጎቸዋል። ከመጽሃፎቹ  አጠራረዝ ጀምሮ፣ የሽፋኖቹ የምስል ጥራት አካቶ፣ እየአንዳንዱ ገጽ የታተመበት የህትመት ጥራት፣ ለእይታ ማራኪነትና ለመነበብ ያለው ሳቢነት የመጽሃፎቹ መልካም ጎን ነው።

– መጽሃፎቹ አግባብነት ባላቸው ክፍሎች፣ ምእራፎችና ንኡስ ምእራፎች የተከፋፈሉ ናቸው። እንዲያም ሆኖ ሁለቱም መጽሃፎች ከአጠቃላይ ቅርጻቸውና ይዘታቸው ጋር የማይሄዱ ክፍሎችና ምዕራፎች መያዛቸው እንደ ድክመት ሊታይባቸው ይችላል። በኔ እይታ።

በመጀመሪያው መጽሃፍ የወጭ ጉዳይን በተመለከተ የገባው ክፍል እንዳለ መቅረት ይችል ነበር። ምክንያቱን በሚቀጥሉት ገጾች አቀርባለሁ። “የመደመር መንገድ”ም የተወሰኑ ምእራፎች ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው ናቸው። በመጽሃፉ የምረቃ ወቅት የተጠቀሰው “የብልጽግና ተረክ” የተሰኘው ምእራፍ፣ በውስጡ ብዙ ቁም ነገሮች የያዘ ቢሆንም የፕሮፓጋንዳ ጎኑ ያየለ ስለሚመስል ቢቀር ጥሩ ነበር። የመጽሃፉን የአጻጻፍ ወጥነት ያደናቀፈው ስለሚመስል ነው። 

ሌሎችም ይህን ንኡስ ምእራፍ ተከትለው የመጡ ሌሎች ንኡስ ምእራፎችም የስራ ዘገባ የሚመስል ነገር አላቸው። በውስጣቸው ብዙ ቁም ነገር ቢኖራቸውም ከትረካ የራቁ ስለሚመስሉ እነሱም ባይገቡ መጽሃፉን በውበትም ሆነ በይዘት የሚያደኸዩት አይሆንም ነበር።

– በሁለቱም መጽሃፎች፣ አረፍተነገሮች በቀላሉ አንባቢ ሊረዳቸው የሚችሉ፣ አጫጭር፣ የሚደጋገሙ አታካች ስንኞችና ቃላቶች ያልበዙባቸው ናቸው። የፊደል ግድፈት ወይም ስህተት የማይታይበት ምልኡ የአርትኦት ስራ ተካሂዶባቸዋል። አንድኛው መጽሃፋ ከሁለተኛው የተሻለ የአርትኦት ስራ የተሰራበት መሆኑ ሁለተኛው መጽሃፍ ትንሽ የአርትኦት ችግር ቢኖርበትም።

– የመጀመሪያው መጽሃፉ “መደመር” በተለይ፣ በተበጣጠሰ መልኩ እዚህም እዚያም ሲወረወሩ የምናያቸውን የፖለቲካ የኢኮኖሚ እሳቤዎችን አመለካከቶችን፣ ጽንሰ-ሃሳቦችን በአንድ መጽሃፍ ውስጥ በጥቂት ገጾች በቀላሉና በተደራጀ መንገድ ማቅረብ ችሏል።

– በሁለቱም መጽሃፎቹ አብይ በግብዝነት ላይ ለተመሰረተ አዋቂ ሊያስመስለው ስለሚችል ጉዳይ አልተጨነቀም። ራሱን ሆነ ማንም ግለሰብ ሊያቀርባቸው የሚችሉ አመለካከቶችን፣ አባባሎችን፣ አስተያየቶችን፣ የአዋቂዎች ድጋፍ ያላቸው ለማስመሰል ጽሁፉን አላስፈላጊ በሆኑ ጥቅሶች አልሞላውም። ይህ አጻጻፍ ለትረካው ያልተደነቃቀፈ አፈሳሰስ ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጓል፤

– ብዙ ጊዜ በባእድ ቋንቋ ውይይት የሚደረግባቸውን፣ የሃገራችን ምሁራን “በአማርኛ ለማቅረብ አስቸጋሪ ናቸው” በማለት በባእንድ ቋንቋ ሲያስተናግዷቸው የኖሩ የሃገራችንን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግሮች፣ እይታዎችን እሳቤዎችንና መፍትሄዎችንም፣ ደራሲው በአማርኛ ብቻ ሳይሆን በኦሮምኛ ጭምር ማቅረብ መቻሉ ትልቅ ክንዋኔ ነው።

– በመጽሃፎቹ ውስጥ በተለይ በመጀመሪያው መጽሃፍ የቀረቡ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ነክ፣ የተለያዩና የረቀቁ አተያዮች፣ ንደፈ ሃሳባዊ መሟገቻዎች በቀላሉ ምሁር ያልሆነ አንባቢ ሳይቀር ሊረዳው በሚችል ሃገራዊ ቋንቋ በመጻፍ፤ በርከት ያለ አንባቢ ሌላ ጊዜ የማይደፍራቸውን የሃሳብ ዘርፎች ደፍሮ ማንበብ እንዲችል፤ አንብቦም የራሱን አቋም እንዲውስድ፣ ከሌሎች ጋር ሃሳብ እንዲቀያያርና እንዲከራከር የሚያስችል አቅም የሚሰጠው ሆኖ አግኝቸዋለሁ።

–  የመጽሃፎቹ  ጸሃፊ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር መሆኑ፣ ከዚህ ቀደም መሰረታዊ በሆነ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ የተጻፉ መጽሃፍትን ለማንበብ ፍላጎት የማይኖረውን የህብረተሰብ ክፍል፣ እነዚህን መጽሃፎች እንዲያነብ ያደረገዋል። ይህ  ብቻ ሳይሆን ከዚህም ንባብ ተነስቶ በሃገሩ ጉዳይ ዙሪያ የተጻፉ ሌሎች መጽሃፎችን የማንበብ ፍላጎት እንዲኖረው የሚያበረታታ፣ የአንባቢን ቁጥር በማሳደግ በጎ ተጽእኖ ማሳደር ያስችላል የሚል እምነት አለኝ።

– መጽሃፎቹ በተለይ “መደመር” በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን የሃገራችንን የፖለቲካ የኢኮኖሚ ችግሮችና  (ዶ/ር አብይ እንደሚለው “ስብራቶች”) መፍትሄዎቻቸውን  በዝርዝር ያቀረበ በመሆኑ ምንም አይነት የረባ የድርጅት ፕሮግራምና ፖሊሲዎች ለሌላቸው የሃገራችን በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ሌላው ቢቀር ፍላጎቱ ካላቸው፣ ለፕሮግራም መጻፊያ ወይም ለፖሊሲ ጥናት መነሻ የሚሆኑ መንደርደሪያ ሃሳቦችን የሚያስታጥቃቸው ሆኖ አግኝቸዋለሁ። 

ከየትም ተቆርጦ በሚለጠፍ ስልት ከሚዘጋጅ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሮግራም፣ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በሃገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ፕሮግራም መጻፍ እንዲችሉ ያግዛቸዋል። የፖለቲካ ድርጅቶች ከጥቅል ፕሮግራም ወደ ዝርዝር የሴክተር ፖሊሲዎች ጥናት የመሻገር ግዴታ እንዳለባቸው ይጠቁማቸዋል። ፖለቲካ ከስሜት ወጥቶ በምክንያት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን በጎ ጫና ያሳርፋል።

– ትልቁ የመጽሃፎቹ ጥንካሬ በስልጣን ላይ የሚገኝ አንድ መሪ “የሃገራችን ዋና ዋና ችግሮችና መፍትሄዎቻቸውም እነዚህ ይመስሉኛል” በማለት ሃገሪቱን ወዴት ሊወስዳት እንደሚሻ ሁሉም ዜጋ በአደባባይ እንዲያየው ጽፎ ማሳተሙ ነው። እንኳን ሃገር የሚመሩ ፖለቲከኞች ቀርተው ህይወታቸውና ሙያቸው ሃሳብን በሃሳብ መሞገት የሆነው የአካዳሚ ሰዎችም መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳብ ለመሰንዘር ድፍርት ባጡበት ሃገርና ዘመን፣ የሃገሪቱ መሪ የሆነ ሰው ሃሳቡን፣ ጨዋው ባለጌውም፣ አዋቂውም አላዋቂውም እንዲያነበውና የፈለገውን አስተያየት እንዲሰጥበት በማድረግ ለህዝብ ማቅረብ መቻሉ ትልቅ ፋይዳ አለው።

– መጽሃፎቹ የደራሲውን ደጋፊዎች በጽናት ከጎኑ እንዲቆሙ፣ ተቃዋሚዎቹ ለምን እንደሚቃወሙት ምላሻቸውን በአግባቡ፣ በጽሁፍ እንዲሰጡ ያበረታታሉ። በጨበጣ የሚደረግን የተቃውሞ ባህል ያዳክማሉ። ከዛም አልፎ ሀገርና ህዝብን ሊያሻግሩ የሚችሉ ሃሳቦችን በአአምሮዋቸው ወይም በቢሮ መሳቢያቸው አስቀምጠው የአላዋቂን ትችት እና የባለጌን ስድብ ፈርተው ምንም ላለማለት በፍርሃት ተሸብበው የሚኖሩ የሃገሪቱ ልሂቃን ከፍራቻ ቆፈናቸው ወጥተው በሃሳብ ማህበረሰብን የመምራት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ያበረታታሉ።

– “የመደመር” ጥንካሬ ተደርጎ መታየት ቢችልም በሌላ በኩል የድክመት ጎን የታየበት ጉዳይ ፣ ከአብይ እምነቶች ጋር የማይስማሙ አመለካከቶች በንጽጽር በሚቀርቡበት ወቅት ጻሃፊው በተቻላ መጠን ሃሳቦችን በገለልተኛነት የማቅረቡ ጉዳይ ነው። በሃገራችን የተለመደው የራስን አመለካከት ትክክለኛነት ለማስረገጥ የሌላውን የማጣጣል፣ የማንቋሸሽ በአሽሙር፣ በስድብና በፍረጃ የሚያቀርብ አለመሆኑ ከመጽሃፉ ጠንካራ ጎኖች ጋር የሚመደብ ሃቅ ነው። ይህም ለሰለጠነ የተዋስኦ ባህል የራሱን ድርሻ ተጫውቷል።

ይህን ስል ግን፣ “አብይ ከራሱ እምነት ጋር ተቃራኒ የሆኑ የፖለቲካ ይሁን የኢኮኖሚ ነክ አመለካከቶችን ወይም እሳቤዎችን በሚገባ ያላቀረበባቸው ቦታዎች የሉም” ማለት አይደለም። ከይዘት ውጭ ባሉ ጉዳዮች ላይ በድክመት ማቅረብ የምችለው አንድ ነጥብ ቢኖር ይህ ብቻ ነው። ይህ ድክመት አንድ ይሁን እንጂ ትልቅ ድክመት ይመስለኛል።

ይህ ድክመት ተቃራኒ  አመለካከቶች በደንብ ካለማወቅ ወይም ካለመረዳት ወይንስ “በተሟላ መንገድ ማቅረቡ የራስን አቋም ያዳክማል” ከሚል የሆን ተብሎ ፍላጎት የተደረገ መሆኑ ማወቅ አይቻልም።

ለምሳሌ “ኢህአዴግ በረጅም የስልጣን ዘመኑ ምንም አልሰራም” የሚሉ ወገኖች ከጭፍን ጥላቻ ወይም ሌሎች የሰሩትን በበጎ ከማያይ ባህላችን የሚመነጭ አመለካከት ብቻ አድርጎ በሚያየው አተያይ ላይ አብይ ያተኩራል። ይህ የአብይ እምነት እውነትነት የለውም ማለት አይደለም።

በሌላ በኩል ግን “ኢህአዴግ ከቆየበት የስልጣን ዘመን ርዝማኔ፣ ካገኘው መልካም አጋጣሚ አኳያ ሲታይ፣ ሃገሪቱ በሁሉም ዘርፎች ማስመዝገብ ትችል ከነበረው እድገት መጠነኛ ሊባል የሚችል እድገት ማስመዝገብ ባለመቻሉ የሃገሪቱ እድገት ወደኋላ የጎተተ እንጂ ወደፊት ያመጣ ተደርጎ ትንሽም እውቅና ሊሰጠው አይገባም” የሚለውን ምክንያታዊ ክርክር በሚገባ አይፈትሸውም።

አብይ፣ በወያኔ ዘመን ለእድገትና ብልጽግና እንቅፋት የነበረውን የአለመካከት፣ የፖሊሲና የአሰራር፣ እንዲሁም የሙስና፣ የዘረፋ፣ የብቃትና የእውቀት ችግሮች በጥልቀት ይዘረዝራል። በዚህ የተነሳ በሃገሪቱ ላይ ወደር የሌለው ጉዳት እንደደረሰ የሚያቀርበው መጽሃፍ በኢህአዴግ ለተሰሩ ስራዎች እውቅና መስጠት፣ ለመጥፎ አሰራሮች፣ ለዝቅተኛ ክንዋኔዎች፣ መወገድ ለሚችሉ የአስተዳደርና የልማት ህጸጾች ማህበረሳባችን ዜሮ ትእግስት እንዳይኖረው የሚያደርግ ጎጂ አቀራረብ ሆኖ አግኝቸዋለሁ።

በኢህአዴግ ላይ የሚቀረበው ነቀፋ “ድርጅቱ ካለማው ያጠፋው በዝቷል። ሃገሪቱ ያስመዘገበችው አሉታዊ እድገት ነው” የሚለው ክርክር በዚህ አይነቱ አመክንዮ ላይ የተመሰረተ ጭምር መሆኑን የሚያሳየው ክርክር በመጽሃፉ ውስጥ ቦታ የለውም። (መደመር ገጽ 25፣ ገጽ 33 ገጽ 155-156 በሌሎችም ገጾች ከሁኔታዎች ማእቀፍ ውጭ ኢህአዴግ ያስመዘገባቸውን ድሎች በአንጻራዊነት የሚያቀርቡ ትረካዎች የቀረቡባቸው ገጾች ናቸው። “በመደመር መንገድ” ገጽ 25 ቤተኛ ባይተዋር በሚለው ርእስ ስር ተመሳሳይ አይታ ይንጸባረቃል።)

ዛሬ በፖለቲካ ሆነ በኢኮኖሚ መስኩ ሃገሪቱ የምትገኝበት እጅግ አስፈሪ የሆነ ረግርግ (ሌላው አካባቢ ቀርቶ 30 አመት ሙሉ ወያኔ የተሻለ አመራራ ሲሰጠው ነበር በሚባልበት በትግራይ ውስጥ ያለውን እጅግ አሰቃቂ የድህነት ረግርግ እያየን ነው። 

ይህን እያየን በ30 አመት ስላደገ የሃገሪቱ የነፍስ ወከፍ ገቢ እድገትና ስለተከናወኑ የልማት ስራዎች ማውራት እንችላለን ወይ) በኢህአዴግ ዘመን መሰራት ሲገባቸውና መሰራት  እየተቻሉ ካልተሰሩ ወይም ሆን ተብሎ ለግል ጥቅም ሲባል በሃገር ኪሳራ ከተሰሩ እኩይ ተግባራት ጋር በቀጥታ ስለሚያያዙ፣ ኢህአዴግ መለካት ያለበት የኢህአዴግ የስታስቲክስ ጽህፈት ቤት በሚያቀርበው ወገንተኛ የእድገት አሃዝ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ አቅሙ፣ ሃብቱና እውቀቱና በነበረው የተመቻቸ ሃገራዊ ሁኔታ በኢህአዴግ ዘመን ሊያከናውን ይችል ከነበረው ተአማኒነት ካለው ግምታዊ የእደገት አሃዝ አኳያ ብቻ ነው። 

በመጽሃፉ የተለያዩ ገጾች አብይ ሃገሪቱ በከንቱ ስላባከነቻቸው እድሎች በቁጭት የጻፈ ቢሆንም ይህ ቁጭት የኢህአዴግን ተጨባጭ ክንዋኔዎች መለኪያ ሆኖ አይቀርብም።

ሌላ አንድ ምሳሌ ልጨምር።

በግለሰቦችና በቡድን መብቶች ቀዳሚነት በሚደረገው ሙግት ዙሪያ “የግለሰብ መብት ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል” የሚሉ ወገኖችን ሃሳብ በተሟላ መንገድ በመጽሃፉ የቀረበበት ሁኔታ አይታይም።

በተለይ የግለሰብ መብት ተሟጋቾች “ለቡድን መብት ለመቆም መሰባሰብ የሚቻለው ለቡድን መብት የሚቆረቆሩ ግለሰቦች በቅድሚያ መብታቸው ተከብሮ ለቡድን መብት የሚቆም ማህበራዊ እንቅሳቅሴ ሲጀምሩና ድርጅት ሲፈጥሩ መሆኑን፣ ከዛም አልፎ በቡድን መብት በቆመው ድርጅት ውስጥም የግለሰቦች መብት ካልተከበረ “የቡድን መብት አስከባሪ ነን” የሚሉ መሪዎች፣ በእውን የቡድኑን መብት እያስከበሩ እንደሆነ መጠየቅ፣ በቡድኑ ውስጥ የሚነሱ ሌሎች የቡድን መብቶች ጥያቄ ማቅረብ የማይቻልበት፣ አባላቱ የቡድኑን እንቅስቃሴ በነጻነት መፈተሽ የማይችሉበት አፋኝ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል” በማለት ለሚያቀርቡት ክርክር ዶ/ር አብይ ቦታ አልሰጠውም። 

“የቡድን መብቶች መከበር የግለሰቦችን መብት እንደማያስከብር፣ እንዳውም በቡድን መብት ማስከበር ስም የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ትልቁ አደጋቸው የግለሰቦችን መብት፣ የሌሎችን ቡድኖች መብት የመጨፍለቅ አደጋ መሆኑ ስፋት ካለው የሰው ልጆች ተመክሮ የሚያቀርቡትን መከራከሪያ ጸሃፊው አይመለከተውም። የሃገራችንም ተመክሮ የሚያረጋግጠው ይህንኑ ሃቅ መሆኑ በአብይ እውቅና አልተቸረውም።

በተቃራኒው የግለሰቦች መብት መከበር ግን በተደራጀ መንገድ የቡድን መብት ለማስከበር ለሚንቀሳቅሱ በሩን እንደሚከፍት፣ ከዛም አልፎ የቡድን መብት በሚገባ ለመከበሩ ከቡድኑ ውስጥም ይሁን ከቡድኑ ውጭ የሚገጥሙትን ተግዳረቶች ለመፍታት የግለሰብ መብት መከበር ወሳኝ መሆኑን በምክንያት ላይ ተመስርቶ ለሚቀርበው ክርክር በአብይ ቦታ አይሰጠውም። እንዳውም ዶ/ር አብይ “የግለሰብ መብት አቀንቃኞች የቡድን ማንነትን በማጥፋት … ጭቆናንውን የሚያድበሰብስና የጭቆና ቅሪትን የሚተው…” በሚል የግለሰብ መብት መቅደም አለበት የሚሉትን ከሚዛናዊነት በራቀ አቀራረብ ይተቻቸዋል። (መደመር ገጽ 90)

በኔ እይታ ከላይ ያቀረብኳቸው ሁለት ምሳሌዎች ላይ የታዩት የአቀራረብ ድከመቶች አብይ የክርክር ጭብጦችን በደንብ ስላልተረዳ ያለፋቸው መስሎ አልታየኝም። በመጀመሪያው ምሳሌ ችግሩ አብይ ከኢሃአዴግ ጋር በመስራት ለድርጅቱ ከነበረው ቅርበት ከውጭ ሆኖ እንደሚያይ ሰው በፍጹም ነጻነት ኢህአዴግን ለማየት ካለመቻል የመጣ ይመስላል።

እራሱ አብይ እንደጻፈው ኢህአዴግ ከልጅነቱ ጀምሮ መላው ህይወቱን ያሳላፈበት፣ ልምድም፣ እውቀትም የገበየበት፣ ራሱም የወጣትነት ጉልበቱንና እውቅቱን ኢንቨስት ያደርገበት ድርጅት ከመሆን ጋር የተያያዘ ከስሜት ተላቆ ያላለቀ አመለካከት ውጤት ይመስላል። (“የመደመር መንገድ”፣ “ሰሚ ፈለጋ” በሚለው ርእስ ስር ገጽ 5 የአብይና የኢህአዴግ ቁርኝት ምን ያህል ጥብቅ እንደሆነ ከፖለቲካ ሀሁ ቆጠራ ከምንዝር እስከ አለቃነት ያደረሰውን የስራ ተመክሮዎች በዚህ ድርጅት ውስጥ ማግኘቱን በበጎ ትውስታ -with fondness – መልኩ ጽፎታል)

ሌላው ምሳሌ፣ የግለሰብን መብት በተመለከተ ያቀረብኩት ምሳሌ፣ አብይ እውቅና ከሚሰጠው የኢህአዴግ በጎ የፖለቲካ ክንዋኔ ከሚለው ብሄር ተኮር ህገ መንግስት፣ ብሄር ተኮር ፌደራሊዝምና የፖለቲካ አደረጃጃት ጋር የተያያዘ ይመስላል።

አብይ የኢህአዴግ ህገ መንግስት፣ የዘር ፌደራላዊ አስተዳደር፣ ዝግ የዘር የፖለቲካ የኢኮኖሚና ማህበራዊ አደረጃጀት “እውን በዚህ ሃገር ውስጥ ብዝሃንነት ያስጠበቀ፣ ለቡድኖች መብት መከበር ጥያቄ መፍትሄ የሰጠ ወይንስ ሁሉም ተያይዞ ወደሚጠፋፋበት የዘሮች ፍጥጫ የሚወስድ የጥፋት መንገድ” የሚል ጥያቄ አያነሳም። “መደመር” ከገጽ 116-117 ላይ የቀረበው ሰፋ ያለ ሃተታ ህገ መንግስቱ የብሄረሰቦችን መሰረታዊ መብቶች ያስጠበቀ፣ የሚጎደሉት ነገሮች የአፈጻጸም እንጂ የፖሊሲ ችግር እንደሌለበት የሚገልጽ ነው። 

በዚሁ መጽሃፍ  ገጽ 117 ላይ አብይ፣ የአፈጻጽም የሚላቸውን ችግሮች ለመፍታት ከለወጡ በኋላ “የተወሰዱት “የዴሞክራሲያዊ ማሻሻያ እርምጃዎች” ያበረከቱትን አስተዋጸኦ “ሃገራዊ መግባባትን በማጠናከር ሰላማችንን ያመጡ ናቸው” ይለናል። አዎን መደመር በተጻፈበት ወቅት የነበረው ሃገራዊ ሁኔታ ይህን ቢመስልም፣ መደመር የተጻፈበት ቀለም ሳይደርቅ፣ በሃገሪቱ የተከሰቱ ሁኔታዎች ግን ይህን አባባል ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ ናቸው።

አብይ ኢህአዴግን ለመመዘን ከወጭ ተመልካች ይልቅ “ቤተኛ ባይተዋር” መሆኑ የተሻለ አቅም እንደሚሰጠው ቢያቀርብም (የመደመር መንገድ ገጽ 25) ከዚህ በላይ ባቅረብኳቸው ሁለት ምሳሌዎች እይታ አብይ ከባይተዋርነቱ ይልቅ ቤተኛነቱ በማየሉ የኢህአዴግን መሰረታዊ ጉድለቶች ማየት እንዳይችል አድርጎታል ለማለት ተገድጃለሁ። ምክንያቱ ይህ ሊሆን አይችልም ብለው ለሚጠረጥሩ ሌላው ምክንያት መሆን የሚችለው የሚቀጥለው ብቻ ነው።

ችግሩ የወቅቱ የአብይ የፖለቲካ ስልጣን የቆመበት መሰረትና በወያኔ ዘመን በተሟላ የመንግስት ድጋፍ፣  ስር እንዲሰድ የተደረገው ዘርን ተኮር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ በቀላሉ መጋፋት የሚችሉት እንዳልሆነ ከመረዳት ከመጣ የፖለቲካ ስሌት ጋር የተገናኘ ይመስለኛል። አብይ በመጽሃፉ ብዙ ነገሮችን ያየበትን ስፋትና ጥልቀት ለተመለከተ አንባቢ፣ ከላይ ባቀረብኳቸው ምሳሌዎች ዙሪያ ጸሃፊው የወሰዳቸው አቋሞች “ከእውቀትና ተመክሮ ማነስ የመነጩ ናቸው” ብሎ ለመቀበል ይከብደዋል። እነዚህ ምሳሌዎች ቁልፍ የሆነውን የሃገሪቱን አንኳር የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጉዳዮች የሚመለከቱ መሆናቸው ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል።

ይህንንም ብዬ ግን መጽሃፉ የሌሎችን ግለሰቦችን እና ቡድኖች ሃሳቦችና አመለካከቶች በተቻለው መጠን ሃቅን ተመርኩዞ በገለልተኛነት ለማቅረብ የሄደበት ከፍታ በጎ ለሆነ በሚዛናዊነት ላይ ለተመሰረተ የተዋስኦ ባህል ማበረታቻ ሆኖ እንዲታይ ያደርገዋል።

– “የመደመር መንገድ”ን የስነ ጽሁፍ ውበት አለማድነቅ አይቻልም። የዶ/ር አብይ የጸሃፊነት ክህሎት የታየበት መጽሃፍ ነው። ከዛም አልፎ ጸሃፊው በሃገራችን የተንሰራፋውን የማንበብ ባህል ችግር በመረዳት አንባቢን ለመሳብ በርካታ ቁምነገሮችን እያዋዛ በመጻፉ፣ መጽሃፉን ተነባቢ ለማድረግ ያደረገው ጥረት ተሳክቶለታል የሚል እምነት አለኝ። ለሌሎች በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ለመጻፍ ለሚፈልጉ ጸሃፍት በጎ ምሳሌ ሊሆን ይችላል።

– ከይዘት ወጭ ያልኩትን ዳሰሳ ሳሳርግ፣ አንድ መጽሃፍ ሲዳሰስ መጽሃፉ የተገለጸባቸው እጅግ በርካታ ጥንካሬዎች እያሉት ጥቂት ድክመቶች ላይ አተኩሮ መጽሃፉን በድክመት የተሞላ አድርጎ የማቅረብ ሌላው ከአድርባይነት የመጽሃፍ ዳሰሳ ባህላችን በተቃራኒው የቆመው አፍራሽ የዳሰሳ ባህላችን ነው። ይህ ባህል ሊታረም የሚገባው ባህል ነው። ከዚህ እይታ በመነሳት የዶ/ር አብይ መጽሃፎች ከይዘት ውጭ ባሉት መመዘኛዎች እጅግ የተዋጣላቸው ናቸው ማለት ይቻላል። ቀጥሎ የማልፈው ወደ ይዘት ዳሰሳ ነው።

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top