Connect with us

የሁለቱ መደመሮች የመጽሃፍት ዳሰሳ

የሁለቱ መደመሮች የመጽሃፍት ዳሰሳ
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

የሁለቱ መደመሮች የመጽሃፍት ዳሰሳ

የሁለቱ መደመሮች የመጽሃፍት ዳሰሳ

ክፍል 2 (አንዳርጋቸው ፅጌ)

5 የይዘት ዳሰሳ

የይዘት ዳሰሳውን መልክ ለማስያዝ እንዲሁም የአንባቢንም ስራ ለማቅለል የእነዚህን ሁለት መጽሃፍት ዳሰሳ በአንድ መሰረታዊ ቁም ነገር ዙሪያ ማድረግ ተገቢ ነው። እንዴት ሁለት መጽሃፎች በአንድ መሰረታዊ ቁም ነገር ዙሪያ ማድረግ ይቻላል ለምትሉ፤ መልሴ እነሆ።

እነዚህ ሁለት መጽሃፎች ከርእሳቸው ተመሳሳይነት ባሻገር “መደመር” የሚለውን ቃል ወሳኝ ቃል በማድረግ በርካታ ጉዳዮች የሚተነተኑባቸው ችግሮች የሚፈተሹባቸው፣ መፍትሄዎች የሚጠቆሙባቸው ሆነዋል። “የመደመር መንገድ” ያስፈለገበት ምክንያት “መደመር” በሚለው መጽሃፍ ውስጥ ስለመደመር የቀረቡትን እይታዎች የበለጠ  በተለያዩ ንድፈሃሳባዊ ባልሆኑ የስነጽሁፍ አግባቦች በሚቀርቡ የተለያዩ ትረካዎች ማበልጸግ ይቻላል በሚል እምነት ነው። አብይ ይህን በቀጥታ አላለም። 

ቢሆንም የኔ ድምዳሜ ትክክል ለመሆኑ ማስረጃው “የመደመር መንገድ” እንደ “መደመር” መግቢያ ወይም መቅድም የሌለው መጽሃፍ መሆኑ ነው። ይህ ማለት “የመደመር መንገድ” ራሱን “የመደመር” ቅጥያ አድርጎ ስላየው ሌላ መቅድም አላስፈለገውም ማለት ነው። 

ስለዚህም ዶ/ር አብይ “መደመር” የሚለውን መጽሃፉን ለምን እንደጻፈው በግልጽ ያስቀመጠው ወይም ያስቀመጣቸው አላማዎች ለ”የመደመር መንገድ”ም የሚሰሩ አላማዎች ናቸው።  እነዚህ አላማዎች ምንድን ናቸው? አላማውን ወይም አላማዎቹን  አሳክቷል ወይ?

የተለያዩ ጸሃፍት የተለያዩ ግቦች አንግበው በመነሳት መጽሃፍት ይጽፋሉ። ለዚህ ግብ የሚያዋጣውን የአጻጻፍ ስልት ወይም አይነት ይመርጣሉ። ትልቁ ጥያቄ ጸሃፍቱ በቅርጽና በይዘት በግልጽ ወይም በውስጠ ታዋቂነት ያስቀመጧቸውን ግቦች በመምታት ተሳክቶላቸዋል ወይ ነው። የሁለቱን መደመሮች ጥንካሬና ድክመት ለመፈትሽ የወሰንኩት ከዚህ ቅኝት አኳያ ነው። 

በቅርጽ ወይም አቀራረብ የሚለውን ጉዳይ ከይዘት ወጭ በሚለው ርእስ ስር ቀደም ብለን አይተነዋል።  አብይ በዚህ ረገድ በሚገባ ተሳክቶለታል። የሚቀረን የይዘት ዳሰሳው ነው። ከባዱ ክፍልም ይህ ነው።

4.1. በቅድሚያ “መደመር” ን በተመለከተ

የ”መደመር” መጽሃፍን ስኬት ለመለካት የምንጀመረው አብይ ይህን መጽሃፍ ለመጻፍ ባነሳሱት ምክንያቶች እና ለማሳካት ባሰባቸው ግቦች ላይ በመመስረት ነው። ወደ እዚህ ቁምነገር በዝርዝር ከመግባታችን በፊት በይዘት ደረጃ መጽሃፉ ያነሳቸውን ሌሎች ቁምነገሮች ለአንባቢ ገልጾ ማለፍ ፍትሃዊ ይመስለኛል።

መጽሃፉ በሚያስገርም መልኩ የተነጣጠሉ ነገር ግን እርስ በርሳቸው የተጎናጎኑ ጉዳዮችን ያነሳል። የመጽሃፉ አደረጃጃትም ይህንኑ በተያያዥነትና በተናጠል የሚቀርቡ ጉዳዮችን አስመልክቶ የተደራጀ ነው። መሰረታዊ ክፍሎቹ 4 ሲሆኑ እነዚህ ክፍሎች ደግሞ በ16 ምእራፎች ተከፍለዋል።

ከላይ በገለጽኩት ምክንያት እያንዳንዱን ምእራፍ የሚመለከት ዳሰሳ ማቅረብ አያስፈልግም። ምእራፎቹ በሙሉ “መደመርን” የበለጠ ለማበልጸግና ለማብራራት የቀረቡ ስለሆኑ ዳሰሳው ትኩረቱ ራሱ መደመር ላይ ቢሆን ተገቢ ይሆናል። ይህን ብዬም አንባቢ እየአንዳንዱን ምእራፍ በጥንቃቄ ቢያነብ ብዙ እውቀት እንደሚገበይ ለመጠቆም እወዳለሁ። ጥቆማየን ለማጠናከር ወደ ዋናው የዳሰሳዬ እምብርት ከመሸጋገሬ በፊት የመጻሃፉን 4 ክፍሎች በወፍ በረራ መልኩ ወደ መቃኘት እሸጋገራልሁ። 

4.2. ክፍል 1 የመደመር እሳቤ መነሻ ሃሳቦች

ከመጽሃፉ አራት ክፍሎች፣ የመጀመሪያ ክፍል “መደመር” የሚለውን ነገር ዶ/ር አብይ ለማብራራት የተጠቀመበት ክፍል ነው። “ነገር” ያልኩት ሌላ ቃል በመጠቀም ለ”መደመር” ያልሆነውን ትርጉም ላለመስጠት ጥንቃቄ ለማድረግ ነው። ወደፊት እንደምናየው መደመር ብዙ ትርጉም አለውና።

የመጀመሪያው ክፍል የመጽሃፉን ቁልፍ ወይም ገዢ ቃል በማብራራት፣ ስርወ መሰረቱን በመግለጽ እንደ ጽንጸ ቃል “መደመር” ያደገባቸውን የተለያዩ ሁኔታዎች ሂደቶችና ደረጃዎች ለመግለጽ በስራ ላይ የዋለው ክፍል ነው።

የመጽሃፉን ቁልፍ ቃል መግለጽ ቀዳሚ ተግባር አድርጎ አብይ መውሰዱ ሌሎችን ክፍሎችና ምእራፎች በቀላሉ ለመከታተል የሚጠቅም በመሆኑ ትክክለኛ አካሄድ ነው። በአንዳንድ የፍልስፍና አስተምርሆዎች በቃላት ትርጉምና አጠቃቀም ላይ ግልጽነትና ስምምነት እንዲኖር ማድረግ የፍልስፍና ተዋስኦ መሰረት ተደርጎ ስለሚወሰድ አብይ መደመርን በመግለጽ መጀመሩ፣ ቃሉ ፍልስፍናዊ ትርጉም እንደተሰጠው አመላካች ነው። ትልቁ ጥያቄ፣ በዚህ ክፍል መደመር ምን እንደሆነ ዶ/ር አብይ  ማሳየት ችሏል ወይ?”

ይህን ገዥ ቃል በሚቀጥሉት የመጽሃፉ ክፍሎች በተደጋጋሚ ስራ ላይ ውሎ እናገኘዋለን። “መደመር” በመደመር ቅኝት ይታያሉ የተባሉ ጉዳዮችን ማሳያ ሆኖ እናገኘዋለን ወይ? በተለይ “መደመር” ጸሃፊው እንደተመኘው፣ እንደ ህዝብ እና እንደ ሃገር ከገባንበት አደገኛ ቅርቃር ሊያወጣን የሚችል አዲስ የአተያይ ግኝት ሆኖ ማየት ችለናል ወይ?

የደራሲውም ትልቅ ትኩረት “መደመርን” ለችግሮቻችን ፈውስ እንደ ተአምራዊ ኪኒን (Magic Bullet) የማቅረብ በመሆኑ የመጽሃፉ ጥንካሬ ወይም ድክመት ዋናው መለኪያ ከዚህ ቃል ጋር የተያያዘ ሆኗል። አብይ በ “የመደመር መንገድ” ገጽ 62 ላይ “መደመር ሃገራዊ ተአምር መስራት ይችላል” ይለናል። አንባቢዎችም ሳንወድ በግድ የመጽሃፉን ዳሰሳ ዋና ትኩርት እዚህ ጉዳይ ላይ እንድናደርግ አድርጎናል።

4.3. የ “መደመር” ክፍል 2 የሃገራችን የፖለቲካ ስብራትን የጥገና አማራጮች እና ክፍል 3 የሃገራችን የኢኮኖሚ ስርአት ስብራትና የጥገና አማራጮች፤

ከአራቱ የመጽሃፉ ክፍሎች ሁለቱ ክፍሎች የሃገራችንን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስብራቶች የሚመረመሩ ናቸው።

እነዚህ ሁለት ክፍሎች በተለይ የኢትዮጵያ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስብራቶች የቀረቡባቸውና መፍትሄ የተጠቆሙባቸው ዝርዝር ጉዳዮችን አካተዋል።

የፖለቲካ ችግሮቻችን አጥጋቢ በሚል ደረጃ ቀርበዋል። የኢኮኖሚ ችግሮቻችንም እንደዚሁ። መፍትሄዎቻቸውም በመጽሃፉ ማህቀፍ ውስጥ ሲታዩ በዝርዝር ቀርበዋል። እነዚህ ሁለት ክፍሎች ውስጥ በቀረቡ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ዙሪያ የተለያዩ ሙያተኞች የራሳቸውን አስተያየቶች መስጠት የሚችሉባቸው በርካታ ነጥቦች አሉ።

የታሪክ ሰዎች ከታሪክ አኳያ፣ የፖለቲካ ሰዎች ከፖለቲካ አኳያ፣ የመንግስት አስተዳደር ባለሙያዎች ከመንግስት አስተዳደር አኳያ፣ የሌሎችም የእውቀት ዘርፎች ባላሙያዎችም በየሙያው ዘርፍ በተነሱ ጉዳዮች ዙሪያ ብዙ ማለት ይችላሉ። ኢኮኖሚስቶች፣ ከተለያዩ የኢኮኖሚ ንድፈሃሳቦች አንስቶ፣ በዝርዝር የኢኮኖሚ መስኮች፣ ግብርናን፤ ንግድን፣ ፋይናንስን፣ ኢንዱስትሪ፣ ቴክኖሎጂና ወዘተ በመሰሉ ጉዳዮች ላይ አብይ ባቀረባቸው ምልከታዎች ላይ በበጎም ወይም በአሉታዊም መንገድ በርካታ አስተያየቶችን መስጠት ይችላሉ።

4.4. መደመርና የውጭ ግንኙነት

አራተኛው ክፍል ዶ/ር አብይ የፖለቲካ ተንታኝ ብቻ ሳይሆን የሃገርና የፖለቲካ መሪ ጭምር በመሆኑ የገባ የሚመስል ነገር አለው። ይህ የመጨረሻ ክፍል የሚጠቁመው ነገር ዶ/ር አብይ መጽሃፉን ሲጽፍ የብልጽግና ፓርቲን በአንድ አይኑ እያየ እንደሆነ ነው። 

እንዳውም ከዚህ የመጽሃፉ የመጨረሻ ክፍል ተነሰተን ወደኋላ መጽሃፉን ስንቃኝ “መደመር” በአንድ በኩል እንደ አንድ አዲስ ፖለቲካ ፍልስፍና፣  በሌላ በኩል እንደ አንድ የፖለቲካ ድርጅት የፖሊሲ አቅጣጫዎች መጠቆሚያነት ታስቦ የተጻፈ ሆኖ እናገኘዋለን። የብልጽግና ፓርቲ መሪዎችን እና አባላትን የማስተማሪያ መጽሃፍ እንዲሆንም ጭምር ታስቦ የተዘጋጀ ቢሆን አይገርምም።

ብልጽግና ከኢህአዴግ በአደረጃጀት ብቻ ሳይሆን፣ በርእዮተ አለም ደረጃ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጋር ተፋትቼያለሁ እስካለ ድረስ አብዮታዊ ዴሞክራሲን በምን እንደተካው መግለጽ አለበት። የአብይ ድካም ይህንን ጉዳይ ግምት ውስጥ ያስገባ ይመስላል። ቀደም ብለን እንዳየነው “የመደመር መንገድ” የሚለው ሁለተኛው መጽሃፍ የመጨረሻው ክፍል ያለቦታው የገባ ከሚመስል ከብልጽግና ፓርቲ ጋር በቀጥታ በተገናኘ ጽሁፍ መዘጋቱ አብይ በአንድ አይኑ ብልጽግናን እያሰበ መጽሃፎቹን ጽፏቸዋል ለሚለው ግምቴ ተጨማሪ ማስረጃ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ። 

ከዚህ በላይ የጻፍኳቸውን ጥቂት መስመሮች ለመጻፍ ለምን እንደፈለግሁ ልግለጽ።

የወጭ ጉዳይ ችግራችን እንደ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ችግሮቻችን የሃገሪቱን እና የህዝቧን ህይወት በሁለንተናዊ መልኩ የሚነካ ችግር ነው የሚል እምነት የለኝም። ይህን ስል “ኢትዮጵያ በጣም ስሱ በሆነ ጂኦ ፖለቲካዊ አካባቢ የምትገኝ፣ ከሌሎች የቅርብና የሩቅ ሃገሮች ጋር የሚኖራትን ግንኙነቶች በጥንቃቄና በተጠና ፖሊሲ አማካይነት መምራት የለባትም እያልኩ” አይደለም። 

“ኢትዮጵያን ከውጭ መንግስታት ጋር የሚኖራትን ግንኙነት በዋንኛነት የሚወሰነው በሃገራችን ውስጥ በሚኖረን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬና ወይም ድክመት ላይ ነው” ለማለት ነው። የውስጥ ችግር የሌለባት ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ የሚገጥማት ችግር አሳሳቢ አይሆንም።

ሌላው ምክንያቴ፣ በሌሎቹ ሁለት ክፍሎች የመደመር ሃሳብ በቁልፍ ማብራሪያነት በቀረበበት ደረጃ ለውጭ ጉዳይ እምብዛም አስፈላጊ ሆኖ አለመታየቱ ነው። የወጭ ጉዳይ ፖሊሲ አቅጣጫ ከመደመር እሳቤ አኳያ እንዲታይ የሚያመላክት ነገር ቢኖርም “ መደመርን” ከሚገባው በላይ በመለጠጥ የተደረገ ጥረት የሚመስል ነገር አለው።

የተቀመጠው የውጭ ጉዳይ የፖሊሲ አቅጣጫ ያለመደመር እሳቤ፣ በተለመዱት የመልካም ጉርብትና፣ የትብብር፣ የጋራ ደህንነትና ጥቅም ማስጠበቅ ወዘተ በሚሉ እሳቤዎች መቅረብ ይችል ነበር የሚል እምነት አለኝ። እነዚህ እሳቤዎች ከመደመር በፊት የነበሩ ስለሆነ ያለመደመርም ለውጭ ጓዳይ ፖሊሲ መቅረጫነት ሊያገለግሉ ይችሉ ነበር።    

አንድ ሃገር በደንብ የታሰበበት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንዲኖረው ማድረግ የግድ ነው። በዚህ ክፍል ውጭ ጉዳይን በተመለከተ በዶ/ር አብይ የቀረቡት ምልከታዎች በንድፈሃሳብ ብቃትና በተግባራዊ መስኩም አንባቢን የሚያስታጥቁት በርካታ ጥሩ ሃሳቦች አሉት።

በዚህ ከፍል ውስጥ በተነሱት ጉዳዮች ላይም የአለምአቀፍ ግንኙነት ሙያተኞች “መደመር እና የወጭ ግንኙነት” በተመለከተ  መደመር የሚለውን ቃል ወደ ጎን አስቀምጠው ቢያነቡት የሚስማሙባቸውና የማይስማሙባቸው ነጥቦች እንደሚኖሩ መገመት ይቻላል። 

ያም ሆኖ አብይ ስፋት ያለውን ወቅታዊ አለም አቀፍ ሁኔታ በትንሽ ገጾች በአግባቡ ጨምቆ “ኢትዮጵያ በዚህ አለም አቀፋዊ ሁኔታ ውስጥ የውጭ ግንኙነቷ ምን ሊሆን ይገባዋል” ለሚለው ጥያቄ የሰጠው ምላሽ፣ ለሃገሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ስብራቶች መጠገኛነት ከሰጣቸው ምላሾች ጋር ተደምሮ ጸሃፊው የዋዛ ፖለቲከኛ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ የመደመር መጽሃፎች አብይ ሊያላብሳቸው የፈለገው የፍልስፍና ገጽታ ቀርቶባቸው በንጹህ የፖለቲካ ጽሁፍነት ከተመዘኑ እስከ ዛሬ ድረስ በሃገሪቱ ታዋቂ የፖለቲካ መሪዎች ከተጻፉት የፖለቲካ መጻህፍት የላቁ ናቸው። ችግሩ አብይ የፖለቲካ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ፍልስፍና መጽሃፎች አድርጎ ስላቀረባቸው ከዚያ አኳያ ሲዳሰሱ ውስኑነት የሚታይባቸው መጽሃፍት መሆናቸው ነው። እኔም የምሸጋገረው ወደዚሁ ዳሰሳ ነው።

  1. “መደመር”  በሁለቱ መጽሃፎች ትልቅ ክብደት የተሰጠው ቃል!

የአብይን ሁለቱን የመደመር መጽሃፎች ለመዳሰስ የሚነሳ ማንም የምር ሃያሲ “መደመር” የሚለው ቃል በመጽሃፉ ውስጥ የተሰጠውን ማእከላዊ ቦታ ሳያጤንና አስተያየቱ ሳይዘነዝር ማለፍ አይችልም። የመጽሃፎቹ ዋልታና ማገር “መደመር” ነው። የመጽሃፎቹ መሰረታዊ ጥንካሬ ወይም ድክመት የሚለካ ከሆነ  “መደመር”ን በተመለከተ ከሚኖረው ጥንካሬና ድክመት  ነው። 

ስለመጽሃፉ ከላይ ያቀረብኳቸው እጅግ ብዙ ጠንካራ ጎኖች እንዳሉ ሆኖም ዶ/ር አብይ ይህን ቃል ማእከላዊና ተአምራዊ ትርጉም የሰጠው በመሆኑ በዋንኛነት መጽሃፉን እንድንመዝንለት የፈለገው ከዚህ ቃል ጋር በተያያዘ ነገሮችን ያየበትን የእይታ ትክክለኛነትና አጥጋቢነት ነው።

5.1. የ”መደመር” ሃሳብ መነሻ

አብይ መደመርን ተራ ከሆነ የመደራረብ፣ የማከል፣ የመጨመር ቃል ወደ ላቀ ጽንሰ ቃል  (concept) አሳድጎ እንዲያይ ያደረጉትን ነጥቦች  በ”መደመር” መቅድም ይዘረዝራቸዋል።

ጸሃፊው በልጅነት እድሜ ተፈጥሮን በተመለከተ የነበረ የደመነፍስ ግንዛቤ፣ የማህበረሰብ ባህሎችን ማጤን፣ ከስራ አለም ከተገኘ ልምድና ተመክሮ፣ የሃገራችን የረጅም ዘመን ታሪክ ከማጥናት፣ የሰውን ልጅ ስነልቦናዊ ስሪቶች ከመመርመር፣ በሰውን ልጅ ተፈጥሮና የራሱ የጸሃፊው የግል ህይወት ላይ ከተደረጉ ማሰላስሎች በመነሳት ከተገኘ እውቀት መደምርን ከተራ ቃል ወደ ላቀ ጽንሰ ቃል አሳድጎ እንዲያየው እንዳደረገው ገልጾልናል። የሁለቱም መጽሃፎች የመጀመሪያዎቹ ገጾች የሚያተኩሩት በአብይ ውስጥ “የመደመር ሃሳብ” እንዲያድግ ባደረጉ ኩነቶች ላይ ነው።  ይህ መንደርደሪያ ግልጽና የማያሻማ ነው።

5.2. መደመር ምንድን ነው?

ከዚህ በላይ ከቀረበው መንደርደሪያ አንባቢ የሚጠብቀው  በመግቢያው ከተዘረዘሩት ተመክሮችዎችና ማሰላሰሎችና ወዘተ በመነሳት ለመደመር የተሰጠ የማያሻማ አገላለጽና የቃሉ አጠቃቀም ነው። የመጽሃፉ  አጠቃላይ ጥንካሬ ሸብረክ ማለት የሚጀምረው እዚህ ላይ ነው።

ከ”መደመር” ገጽ V ጀምሮ የመደመር ትርጉም ወደ አንድ መሰባስቡን ትቶ መሰነጣጠቅ ይጀምራል።  መደመር አስተሳሰብ (way of thinking) ፍልስፍና፣ እሳቤ፣ ርእዮተ አለም፣ አተያይ (perspective)፣ መርህ፣ እሴት፣ ተራ መተባበር፣ አንድነት፣ መከማቸት፣ መሰብሰብ፣ የበጎ ባህርይ መገለጫ፣ ብያኔ፣ የላቀ ድምር (synergy) የሚሉ የተለያዩ ትርጉሞች እየተላበሰ እስከ መጻሃፉ መጨረሻ ይቀጥላል።

በመደመር ፍልስፍና በመደመር እሳቤ፣ በመደመር መርህ፣ በመደመር ብያኔ ወዘተ የሚሉ አገላለጾች በሁሉምና በሁለቱም  የመጽሃፉ ገጾች በተደጋጋሚ ይገኛሉ። በመሆኑም ለማስረጃነት ገጽ መጥቀሱ አስፈላጊ አይደለም።

አንዱ የ”መደመር” ድክመት ለመደመር አንድ ጠንካራ ግልጽ የሆነ ትርጉም ሰጥቶ ከመጽሃፉ መጀመሪያ እስከ መጨረሻ ይህ አጠቃቀም በስራ መዋል አለመቻሉ ነው። ይህ ባለመሆኑ መደመር ዶ/ር አብይ እንደተመኘው በራሱ መቆም የቻለ የፖለቲካ ፍልስፍና ሊሆን አልቻለም።

መደመር ግልጽ የሆነ የፍልስፍና ትርጉምና አጠቃቀም ያለው ቃል ቢሆን ኖሮ መጽሃፉ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ የሚያነሳቸውን ጉዳዮች በዚህ ፍልስፍና እይታ እየተመለከተ የሚቀጥል መሆን ይችል ነበር። (ይህ የመጀመሪያው መጽሃፍ ድክመት ወደ ሁለተኛው መጽሃፍ በቀጥታ ተዛውሯል። ሁለተኛው መጽሃፍ የወረሰው የመደመር ትርጉም ከአንደኛው የመጣ በመሆኑ። )

ለፍልስፍና ጽሁፍ ስኬት አንዱ ቁልፍ መለኪያ፣ የጽንጸ ቃል ወይም የጽንሰ ሃሳብ አጠቃቀም ቀጣይነትና ወጥነት ያለው ትርጉም ማላበስ ነው። አብይ ይህን ማድረግ ችሎ ቢሆን መደመር ራሱን የቻለ የአስተሳብ መሰባሰቢያ (school of thought) ይሆን ነበር። ጥሩ የአስተሳሰብ መሰባሰቢያ ከሆነ ደግሞ አድማሳዊ ጉልበት ስለሚኖረው እንደ ፖለቲካ ፍልስፍና በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ውጭም በአስተሳሰብ ማሰባሰቢያነቱ ለአፍሪካም ፋይዳው የጎላ የፖለቲካ ፍልስፍና ይሆን ነበር።  ይህ አልሆነም።

በዚህ የተነሳ ዶ/ር አብይ በፈላስፋ እይታ የጀመረው ጽሁፍ በሂደት፣ በአንድ የፖለቲካ መሪ፣ በአንድ ቴክኖክራት፣ በዩኒቨርስቲ መምህር፣ በሰባኪ፣ በስነምግባር አስተማሪ፣ በአነቃቂ ተናጋሪ፣ እንደሚዘጋጁ የተለያዩ ጽሁፎች የተለያዩ ገጽታዎች ያለው ሆኗል። ዶ/ር አብይ (መደመር ገጽ V ላይ) እንደነገረን ብዙዎቹ ጽሁፎች በዚህ አይነቱ መንገድ ተዘጋጅተው የነበሩ የማሰልጠኛና የማስተማሪያ ጽሁፎች መሆናቸው ለትዝብቴ ትክክለኛለት ተጨማሪ ማረጋገጫ ነው። 

5.3. የ“መደመር” ፋይዳ ፤

በመጀመሪያው መጽሃፍ፣ በፖለቲካ ጉዳይ ላይ የቀረበው ጽሁፍ መደመር የሚለው ቃል ሳይገባበት በአንድ የበሰለ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር፣ ወይም ብቁ ፖለቲከኛ ሊቀርብ ከሚችለው ልዩነት የሌለው ሆኗል። በተመሳሳይም በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ የተጻፈው ጽሁፍ በአንድ ብቁ የፖለቲካ ኢኮኖሚስት ወይም ቴክኖክራት ሊጻፍ የሚችል ሆኗል።

ዶ/ር አብይ በፖለቲካ እንደ ሃገርና ህዝብ የገባንባቸው ችግሮች በደንብ ዘርዝሯቸዋል። በመፍትሄነት ያስቀመጣቸው ነጥቦች በርካታ ናቸው።

ርእዮተአለም ይሁን ቀኖና ከውጭ ቃርመን በማምጣት ከዚህ ቀደም በታሪካችን የሰራነው ስህተት ደግመን እንዳንሰራ ያስጠነቅቀናል። መፍትሄዎቹ በሚገባ ከሃገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የተገናዘቡ፣ ፖሊሲዎቹ በጥናትና ምርምር የተደገፉ በጥልቀት የታሰበባቸው ሊሆኑ እንደሚገባ፣ መዋቅራዊና ተቋማዊ ማሻሻያዎችና ግንባታዎች እንደምንሻ፣ በነዚህ መዋቅሮች ውስጥ ለመስራት የሚመጥኑ በቂ እውቀትና ክህሎት ያላቸው ሰራተኞች እንደሚያስፈልጉ፣ እነዚህ ሰራተኞች ሊኖራቸው የሚገባው የስነምግባር የሞራል ባህርያት  ምን እንደሆኑ ይዘረዝራል።

የኢኮኖሚውና የማህበራዊ ችግሮቻችንም በሚገባ ተዳሰዋል። እዚህ ላይም ቢሆን ለችግሮች ብዙ አይነት መድሃኒቶች ተጠቁመዋል። መፍትሄዎቹ እንደ ፖለቲካው፣ ሃገራዊ ቅኝት ያለው መፍትሄ መሻት፣ የተቋም ግንባታ የመዋቅር ለውጥ ወይም ማሻሻያ፣ የግለሰቦች የእውቀት የክህሎት የሞራል ግንባታ የሚጠይቅ መሆኑ ተዘርዝሯል። በቀረቡት ችግሮችና በተሰነዘሩት መፍትሄዎች ብዙዎቻችን ልዩነት የሚኖረን አይመስለኝም።

እነዚህ መፍትሄዎች መሃል “መደመርን” የምናገኘው፣ ተቋማዊና መዋቅራዊ መስተጋብር የሚያስፈልጋቸው ነገሮች፣ እርስ በርሳቸው ተቀናጅተው ተሰናስነው በመስራት ስለሚያስገኘው ጠቀሜታ ዶ/ር አብይ ከሚሰጠው አስተያያት ጋር ተያያዞ ነው። በግልሰቦች በቡድኖች መሃከል የሚደረግ መስተጋብር ጥላቻን ትቶ በፍቅር፣ መጠላለፍ ትቶ በትብብር፣ መከፋፋልን ትቶ በአንድነት ላይ ከሆነ ሃገራችንና እና ማህበረሰባችንን ወደ ከፍታ ማሻገር እንደምንችል በመዘርዝር ነው። ይህ የመደምር ትርጉም በ “የመደመር መንገድ” በሚለው መጽሃፍ በስፋት ስራ ላይ የዋለ ነው። ይህን የመደምር ምልከታም አለመቀበል አይቻልም።

ይሁንና በሁለቱም መጽሃፎች ውስጥ መደመር በስፋት በስራ ላይ የዋለበት አተያይ  በባህላችን ከምናውቃቸው፣ “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር፣ ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሃኒቱ፣ አንድ አይነድ አንድ አይፈርድ፣ አንድ በሬ ስቦ አንድ ሰው አስቦ፣ ጥርስና ከንፈር ሲደጋገፍ ያምር፣ ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ጌጡና ወዘተ ከመሳሰሉ” ተባብሮ በመስራት፣ በመታገል፣ በመምከር፣ በማሰላስል፣ በማጌጥ ስለሚገኘው ማህበራዊ ጠቀሜታ በባህላችን ከምናውቀው እውቀት በላይ የተሻገረ አዲስ ነገር የለበትም። 

እንዲህ አይነት የባህል ሃብት እንዳለን ለረሳነው በማስታወሻነት የሚኖረውን ፋይዳ ግን አሳንሼ አላየሁትም። 

በሌሎች ገጾች (መደመር ገጽ 36) የመደመር ሃሳብ እያፈረሱ እያወደሙ ከዜሮ አለመጀመር ጋር ይያዛል። እዚህ መደመር ተራ ድምር ሆኖ ነው የቀረበው። በነበረው ላይ መደመር ከተደመሩት ነገሮች በላይ የላቀ የመደመር ውጤት የሚያመጣ ስላልሆነ መደመሩ ከተራ ክምችት ማሳደግ የዘለለ አይደለም።

በተበታተነ መንገድ ወደ አንድ ግብ ከመሮጥ በጋራ ወደ አንድ ግብ መሮጥ ያለውን ጠቀሜታ አብይ በሚያስረዳባቸው ቦታዎች መደመር፣ ከተራ ድምር በላይ የላቀ ውጤት የሚያስገኝ ሆኖ ይቀርባል። አንድ እና አንድ ሲደምር ሁለት መሆኑ ቀርቶ ከሁለት በላይ የሚያድገበትን እሳቤ የያዘ አገላለጽ ነው።

ይህ አመለካከት ከዚህ በላይ በጠቅስናቸው ባህላዊ አባባሎች የተገለጸ ማህበራዊ ግንዛቤ ነው። አንድ በሬ ብቻውን ከሚያርስ አንድ ሰውም ብቻውን ከሚያስብ ሁለቱም ሁለት ሁለት ወይም ከዛ በላይ መሆናቸው ከተራ ድምራቸው የላቀ ውጤት ማምጣታቸው በሚገባ ግንዛቤ የተያዘበት ተረትና ምሳሌ ነው። መደመር የእንግሊዝኛውን synergy (ከተራ ድምር በላይ) የሚል ትርጉም ያገኘበት ምሳሌ ነው።

“አንድን ወይፈን ወይንም አንድ አሮጌ በሬ ለብቻቸው እየጠመዱ ከማረስ፣ ገበሬው ወይፈኑን ከአሮጌው በሬ ጋር አቀናጅቶ በመጥመድ ስራውን የሚሰራው የሁለቱ ቅንጅት በጉልበት ብቻ ሳይሆን በልምድና በእውቀት ጭምር ከተራ ድምር በላይ የተሻገረ ውጤት እንዳለው ስለሚያውቅ ነው።” ይህ ምሳሌ በአብይ ሁለተኛው መጽሃፍ በ“የመደመር መንገድ” ውስጥ ተጠቅሷል (ገጽ 22።) ይህ ሆኖ ይህ የላቀ የመደመር እሳቤ፣ ከተራ ድምር በላይ የሚል ትርጉም ያለው እሳቤ በሁለቱም መጽሃፎች ውስጥ በጥቂት ጉዳዮች ላይ ካልሆነ  በስተቀር በመጽሃፉ ውስጥ የቀረቡ በርካታ ጉዳዮችን የሚመለከት ሆኖ አናገኘውም።

ከዚህ ውጭ ለመደምር የተሰጡ ሌሎች ትርጉሞች  በሙሉ ከዚህ በፊት በተለያዩ ሰዎች የተባሉና የተጻፉ፣ በተለያዩ የሃገሪቱ የፖለቲካ ሰዎች፣ ምሁራን፣ የሃይማኖት መሪዎች በተለያዩ አጋጣሚዎች በደጋጋሚ የተነገሩ ናቸው። የአቀራረብ፣ የተቆርቋሪነት ስሜት፣ የዝርዝር ልዩነቶች ካልሆነ በስተቀር ሃሳቦቹን በተደጋጋሚ የሰማናቸው ናቸው። በችግሮች ትንተና እና በመፍትሄዎቹ ፍለጋ ላይ አብይ ከብዙዎቹ የበለጠ የላቀና የጠለቀ ጥረት ያደረገ መሆኑን  ሳንዘነጋ።

5.4. ያለመደመር ያለፉት ዘመናት፣ መጪው ዘመን በመደመር እይታ

የኢትዮጵያ መንግስታት “የሃገሪቱን ችግር እናቃልላን” በሚል ፖሊሲዎች ነድፈዋል። ተቋማት ገንብተዋል ወይም ለመገንባት ሞክረዋል። የሰው ሃይል አሰልጥነዋል። “ሃገር ለማዘመን፣ ድህነት ለመቅረፍ፣ ኢትዮጵያን ወደ ቀድሞ ገናናነቷ ለመለስ” በሚል ብዙ ነገር ለማድረግ ሞክረዋል። ሁሉም በአንድ አይነት ሚዛን የሚለኩ ባይሆኑም።

በኢትዮጵያ ስንት አይነት የፖለቲካ-ኢኮኖሚ ስርአት ነበረ። ንጉስ መር ባላባታዊ የካፒታሊስት ስርአት  የትም የማይወስደን በመሆኑ፣ በሶሻሊዝም ተተካ። ሶሻሊስዝም የትም ሳይወስደን ሲቀር በብሄር ፌደራሊዝምና በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ተተካ። አሁን ደግሞ እድሜው አጭር ቢሆንም፣ ቃሉ በውል በተግባር ሲተረጎም ምን እንደሚመስል ባናውቅም፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ስርአቱ “በመደመር” እሳቤ ወደ ዴሞክራሲና ወደ ብልጽግና እንደሚያመራ እየተነገረን ነው።

በወያኔ ዘመን ብቻ “መልካም አስተዳደር ለማስፈን፣ የተሳለጠ መንግስታዊ አገልግሎት ለህዝብ ለመስጠት ብልጽግና ለማስፈን በሚል ስም ስንት አይነት ፖሊሲዎች ተቀረጹ፣ ስንት አይነት የአሰራር ፈሊጦች (Fads) ተዘረጉ፤ ታጠፉ። ለሰራተኞች የሙያ ማሻሻያ፣ የስነምግባር ማዳበሪያ እየተባለ፣ ስንት ወርክሾፖች፣ አውደ ጥናቶች፣ ስልጠናዎች ተሰጡ። ስንት ነዋይ ፈሰሰባቸው።

አብይ በደንብ እንደሚያውቀው (የመደመር መንገድ ገጽ 6 እና ገጽ 101)  ኢህአዴግ ውስጥ ግምገማ የሚባለው ነገር አላማው በኋላ እየተቀየረ ቢሄድም የድርጅቱን መሪዎችና አባላት በማያቋርጥ የግምገማ ሂደት ህጸጾቻቸው ሳይከማቹ ማረም ነበር። ስንት ሽዎች ግምገማዎች ተካሄዱ። የእነዚህ ግምገማዎች መጨረሻቸው ምን ሆነ?

ሌላው ኢህአዴግ ውስጥ በትግሉ ወቅት ጎልብቶ የነበረ አሰራር ስራን በእቅድ መስራት ነው። ጥቂት የተማሩ የወያኔ አመራሮች በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ ያልተማሩ አባላቶቻቸውን መስመር አስይዞ የሚፈልጉትን ስራ እንዲሰሩ ለማድረግ የማያፈናፍን እቅድ በማዘጋጀትና እቅዱን በቁጥጥር ማስፈጸም ብቻ መሆኑን የተረዱት ገና በማለዳው ነበር። ከቢዝነስ ማኔጀመንት ትምህርት የተወሰዱ ፈሊጦች  በመጠቀም በጣም ጥቂቶች አንድን በቂ እውቀት የሌለውን ሰፊ ሃይል ባሻቸው መንገድ መምራትና የፈለጉትን አጀንዳ ማስፈጸም እንደሚችሉ አረጋግጠዋል።

የኢህአዴግ ተራ ታጋይ አንድ ስራ ሲባል እቅዱ የታለ ብሎ የመጠየቅ የሚያስገረም ልምድ እንደነበረው ይታወቃል። አብይም በኢህአዴግ ውስጥ እሱ እራሱ ያለፈበት ሂደት ነው። ታጋዩ እቅድ ተዘጋጅቶለት፣ በእቅድ ላይ ኦረንቴሽን ( ማብራሪያ) ካልተሰጠው ፈጽሞ በግል ተነሳሽነት ምንም አይነት ስራ የሚሰራ አልነበረም።

ትግሉ ካበቃ በኋላ ሁሉም የኢህአዴግ መሪዎች መለስና ሌሎችም በርካታ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያላጠናቀቁትንም ጨምሮ አንዳቸውም ሳይቀሩ በኮርስፖንደንስ “የተማሩት” ትምህርት ማስተርስ ኦፍ ቢዝነስ አድሚንስትሬሽን (MBA) የሆነው ለዚህ ነው። ያ የቆየ ልምድ፣ የኢህአዴግን ሰዎች፣ ችግሮችን ቴክኒካዊ ብቻ በሆነ መንገድ መፍታት ይቻላል የሚሉ፣ ስፋት ያላቸውን የፖለቲካ የፍልስፍና ጥያቄዎችን ማንሳት አላስፈላጊ አድርጎ የሚያይ ስነ ልቦና ያላቸው መሪዎች እንዲሆን አድርጓቸዋል።

ዛሬ በየመስሪያ ቤቱ በመንግስት ሃላፊነት ከፍተኛ እና ዝቅተኛ ደረጃ የተቀመጠ የቀደሞ የኢህአዴግ ካድሬ፣ ኢህአዴግ በቃል ያስጠናውን የስራ ማከናወያ ፎርማት በቃሉ የማያውቅ የለም። አንድ ወንበር ከአንድ ጥግ ወደሌላው ጥግ ለማንቀሳቀስ የፕሮጀክቱ አላማ፣ ቅደመ ዝግጀት፣ ዝግጅት፣ የሚያስፈልጉ ግብአቶች፣ ስራን በየምእራፉ መቆጣጠሪያ ነጥቦች፣ የስራው ባለቤት፣ ስራ የሚፈጸባቸው ቀናት፣ ውጤት፣ የውጤት መገምገሚያ ነጥቦች ወዘተ የሚል ነገር ሳይደረድር ስራ የሚሰራ አካል ያለ አይመስለኝም። 

ኢትዮጵያ ለስራ ከሚጠፋው ሃብትና ጉልበት ይልቅ ፕሮፖዛልና ፕሮጀከቶች በማሽሞንሞን የሚጠፋው ጉልበት፣ ገንዘብን ጊዜ የሚጠፋባት ሃገር ሆናለች። በየመስሪያ ቤቱ መግቢያ ላይ፣ የተቋሙ ተልእኮ፣ ራእይና መርህ የሚሉ ከመስሪያ ቤቱ የቆሸሸና ህዝብ አንገላታች አሰራራ ጋር የሚጻረሩ፣ ብዙ ገንዘብ የወጣባቸው ቢል ቦርዶች፣ በኢሃዴግ ዘመን የነበሩ የአሰራር ፈሊጦች ለስራ ሳይሆን በባእድ አምልኮት ደረጃ ያደጉ ጣኦቶች ለመሆናቸው ማስረጃዎች ናቸው። ከፈረንጆቹ ተኮርጀው መጥተው ያለቦታቸው የሰነቀርናቸው አጸያፊ ነገሮች ሆነው ነው የሚታዩት። 

“ታማኝነት እንጂ ትምህርት ለሹመት አያስፈልግም” የሚለው የመለስ አባባል ስራን አቅደን ከሰጠነው፣ መቆጣጠሪያውን ካበጀንለት ማንም መሃይም በሚኒስትርነት ቦታ ብናስቀመጠው ስራውን መስራት ይችላል ከሚል በትግሉ ዘመን ተፈትኖ ውጤት አስገኝቷል ከሚባልለት ልምድ የፈለቀ አባባል ነው። 

እንዲህ አይነቱ እንደዶሮ በቀጭን ገመድ የታሰረ ሚኒስቴር ገመዱ ሲላላ ስራውን የማይበድልበት፣ የግል ጥቅም አሳዳጅ የማይሆንበት ምንም የሚያቆመው ነገር እንደሌለ በተግባር ታይቷል። እንዲህ አይነቱ ሚኒስቴር በየቢሮው ተጎልቶ ስራ ተሰራ አልተሰራ፣ መንግስት በሰጠው ላፕ ቶፕና ዋይፋይ አደንዛዥ መዝናኛ ሲኒማ ሲያይ፣ የአለምን አሉባልታ በማህበራዊ ሚድያ ሲያላምጥ ውሎ ያለምንም ህፍረት ከቢሮው ወጥቶ እንደሚሄድ ጸሃይ የሞቀው ሃቅ ነው።

ከዚህ በላይ ያስቀመጥኳቸው ነገሮች እውነት መሆናቸው በዶ/ር አብይ ይታወቃሉ። በዛው ልክ ግምገማው፣ በእቅድ መስራቱም (የፈለገው ድክመት ቢኖርበትም) ችግር ፈችነታቸው እየተዳከመ፣ ችግሮች በኢህአዴግ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሃገር ደረጃም እየተበራከቱ እንደሄዱ አብይ በመጽሃፎቹ ደጋግሞ የገለጸው ሃቅ ነው። ግምገማ፣ የእቅድ ፎርማቶች፣ የስራ አፈጻጸም መመሪያዎች፣ የሙያና የስነምግባር ግንባታ ስልጠናዎች፣ በኮርስፖንደንስና በውጭ ሃገር ጉዞ ትምህርት በመከታተል የተገኙ ዲግሪዎች ኢህአዴግን ይሁን ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ከፍታ ሲያደርሷቸው ማየት ግን አልተቻለም። ለምን?     

አብይ የኢንሳ-ኢመደኤ (በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ) ሃላፊ በነበረበት ወቅት “የመደመርን እሳቤ በተግባር ስራ ላይ  በማዋል ያገኘውን ስኬት  በሃገር ደረጃ ማዛወር ይቻላል” የሚል ጽኑ እመነት አለው።  ይህ እምነት ሃገራዊ ችግሮቻችንን አንዳንድ ቴክኒካዊ የሆኑ መፍትሄ ብንፈልግላቸውና በሚገባ ለመተግበር ብንሞክር ይቃለላሉ የሚል ኣስተሳሰብ ውጤት ነው ( የመደመር መንገድ ገጽ 20)። 

ይህን የምለው አብይ በኢንሳ ላገኘው ስኬት ከሚሰጠው ትልቅ ትርጉም በመነሳት ነው። ግን ኢንሳ በጣም አነስተኛ በቀላሉ ሰዎች ሊቆጣጠሯቸው የሚችሏቸው ተለዋዋጮች (variables) እንቅስቃሴውን የሚገዙት ተቋም ነው።፣ የተቋሙ አለቃ በሆነው ግለሰብ ብቃትና ጽናት ሊቃለሉ የሚችሉ ችግሮች ያሉበት፣ አነስተኛ የሰራተኛ ቁጥርና እንደ አዲስ ስራ የጀመረ ተቋም ነው። አብይ ይህን ተቋም  ኢትዮጵያ ከምትባል ውስብስ ተቋም ጋር ለንጽጽር ማቅረብ የማይችል እንደሆነ በደንብ ያጤነው አይመስልም።

እንደ አብይ አገላለጽ ከኢንሳ ትልቁ ስኬት ተቋሙ ያፈራቸው በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቤት በከፍተኛ ሃላፊነት መስራት የቻሉ ግለሰቦች መኖራቸው ነው። ከነዚህ የኢንሳ ሰዎች መሃከል ስንቶች አብይ ካስቀመጣቸው ከፍተኛ የሞራልና የብቃት ማማ ላይ ዛሬ እናገናቸዋልን። ኢንሳን ካፈራቸው መሪዎች መሃል ስንቶቹ ከወያኔ ጋር ሆነው ኢትዮጵያን ለማፍረስ ተግተው ሲሰሩ አየናቸው። አብይ ይህ ሃቅ በጥሞና መፈተሽ ችሎ ቢሆን  ችግራችን የትምህርት፣ የስልጠና፣ የተቋም ግንባታ፣ የመዋቅር ማሻሻያ ብቻ ሳይሆን ከዛም ያለፈ መሰረታዊ ችግር እንደሆነ ማየት ይችል ነበር።

አብይ ለመደመር ስኬት አስፈላጊ ናቸው የሚላቸው ነጥቦች፣ የጋራ የሆኑትን መለየት፣ የጋራ ግብ ማስቀመጥ፣ ለጋራ ግብ መስራት ናቸው( መደመር ገጽ 43)። እነዚህ ሶስት መሰረታውያን በወያኔ ዘመን ከታዩ ሌሎች ተመሳሳይ እቅድ ማዘጋጃ፣ መቆጣጠሪያ፣ ማስፈጸሚያ የተለያዩ ሞዶች (Fads) መሰረታዊ ልዩነቶቻቸው እምብዛም የሚታይ አይደለም። ተግባር በጋራ የሚፈጸም እስከሆነ ድረስ ግቡም የጋራ ነው። ግብ የጋራ ቢሆንም ፈጻሚዎች ግለሰቦች ናቸው። ኢትዮጵያ ማድረግ ያልቻለችው ግለሰቦችን የጋራ ለሆነው ግብ ጥልቅ በሆነ የጋራነት ስሜት እንዲተጉ ማድረግ ነው። ኢትዮጵያ፣ ብዙሃኑ በጋራ ለጋራ ግብ መስራታቸው ቀርቶ ጥቂቶች በተናጠል ሃገርና ህዝብን እያሰቡ የማይሰሩባት ሃገር እየሆነች መሄዷ የማይካድ ሃቅ ነው። ይህ ደግሞ ቀደሞ ከነበሩት ዘመናት ይበልጥ በወያኔ ዘመን እየባሰበት የሄደ ጉዳይ ነው።  

አብይ በደንብ የታሰበባቸው ፖሊሲዎች አለመኖራቸው ሲነግረን በተሰበሩ ፖሊሲዎችም ቢሆን ለምን የተሰበረ እድገት ማምጣት እንዳልቻልን አይጠይቅም? የተማረ የሰለጠነ ሙያተኛ በሁሉም መንግስታዊና የግል ድርጅቶች ሃላፊነቶች ላይ የማስቀመጥን አስፈላጊነት ሲነግረን ለምን በከፍተኛ ደረጃ ትምህርትና ስልጠና የወሰዱ ሰዎች እንዳልተማረና ስልጠና እንዳልወሰደ ሰው እንዲያውም በባሰ ደረጃ ስልጠናቸውን እና ትምህርታቸውን የማይመጥን ስራ ሲሰሩ ይገኛሉ ለሚለው ትዝብት መልስ አይሰጠንም።

በሌሎች ሃገሮች ስሉጥ መንግስታዊ አገልግሎት ለህዝብ መስጠት የቻሉ፣ የተዋጣላቸው የስራ ማቀጃና መተግበሪያ ክህሎቶች ወደ ሃገራችን በከፍተኛ ወጪ ስራ ላይ እንዲውሉ እየተደረገ መንግስታዊ አስተዳደሩ ህዝብን ያስመረረ፣ በጉቦ በምልጃ በዘመድ አዝማድ በዘር የሚሰራ፣ እንዳውም እየባሰበት እንጂ የመሻሻል ፍንጭ የማይታይበት እየሆነ ለምን ይሄዳል ብሎ አብይ አይጠይቅም። እነዚህ ስራ ማሳለጫ ዘመናዊ  መሳሪያዎች ሳይኖራቸው የአጼ ሃይለስላሴና የደርግ ዘመን ቢሮክራሲዎች ከወያኔ ዘመን ቢሮክራሲ ለምን የተሻለ እንደነበሩ ጥያቄ አያነሳም።

የመደመር መንገድ ገጽ 65 ላይ ችግሮቻችንን “ትክክለኛ መሪዎች በመፍጠር፣ የለወጥ አስፈንጣሪዎች በመፍጠር፣ የለወጥ ባለቤት ብዙሃኑን ህዝብ በማድረግ” መፍታት እንደምንችል የቀረቡ ሃሳቦች አለው። ተራ የቢሮክራት ስነ ምግባርና ህዝብ አገልጋይነት መስፈርቶች ከንጉሱ ዘመን እና ከደርግ ዘመን እየባሰበት እየሄደ ባላበት፣ ማንኛውም ወጣት የሃገሩን ጉዳይ እንደራሱ ጉዳይ እንዳያይ በከፋ ግለሰበኛነትና ጎጠኛነት የተመረዘ ሃገር ውስጥ እየኖረ እንዴት ትክክለኛ፣ አስፈንጣሪ መሪና የለወጥ ባላቤት ነኝ የሚል ህዝብ መፍጠር እንደሚቻል አብይ አይነግረንም።

ድህነት ያጠፋል፣ የብዙሃኑን መብት ያስከብራል የተባለው አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ መንግስት የዜጎችን መብት አሰቃቂ በሆነ መንገድ ያፈነ፣ በገዛ ሃገራቸው ዜጎች በድህነትና በኑሮ ወድነት ከሚጠበሱ ከገዛ ሃገራቸው ይልቅ መከራና ሞት የበዛበትን የስደት ህይወት ሚሊዮኖች እንዲመርጡ አድርጎ ማረፉን እያየን ነው።

“የአገር ህልውና በተሻለ መሰረት ላይ ለማጽናት” በሚል የተሞከረ የመንግስትና የአስተዳደር አወቃቀር መቀመቅ ውስጥ ጨምሮናል። የቋንቋ ፌደራሊዝም በፍጥነት ወደ ዘር ፌደራሊዝም እንዴት እንደተንሸራተተ፣ ሁሉም በየዘሩ ዝግ እስር ቤት ተቆልፎ ነገ አንዱ በሌላው ዘር ለሚለኩስበት የዘር ጦርነት በተጠንቀቅ የቆመበትን አስፈሪ ሁኔታ ፈጥሯል። የሰው ልጅ በገዛ ሃገሩ፣ በገዛ የሃገሩ ሰው በዘሩ እየተለየ እንደ ከብት የሚታረድበትን አሳዝኝና አሰቃቂ አገር አስረክቦናል።  ወያኔ የዘረጋው የመንግስትና የአስተዳደር አወቃቀር የሃገርን ህልወና ማስከበር ሳይሆን የሃገር ክስመትን የሚያፋጥን ሂደት አስጀምሮ አርፎታል።

እውነት ነው ኢህአዴግ በጣም አጥብቦ ሜካኒካዊ አድርጎ ያያቸውን ጉዳዮች አብይ አስፍቶ አይቷቸዋል። ከቴክኒካዊ ከሆኑ ጉዳዮች በመሻገር ከመደመር ጋር የተያያዙ በጎና ጎጂ ስነልቦናዊ ቅላጼዎች ምን እንደሆኑ ዘርዝሮልናል። 

የቴክኒክ ብቻ ሳይሆን የባህል፣ የስነልቦና ተሃድሶም አስፈላጊ እንደሆነ ደግሞ ደጋግሞ ነግሮናል። የመደመር እቅፋቶች፣ የመደመር የተግባር ሳንካዎች ምን እንደሆኑ ገልጾልናል። የመደመር አምዶች በማለት (የመደመር መንገድ ገጽ 36) ህዝቦች ኪሳራ ሳያስተነግዱ አትራፊ የሚሆኑበትን ግንኝነት መመስረት የሚችሉባቸውን ዘዴዎች ነግሮናል። እነዚህ ሁሉ ከመደመር ጋር የተሳሰሩ በተለያዩ ቃላቶችና ከተለያዩ እይታዎች የቀረቡ ሃሳቦች እንደሃሳብ ውብ ሃሳቦች ናቸው። ሃሳቦቹ ችግር ላይ የሚወድቁት ከወረቀት ወርደው ተግባራዊ በሚያደርጋቸው ሰው እጅ ሲገቡ ነው።

ሰዎች በመመሪያ በትእዛዝ በስልጠና በተማጽእኖ ከሚፈጽሙት የጋራ ግብ በላይ ቀጣይነት  ላለው ትልቅ ክንውን እንዲነሱ የሚያደርጋቸውና የሚያጸናቸው በጋር ማንነት በጋራ እጣ ሲተሳሰሩ ነው። ኢትዮጵያ ይህ መሰረታዊ የጋራ ነገር የጠፋባት ሃገር በመሆኗ ለሃምሳ አመታት ፖለቲካውም ኢኮኖሚውም ባላበት ከመርገጥ ግን ነቅንቅ ማለት አልቻለም። እንዳውም እየባሰበት ነው።

በጥቅሉ አብይ ከግል ፍላጎታችን ሃገራችንን ብናስቀድም፣ በጥላቻ ቦታ ፍቅርን ብናነግስ፣ ከምንጠላልፍ ብንተባበር፣ በህዝብ ከመገልገል ህዝብን ብናገለግል፣ በግል ከመትጋት በጋራ በመትጋት ችግሮቻቻን እንዴት በቀላሉ መቅረፍ እንደምንችል በተማጽኖ ደረጃ የሚያቀርባቸው ነጥቦች እሱ ሲያቀርባቸው አድማጭ እንደሚያገኙ ሌሎች ሲያቀርቧቸው ግን ለምን ተደማጭነት እንዳላገኙ ተጨንቆ ያሰበ አይመስልም።

ያለፉትን መቶ አመታታ ብቻ ብንወስድ ተመሳሳይ ማሳሰቢያዎች ተማጽእኖዎች ከበርካታ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ቀርበዋል። ነገስታቱ፤ ነገስታቱን ያስወገዱ አምባገነኖች ሳይቀሩ የቀደሞ የሃገሪቱን ገናናነት እያጠቀሱ በአንድነት መትጋትን እየሰበኩ ብዙ ብለዋል። የሃገር ወዳድ ምሁራን የእድሜ ልክ ውትወታ ይሄው ነበር። 

ከመቶ አመት በፊት ነጋድራስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ “መንግስትና ህዝብ” በሚለው መጽሃፋቸው ኢትዮጵያውያን ከሌላው የአለም ህዝብ የሚለያቸውን ገናና ታሪክ፣ ጀግንነትን ከዛም አልፎ የብሩህ አይምሮ ባለቤትነትን በምሳሌነት  እየጠቀሱ እንዴት በስልጣኔ፣  በዘመናዊነትና በብልጽግና ከአለም ጭራ እንሆናለን፣ ማስተካከያዎች ካደረግን ከሰለጠኑት ሃገሮች በላይ መሆን እንደምንችል ቁጭት በተሞላው መንገድ ጽፈዋል።

በአፍሪካ ውስጥ ብዙ አነቃቂ ተናጋሪዎችና አልፎ አልፎም አንዳንድ የሃገር መሪዎች ተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረጉ ንግግሮች ያደርጋሉ። መሬት ላይ ግን ጠብ የሚል ለውጥ የለም።

የሚገርመው እንቆቅልሽ ችግሮቻችን እየተወሳሰቡና እየከፋባቸው እየሄዱ እንደሆነ አብይ በመጽሃፎቹ የሚክደው ነገር አለመሆኑ ነው። ይህን ብሎንም እሱ ተስፋ እንደማይቆርጥ እኛም ተስፋ እንዳንቆርጥ አጥብቆ ይማጸነናል። ሃገሩን የሚወደ አንባቢ በተማጽእኖው ልቡ መነካቱ አይቀርም። አብይ በመደመር የማናሸንፈው ችግር የለም ብሎ ያስባል።

አብይ ሃገሪቱ እንደ አንድ የፖለቲካዊና የኢኮኖሚ ማህበረስብ ከመቆም ይልቅ ወደ ተሰነጣጠረ ማህበረሰቦች እየተቀየረች እንደሆነ ደጋግሞ ነግሮናል። ቴክኒካዊ ከሆኑ የችሎታ እና የብቃት ችግሮች ይበልጥ ሃገሪቱን ወደፊት እንዳትራመድ ሰንጎ የያዛት ልሂቃኑ መግባባት የታሳኑባቸው ጉዳዮች የበዙ በመሆናቸው መሆኑን አብይ ተረድቶታል።

ይህ የተለያየ አመለካከት ከታሪክ አንስቶ፣ ዴሞክራሲን፣ ፌደራላዊ አወቃቀርና አስተዳደርን፣ የመንግስትን ቅርጽ፣ ሰነድቅ አላማን፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲን እና ሌሎችንም አካቶ በተቃራኒ ጫፍ የቆመ መሆኑን አብይ በግልጽ አስፍሮታል (መደመር ገጽ 119)። ዋልታ ረገጥ  አተያዮች አቋሞች ሃገሪቱን ሰንገው በመያዝ አበሳዋን እያሳይዋት እንደሆነ ጽፏል። ሁለተኛው መጽሃፍ የተሞላው እነዚህን ችግሮች ማስረዳት በሚችሉ ምሳሌዎች ነው።

አብይ ይህን ሁሉ ተገንዝቦ በመፍትሄነት የሚያቀርባቸው ሃሳቦች ከዚህ በፊት የተለያዩ መንግስታትና የፖለቲካ ድርጅቶች ከሚያቀርቧቸው የተለዩ አለመሆናቸው ድካሙን መና አስቀርቶታል የሚል እምነት አለኝ።

5.5. “መደመርን” ወደ ትልቅ ኢትዮጵያዊና አፍሪካዊ ፋይዳ ወዳለው ፍልስፍና ማሳድግ የሚቻልባቸው የዶ/ር አብይ ምልከታዎች

በኔ እምነት አብይ ለችግሮቻቸን ሁሉ መፍቻ ወደሚሆኑ መደመርን ትልቅ ሃገራዊና አህጉራዊ የፖለቲካ ፍልስፋና ማድረግ የሚችልባቸው የሃሳብ ክሮች በራሱ መጽሃፉ ውስጥ ነበሩት። እነዚህ ክሮች እየተረተረ ወደሚወስዱት ስፍራ ለመሄድ አልቻለም። ለምን አልቻለም?

የፖለቲካ መሪ እንጂ ፈላስፋ ስላልሆነ አንዱ ምክንያት ነው። በፖለቲካ ፕራግማቲክ  መሆን የግድ ስለሆነ። በፍልስፍና መልኩ የሚያቀርባቸው ሃሳቦች ከወቅቱ የፖለቲካ እውነታ ጋር የማይሄዱ ከሆነ ሽህ ጊዜ ሃቅ ቢኖራቸውም ከጥቅማቸው ጉዳታቸው ያይላል ተብሎ ታስቦ ሊሆን ይችላል።

ሌላው አብይን ስር ነቀል የእይታ ለውጥ እንዳያደረግ ምክንያት የሆነው ቀደም ብዬ የገለጽኩት፣ መሰረታዊ ለሆኑት የሃገሪቱ ችግሮች መፍትሄ የሚሻው በጠንካራ ኢህአዴጋዊ እይታ ነገሮችን እያየ ስለሚሆን ይችላል።   

አብይ፣ የትም የማያደረሱ በንድፈ ሃሳብ ይሁን በተግባር በርካታ ችግሮች ያስከተሉ የኢህአዴግ ዘመን የፖለቲካ ቲዎሪዎችን እና ፖሊሲዎች፣ ችግሩ ከቲዎሪው/ፖሊሲው ሳይሆን ከአተገባበብሩ ነው በማለት የተግባር ማሻሻያ በማቅረብ ለመሄድ ያደረገው ሙከራ የሚያሳየው ስር ነቀል የአተያይ ለውጥ (Paradigm shift) ማድረግ እንዳልቻለ ነው። በሳይንስም ሆነ በሌላው የእውቀት ዘርፍ ስር ነቀል የአተያይ ለውጥ እንቅፋት፣ ነባሩን አተያያ ችግር ፈጣሪ ነው ብሎ ከመጠራጠር አተያዩ ተግባራዊ እየሆነባቸው ያሉ ስልቶችን፣ የመተግበሪያ መሳሪያዎች፣ ሁኔታዎችን መጠርጠር ነውና።

የመጨረሻው ምክንያት ሊሆን የሚችለው ችግሮቹን በደንብ ተገንዝቦ ከችግሮቹ መውጫ መንገዶቹንም ከምሩ ፈልጎ፣ በመጽሃፉ ካስቀመጠው የችግር መውጫ መፍትሄ ሌላ አማራጭ አልታይህ ብሎት ሊሆን ይችላል።

ቀጥሎ፣ በኔ አስተያየት አብይ በሁለቱ መደመሮች መጽሃፎቹ ውስጥ እያነሳ የተዋቸው ነገር ግን ለስር ነቀል የአመለካከት ለውጥ መነሻ ሊሆኑ ይችሉ የነበሩ ጉዳዮችን ወደ ማሳየት ነው።  

“መደመር” ገጽ 34 ላይ

“ከኢትዮጵያውያን መሰረታዊ ስሪት የሚነሳ ችግሮቻችን ሊፈታ የሚችል፣ እኛው እያቃናነውና እያሟላነው የምንሄደው፣ ከአለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተገናዘበ፣ ሁላችንንም ሊያግባባና ሊያስተባብር የሚችል  አንዳች ሉአላዊና ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ያስፈለገናል” ይላል። 

አብይ ይህን ብሎም ሃሳቡን አይገፋበትም። እንዲያውም ይህን ንኡስ ምእራፍ የሚዘጋው ኢትዮጵያዊ የሆነውን ፍልስፍና የምናገኘው “በአለም ላይ የሚቀነቀኑ ፍልስፍናዎች በመዳደስ” ነው በሚል በሌሎች ቦታዎች ያስጠነቀንን የውጭ ፍልስፍና ቃራሚነት የሚያመጣውን አደጋ በሚያቃልል መልኩ ነው።

በሌሎች የመጽሃፉ ክፍሎች ለምሳሌ “መደመር” ከገጽ 103 እስከ ገጽ 125 በሚደርሱት ገጾች፣ እንዲሁም በ “የመደመር መንገድ ገጽ 43 ላይ  አብይ ምን አይነት ዴሞክራሲ ያስፈልገናል? በሲቪክ ብሄረተኛነት እና በማህበረሰባዊ ብሄረተኛነት መካከል ስላለው መሳሳብ፣ የሀገር መንግስት ቅቡለነት የማረጋገጥ ፈተና በሚሉ ርእሶች ስር መሰረታዊ ወደ ሆነው የሀገሪቱ ችግሮች የሚጠጋበት እድል አግኝቶ ነበር።

እነዚህን ችግሮች የሚመለከትበት አይን ከኢህአዴግ በወረሰው በተለመዱት የፖለቲካና የታሪክ መነጽሮች አይን ስለሆነ ያው ሌሎች ደግመው  ደጋገመው ሲያቀርቧቸው ከነበሩት መፍትሄዎች የተለዬ መፍትሄ ማቅረብ እንዳይችል አድርጎታል። “ኢህአዴግ ለሃገራዊ አንድነት” ትኩረት ባላማድረጉ ችግር ላይ እንደወደቅን እንጂ ኢህአዴግ ሃገራዊ አንድነት እንዳይኖር በማወቅም ሆነ ባለማውቅ ሆን ብሎ ይሰራ የነበረ ድርጅት መሆኑ አብይ አይታየውም። የብሄር ማንነት ሃገራዊ ማንነት በሚዛን መሆን ይኖርባቸዋል የሚል አስተሳሰብ እንጂ የሃገራዊ አንድነት ከሁሉም ነገራችን በላይ ወሳኝነት ያለው አለመሆኑ ያስከተለውን መዘዝ ማየት የቻለ አይመስልም።

በአንድ ሃገር ሁለት አይነት በእኩልነት የሚታዩ ብሄረተኛነቶች ሊኖሩ አይችሉም። ይህ የስሜት ተፈጥሯዊ ባህርይ ነው። ብሄረተኛነት ደግሞ ስሜት ነው። አንዱ ስሜት የግድ ከሌላው በላይ መሆኑ የግድ ነው። እያየነው ነው።  በኢትዮጵያ ውስጥ የምናየው ችግር ከዚህ የመነጨ ነው። የማይታረቁ ነገሮች እንደሚታረቁ አድርጎ በማቅረብ ነው ሃገር ችግር ውስጥ የወደቀችው። ችግሩ የሚፈታው በጥገና ሳይሆን ስር ነቀል የአመለካከት ለውጥ በማድረግ ነው።

ኩሩ ትግሬ ሆኖ ኩሩ ኢትዮጵያዊ የማይኮንበት ምክንያት የለም የሚለው የመለስ ዜናዊ አባባል በራሱ በመለስ ዜናዊ ጭንቃላት ውስጥ እንጂ በእውን አለሙ የማይገኝ እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልግ ነበር። ዛሬ የመረጃ እጥረት ያለብን አይመስለኝም። ብሄሮች ወይም ብሄረሰቦች ኢትዮጵያን በመሰለ ሃገር ውስጥ በጋራና በሰላም ለመኖር ሁሉም ብሄሮች በመግባባት የተቀበሏቸው አይነኬ የሃገር አንድነት እሴቶች የግድ መኖር እንዳለባቸው በአመክኖዋዊ ትንተና ማሳየት ይቻላል።  እንደ ነጋዴ ሁለቱን የብሄረተኛነቶች አይነት ሚዛን ላይ በማስቀመጥ እያቻቻሉ የሚፈታ ችግር እንዳልሆነ መታወቅ ነበረበት። እነዚህን በመሰሉ ችግሮች ላይ አብይ ብዙ ትኩረት ቢያደርግም  የአመለካካት ሽግግር  በማድረግ ወደ እውነተኛው መፍትሄ መጠጋት አልቻለም።

አብይ በሃገራችን ውስጥ የትብብር የአንድነት ውጤት የሆኑ ብዙ ክንውኖችን በምሳሌነት ያነሳል። የጋራ ሊሆኑ የሚችሉ እሴቶቻችንን በስፋት ያቀርባል። “ወደ ኋላ ዞር ብላችሁ እዩት ስንተባባር ምን መስራት እንደምንችል። ያለፈው በትብብር ላይ የተገኘ የድል ታሪካችን የወደፊቱ ታላቅነታችን የመሰረት ድንጋይ መሆን ይችላል” እያለ ይወተውተናል።  “ጣሊያንን አሸንፋለሁ ብሎ በተስፋ ከቤቱ የወጣ ያ የአድዋ የድል ባለቤት እንዴት ለጥቃቅን ነገሮች ተሸንፎ እጀ ሰጥቶ ምኞትና ህልሙን በመቀስ ቆረጠ (ገጽ 360 የመደመር መንገድ)።” ይለናል።

አብይ ደግሞ ደጋግሞ ኢትዮጵያውያን እርስ በርሳችን እንዳንለያይ ሆነነ የታጋመደን… እጣችን … በአብሮነታችን ድርና ማግ ውብ ሆኖ የተሸመነ ጥበብ” መሆኑ ይነግረናል (የመደመር መንገድ ገጽ 352)። ደግሞ ደጋግሞ በኩራት የሚያነሳቸው የኢትዮጵያ የታሪክ ቅርሶች፣ በጋራ ጠላትን በመመከት የተገኙ ድሎች በመደመር ምን ማከናወን እንደሚቻል ከመጠቆም አልፈው ራሱ የመደመር ሃሳብ የሚፈተልባቸው ድርና ማግ እንዴት መሆን እንደሚችሉ ማሳየት አልቻለም።  

ድርና ማግ መሆን የሚችሉት እነዚህ የታሪክ ቅርሶች፣ ታሪካዊ ድሎች በሁሉም የሃገሪቱ ዜጎች መንፈስ፣ ነፍስ፣ ስነልቦና ውስጥ በተመሳሳይ የኔነት ስሜት ሲኖሩ ብቻ ነው። ይህ እንዳይሆን የልሂቁን ዋልታ ረገጥ ሰነጣጣቂ አመለካከት ስህተተኛነት ቀጥሎም ጎጂነት መጀመሪያ እራሱ ልሂቁ አምኖ እንዲቀበለው ማድረግ ያስፈልጋል።  አብይ ይህን አላጣውም። ይህ ችግር ይፈታል ብሎ የሚያስበው አሁንም በነባሩ የችግር መፍቻ ሞዴል ነው።

የልሂቁ ችግር ካለፈና ከቅርብ ጊዜ ታሪካችን የሚመዘዝ በደል፣ ቂም፣ በቀል፣ ጥላቻ ነው ብሎ በማማኑ የዚህ ችግር መፍቻ ይቅርታና ፍቅር ነው ብሎ ያምናል። ለዚህ ነው ዶ/ር አብይ በይቅርታ ብሄራዊ መግባባት የተደረሰባቸውን የሌሎች ሃገሮች ተመክሮዎች እንድናጤን የተጋው።

በ “የመደመር መንገድ” መጽሃፉ ገጽ 64 እና ገጽ 195 “ቁስላቸውን ያደረቁ ሀገራት” ምእራፍ 6 ሙሉ በሙሉ፣ እንዲሁም “የኢትዮጵያን እርቅ ፍለጋ”  የሚለው ምእራፍ 7 በከፊል የተመደበው እንዴት እኛም በይቅርታና በፍቅር በመደመር ከገባነበት ሃገራዊ ችግር መውጣት እንደምንችል ለማሳየት ነው።

ዶ/ር አብይ በእርቅና መግባባት ሞዴለነት ያቀረባቸው ሃገሮች (ካናዳ ሩዋንዳና ደቡብ አፍሪካ) ከኛ ሃገር ጋር የሚመሳስል ችግራቸው በጣም ጥቂት ነው። እሱም ይህን አልካደም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ ለተፈጠሩ ቁርሾዎች ማስወገጃነት ያገለግሉ ካልሆነ በስተቀር ከታሪክ ጋር ተያይዞ ለሚነሳ መካሰስ መፍትሄ መስጠት የሚችሉ አይደሉም። 

ትልቁ ችግራችን የደርግ ወይም የወያኔ ዘመን በደል ያመጣው ቁርሾ ሳይሆን በመቶዎች አመታት ወደኋላ እየተመለስን የምናቀርባቸው የመበዳደል፣ የቂምና የበቀል ትርክቶች ናቸው። የደርግ እና የወያኔ ዘመን ቁርሾዎችም በእርቅ መንገድ ይፍቱ የሚለውን ሃሳብ እየተቃወምኩ አይደለም። ለነዚህ ዘመናት ግፍና በደል ወግ ባለው የእርቅ ሂደት ውስጥ ሃገሪቱ ብታልፍ መልካም ነው።

በተለያዩ ልሂቃን መሃል ያሉ ችግሮች በይቅርታ፣ ወይም የተለያዩ ሃገራት ተመሳሳይ በሆነ የሃገር ግንባታ ማለፋቸውና  እኛ የተለየን አለመሆናችን በማመላከት የሚቃለሉ አይደሉም። አብይ ግን በሁለቱ መንገዶች ከመሄድ ውጭ ሌላ አማራጭ አይታየውም።

ሁሉም የተበደለበትን የክስ ፋይል ማውጣት በሚችልበት ሃገር፣ ይቅርታ ሰጪ ይቅርታ ተቀባይ ሊኖር አይችልም። ሁላችንም ይቅር እንባባል ከተባለም ለአንድ ምሽት ለይቅርታ በተሰባሰበው፣ ለዚህም ሲባል የተዘጋጀው የሞቀ ድግስ በስሜት ለወሰወሰው ተሰብሳቢ ይሰራ እንደሆነ እንጂ ችግራችንን ከመሰረቱ የሚፈታው አይሆንም። 

ምክንያቱም፣ ልሂቃኑ የዋልታ ረገጥ ትርክታቸውን ማስቀጠል የሚፈልጉት ይቅርታ እንዲጠየቁ ሳይሆን ይህ ዋልታ ረገጥ ትርክትና የሚቀሰቅሰው የቂምና የበቀል ስሜት ትርፍ ያስገኝልናል ብለው በማሰባቸው ነው። ትርፉ ከጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች የሰሜትና የቁስ እርካታ የማይሻገር ነው።  ይህ ደግሞ የደሃ ሃገር እርግማን ነው።

የችግሩ መፍትሄ ሁሉም ቂምና በቀሉን በማራገብ የሚያደርገው መካረር፣ መከፋፈል ትርፍ የማያስገኝ መሆኑን በማያሻማ ትነታኔና መረጃ ለአብዛኛው ልሂቅና ህዝብ ከማሳየት ውጭ ሊሆን አይችልም። ይህ አካሄድ በጣም ከባድ ነው። ተከታታይ ስራ፣ ብዙ ድካምና ረጅም ጊዜ የሚፈጅ ነው። ግን ሌላ መንገድ የለም። 

የዛሬ ሶስት አመት ይህን ተገንዝበን ቢሆን ኖሮ ከሌሎች አብይ ከሰራቸው ስራዎች ጎን ለጎን ይህን ስራ ማስጀመር አያቅተንም ነበር። ከዚህ ቀደም የተሄደበት መንገድ ባለመሆኑ ዶ/ር አብይ በሃሳብ ደረጃ ጀመር ቢያደረግውም ሊገፋበት የሞከረው አልሆነም። 

ሌላው አብይ የዋልታ ረገጥ  እይታ ያመጣቸውን ችግሮች መፍቻ በሁለቱም መደመሮች ደጋግሞ ብዙ ምሳሌዎችን በመጥቀስ ለማሳየት የሞከረው የሌሎችን ሃገራት ብሄራዊና  ሃገራዊ መንግስት ግንባታ ከኛ ሃገር ጋር ያለውን ተመሳሳይነት ዋልታ ረገጦቹ እንዲያዩት በማደረግ ነው።

ይህም ሙከራ የትም  የሚያደርሰው አይደለም። ምክንያቱም  ሁሉም ልሂቅ ጥላቻውን ቂምና በቀሉን በልቡ ይዞ የሚዞረው ይህን የአለም ሃገረ መንግስታት የአመሰራርት ታሪክ አጥቶት አይደለም። በእሳት በብረት በመገበርና በማስገበር ሂደት ሃገሮች እንደተገነቡ የማያውቅ ልሂቅ ዛሬ በሃገራችን አይገኝም። 

ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ዘመናትን ከተሻገሩ የታሪክ ኩነቶች ጋር የተያያዙ ቁርሾዎችን የሚያረግብ እርቅ አይደለም። ወይም ሌሎች ሃገሮች እንዴት እንደተመሰረቱ የሚያሳይ ለልሂቃኑ የሚሰጥ ሴሚናር አይደለም። ከሌሎች ነገሮች የጸዳ በጋራ በተሰሩ የታሪክ ክንዋኔዎች ዙሪያ መፈጠር የሚገባው ብሄራዊ መግባባት ላይ ሃገር መገንባት ካልቻልን መጨረሻችን አሰቃቂ እንደሚሆን ማሳየት ብቻ ነው።

አብይ ለብሄራዊ መግባባት መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ሃሳቦችንም ከማሳየት አልቦዘነም። የመደመር መንገድ ገጽ 30 በአፍሪካና በአሜሪካ የሚገኝ ጥቁር ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚጋሩት የኢትዮጵያዊነት ትርጓሜ ምን እንደሆነ ይነግረናል። “ የነጻነትና የአሸናፊነት በሌሎች አልገዛም” የሚል “አስተሳሰብ ድምር ነው”ይለናል። ሆኖም ግን ይህ ግንዛቤ በራሱ በኢትዮጵያውያን አይን እንድ ወጥ በሆነ መንገድ የማያታይ መሆኑ ችግር እንደፈጠረ ይነግረናል።

አብይ “መደመር” ገጽ 119 ላይ የብሄራዊ መግባባት የሚጠይቁትን ጉዳዮች ዘርዘር አድረጎ ቢያነሳም፣ የሚያጠቃልለው “ብሄራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ አስቀድመን ያለፉ ቁስሎቻችንን ማከምና መዳን ይገባናል፣ እርቀ ሰላም ማውረድ ያሻናል” በማለት ነው። ለብሄራዊ መግባባት አስፈላጊ ነው የሚለው እርቀ ሰላም በመቶዎች ለሚቆጠሩ አመታታ ወደኋላ እየተመለስን የሚደረግ እርቀ ሰላም በኢትዮጵያ ማህቀፍ ቦታ ሊኖረው የማይችል መሆኑን ግን አብይ ማየት የቻለ አይመስለኝም።  

ከዛም አልፎ ይህን ችግር እያባባሰው የመጣውን የወያኔ ዘመን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የባህል አተያያና ይህን ተከትሎ የመጣው በተግባር የተተረጎመ መዋቅርዊና ተቋማዊ ጉልበት የተሰጠው በማህበረሰባዊና ግለሰባዊ አመለካከቶች ላይ ያደረሰውን ትልቅ ጉዳት በተመለከተ አብይ  የሚሰጠን ምልከታና መፍትሄው ላይ ውስኑነት አለው።        

ዶ/ር አብይ የኢትዮጵያን ችግር በሚገባ እንድረዳ  የሚያደርጉ ጠለቅ አድርገን እንድናስብ የሚያግዙ ጉዳዮች አንስቷል።

በአንድ ወቅት ከኢትዮጵያ ጋር በተመሳሳይነት የእደገት ደረጃ ላይ የነበሩ እነጃፓን፣ ኮሪያና ቻይና የመሳሰሉ ሃገሮች እንዴት በአጭር ጊዜ ሃገራቸውን ዘመናዊ ማድረግና ማበልጸግ እንደቻሉ እኛ ግን ከዘመናዊ ስልጣኔና ብልጽግና ተኳርፈን እንደቀረን በቁጭት ይነግረናል።

በ(የመደመር መንገድ” ገጽ 49-51 “ የእስራኤል ህዝቦች ራሳቸውን አጠንክረው የደረጀ ሃገር ገንብተው መኖር ጀምረዋል። ለሃገር ግንባታቸው መሳካት አስተዋጽኦ ካባረከቱት ጉዳዮች መካከል፣ እንደ ህዝብ አንድ የሚያደርጓቸው እሴቶች፣ ወጎች፣ ልማዶች አለመተዋቸው፣ ተመሳሳይ ስነ ልቦና እንዲኖራቸው አስተዋጽኦ አድርጓል” ይለናል።

አብይ ስእስራኤል ሆነ ስለ እስያ ሃገሮች በፍጥነት የመልማት ምክንያቶች የሆኑትን መሰረታዊ ጉዳዮች እየጠቀሰም እነዚህን ምክንያቶች በንጽጽር ወደ እኛ ሃገር አያመጣቸውም። እነዚህ ሃገሮች ለምን ተሳካላቸው እኛ ለምን አልተሳካልንም የሚለውን ጥያቄ አብይ የሚመልሰው የእነዚህ ሃገር ህዝቦች መተባበር፣ በጋራ ማለም በጋራ መስራት በመቻላቸው ነው የሚል ነው። 

“ለምን እኛ በጋራ ማለም፣ በጋራ መስራት አልቻልንም ለሚለው ጥያቄ ዞሮ ዞሮ፣ ሃገር በቀል አመለካከቶች መጥፋት፣ ከትክክለኛ ፖሊስ እጦት፣ ፖሊሲዎችን ወደ እቅድ በመተርጎም እቅድ የማስፈጸም እውቅትና ክህሎት እጥረት፣ ከባህል ከስነልቦና፣ ከፍልስፍና የመጡ ተባብሮ ተደምሮ የመስራት የአመለካከት ችግሮች የሚሉ ምላሾች ላይ የተቸከለ ምላሽ ነው የምናገኘው። 

አብይ ቴክኒካል ከሆነው መፍትሄ ወጣ ሲል የሚያቀረበው መፍትሄ “በይቅርታ ለመሻገር በፍቅር ለመደመር” እስከጣርን ድረስ ችግራችን ለማቃለል እንችላለን የሚል ነው። ይህ መፍትሄ በስፋትና በተደጋጋሚ የሚቀርብ መፍትሄ ነው። እዚህም ላይ ዶ/ር አብይ የመፍትሄ ምልከታዎቹ ከጠንካራ የእምነት ሰው ከመሆኑ ጋርም የተሳሰሩ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬ ጭሮብኛል። እምነት፣ “በይቅርታ ለመሻገር በፍቅር ለመደመር” ለጆሮ በሚጥም መንፈስን በሚያረካ ውብ ስንኝ አማካይነት የሚደረግ ጥረት ሁሌም ያሸንፋል የሚል ጽናት የሚሰጥ ነው።

ፖለቲካ በይቅርታ ለመሻገር በፍቅር ለመደመር የማይፈልጉ አካላትን በመቀነስ፣ ተደምሮ ለመሄድ የሚፈልጉትን ደምሮ፣ የድምር ውጤት ማብዛት እንደሚቻል በስኬት የተጠናቀቁ ምሳሌዎች የበዙበት የህይወት ዘርፍ ነው። የወያኔ እና የብልጽግና ፓርቲ ግንኙነት በመቀነስ መደምርን ማግዘፍ እንደሚቻል ጥሩ ምሳሌ ነው። ወያኔ ያለበት ብልጽግና ፓርቲ ወይስ የሌለበት ብልጽግና የድምር ውጤቱ ያማረ? ለሚለው ጥያቄ የብልጽግና አባላት ምን መልስ እንደሚሰጡ ግልጽ ነው።

በሌሎችም የህይወት ዘርፎች አሉታዊ አስተዋጽኦ ያላቸውን አካላት በመቀነስ ለሚቀሩት አካላት ድምር ሲነርጂ መፍጠር እንደሚቻል ይታወቃል። የአብይ የመደበር እሳቤ በመቀነስ መደመር የሚል እይታ የሌለው መሆኑ በአንድ አንድ አጋጣሚዎች ከሚያመጣው በጎ የበለጠ ዋጋ አስከፋይ ሊሆን ይችላል። እስካሁንስ ሳያስከፍለን ቀርቷል ወይ የሚል ጥያቄ ያስነሳል።   

በአጠቃላይ አብይ በቴክኒካል፣ ወይም በተማጽእኖ ወይም እምነታዊ በሆኑ መፍትሄዎች ይፈታሉ ብሎ ካሰባቸው ችግሮች ይልቅ ከፍልስፍና ጋር የተያያዙ ናቸው ያላቸው ችግሮች ትልቁን ቦታ ሊሰጣቸው ይገባ ነበር። መደመር፣ ቴክኒካዊ፣ ሃይማኖታዊና ተማጽኗዊ ከሆኑ ገጽታዎቹ ፍልስፍናዊ ወደሆነ ገጽታ ማጋደል ባለመቻሉ የችግሮቻችንን  መሰረታዊ ምክንያቶች እና ቁልፍ መፍትሄዎቹን ማወቅ እንዳንችል ሆነናል።

በተለያዩ የመደመሮቹ ገጾች በተለያዩ አጋጣሚዎች አብይ አፍሪካን እና እንደ ናይጀሪያ አይነቶቹን ሃገሮች ያነሳል። ናይጀሪያ በተፈጥሮ ሃብት የታደለች፣ አንቱ በተባሉ የአለም ዩኒቨርስቲዎች በመቶ ሺዎች ልጆቿን ያስተማረች፣ አገር ናት። ናይጀሪያ የቅኝ ገዥዎች ውጤት በመሆኗ እንደኛ ሃገር በመቶዎች አመታታ ወደ ኋላ የሚመለሱ የብሄር ብሄረሰቦች መካሰስ ያለባት ሃገር አይደለችም። ቅኝ ገዥዎች ከሄዱ በኋላ በተለያዩ ብሄሮች መሃከል ግጭት የተነሳባት ሃገር ብትሆንም ናይጀሪያን ከነሃብቷና ከተማረ የሰው ሃይሏ ጋር ትንንሾቹን የእስያ ነብሮች እንኳን የደረሱበት የልማትና የእደገት ደረጃ ላይ አልደረሰችም። የምትደርስም አትመስልም።  አብይ ግን ናይጀሪያንም ቢሆን ያለችበትን ሁኔታ በበጎ አይን ነው የሚያየው። ለምን? ምንድን ነው በአፍሪካውያንና በእስያውያን ወይም በምእራባውያን መሃከል ያለው ልዩነት። በተፈጥሮ ሃብት፣ በሰው ሃይል፣ በሰው ምንነት ወይስ ሌላ በምን? ለምን የናይጀሪያን ዝቅተኛ የእድገት ደረጃ በቁጭት አንመለከትም?

ከላይ በጠቀስኳቸው ምክንያቶች የተነሳ፣ ለትልቁ እና ሁሉን ገዠ ለሆነው የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ስብራት ፈውስ የሚሆን መድሃኒት ከአብይ ብእር አልተገኘም። “መደመር”ን አብይ እንደተመኘው የፍልስፍና ጽንሰ ሃሳብ አድርጎ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ የአመለካከት መሰባሰቢያ ማድረግ የሚችልበትን እድልና አጋጣሚ አባክኖታል። 

የመደመርን ፍልስፍና አብይ በ “የመደመር መንገድ” መጻሃፉ ደግሞ ደጋግሞ እንደሚያነሳው ሽንቁር እንስራ ሆኖ ነው ያገኘሁት። አብይ በመደመር መጽሃፎቹ ያላነሳቸው፣ ያልፈተሻቸው በውብ ብእሩ ያልነካቸው ችግሮቻችን እና መፍትሄዎቻቸው አሉ ብዬ አላምንም። ሆኖም ግን ሁሉንም ያፈሰሳቸው በሚገባ ሽንቁሩ ባልተደፈነ የመደመር እንስራ ውስጥ በመሆኑ እንስራው ሞልቶ ጥማችንን ማርካት አልቻልንም።

መጽሃፍ የሚዳስሱ ሰዎች የአንድን መጽሃፍ ጠንካራና ደካማ ጎን አቅርበው ዳሰሳቸውን መቋጨት መብታቸው ነው። ከፈለጉም ግን ጉድለት ያሏቸውን ለይተው ጉድለት ማስተካከያ ብለው የሚያስቧቸውን ሃሳቦች በዳሰሳው ማካተት መብታቸው ነው። የኔ ዳሰሳ ዝም ብሎ መጽሃፍ ለመዳሰስ ብቻ አይደለም። 

በተለይ ለአብይ መጽሃፎች የሰጠሁት ክብደት ዳሰሳ አቅርቤ ብቻ ዞር እንድል አይፈቅድልኝም። የዳሰሳውን  ዳራ በገለጻኩባቸው ቀዳሚ ገጾች ላይ እንዳመላከትኩት  የ”መደመርን” ድክመት ማሳየት ብቻ ሳይሆን ይህን ድክመት እንዴት ማስወገድ ይቻል  እንደነበር በማመላክተም ጭምር መቋጨት ነው። 

ዶ/ር አብይ በተደጋጋሚ “መደመርን” ወደ እውነተኛ ፍልስፍና መውሰድ የሚችላባቸውን እድሎች በመጽሃፉ አግኝቶ አባክኗቸዋል ብያለሁ። ቀጥሎ የምሸጋገረው ባክነዋል ካልኳቸው እድሎች ወደ ዋናው የመደምር ፍልስፍና እንዴት መሸጋጋር እንችል እንደነበር ወደ ማሳየቱ ነው።

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top