“መንግስት ተጠያቂነትን የሚያሰፍን የእርምት እርምጃ በአስቸኳይ እንዲወስድ እንጠይቃለን”
~ ከኢዜማ የተሰጠ መግለጫ
በሀገራችን በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለውን ማንነት ላይ ያተኮረ ግድያን በተመለከተ ከኢዜማ የተሰጠ መግለጫ
ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ዜጎች በማንነታቸው እየተለዩ በአሰቃቂ ሁኔታ በተደጋጋሚ ጥቃት ሲደርስባቸው ቆይቷል። በአጣዬና በሌሎችም አካባቢዎች ተመሳሳይ ድርጊቶች የተፈፀሙ ሲሆን ሁሉም ዜጎች በሕይወት የመጠበቅ እና በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች በነፃነት የመንቀሳቀስ፣ ኑሮ የመመስረት እና የመሥራት ሰብዓዊ መብት እንዳላቸው በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የተደነገገ መብት መሆኑ ይታወቃል።
ነገር ግን ይህ መብት ከምንም ነገር በላይ ሊከበርላቸው የሚገቡ ዜጎች በተደጋጋሚ በተከሰቱት ማንነት ተኮር ጥቃቶች ውድ ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ አካላቸው ሲጎል እና ከቤት ንብረታቸው ሲፈናቀሉ ቆይተዋል።
ንፁሃን ላይ የሚደርሰው ማንነት ተኮር ጥቃት መብታቸውን የሚጥስ ብቻ ሳይሆን አሰቃቂ እና ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ የሚፈፀም መሆኑ እጅግ ልብ የሚሰብር እና በሰብዓዊ ፍጡር የሚፈፀም መሆኑን ለማመን የሚያስቸግር አድርጎታል።
በያዝነው ሳምንት መግቢያም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ገንቤል ወረዳ በቦኔ ቀበሌ በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎች ላይ ማንነት ላይ መሰረት ያደረገ ጥቃት ተፈፅሞ ብዙ ንፁሃን ዜጎች መተኪያ የሌለው ሕይወታቸውን እንዲያጡ እና ለትውልዶች ከኖሩበት ቀያቸው እንዲፈናቀሉ ሆነዋል።
ከዚህ ከጥቃት ከተረፉ ዜጎች ቃል ለመረዳት እንደተቻለው ጥቃቱ ከመፈፀሙ በፊት አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ አካባቢው እንዲያስተዳድሩ ኃላፊነት ከተሰጣቸው የቀበሌና ወረዳ አስተዳዳሪዎች ማስፈራሪያ ደርሷቸው ነበር። ይህም፣ ጥቃቱ ሆን ተብሎ እና ታቅዶበት ለመፈፀሙ እና እና የአካባቢው ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለባቸው ሰዎች ተሳትፎ አንዳለበት ማሳያ ነው።
እስከአሁን በዜጎች ላይ በተደጋጋሚ የተፈፀሙ ለከት ያጡ ኢሰብዓዊ የወንጀል ድርጊቶች የተፈፀሙት በታወቁ ውሱን በሆኑ ቦታወች መሆናቸው በክልሉም ሆነ በፌደራል መንግሥት በኩል ችግሩን የሚመጥን ትኩረት ላለማግኘቱ አመላካች ነው።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በንፁሃን ዜጎቻችን ላይ በደረሰው ግድያ እና መፈናቀል የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ በጥቃቱ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን ላጡ እና ለመላው ኢትዮጵያዊያን ልባዊ መፅናናትን ይመኛል።
በተደጋጋሚ የተከሰቱት ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እንደሀገር እንዳንረጋጋ እና ዜጎች ከፍርሃት ተላቀው የዕለት ተለት ሕይወታቸውን እንዳይመሩ እንቅፋት ከመሆኑም በተጨማሪ ከውጭ ለሚመጣብን ሉዓላዊነታችን እና የሀገር ደኅንነታችን ላይ ላነጣጠረ አደጋ ተጋላጭ አድርጎናል።
እነዚህ ጥቃቶች የሚፈጽሙት በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉም ሆነ ከመንግሥት በተፃራሪ የቆሙ አካላት በድርጊቱ ማሳካት የሚፈልጉት ዓላማ በሀገራችን ውስጥ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዳይፈጠር እንቅፋት መሆን ሲሆን ከዚህ ከፍ ሲልም የማያባራ የእርስ በርስ ብጥብጥ በማስነሳት ሀገራችን ለማፍረስ ነው።
ይህን ዓላማቸውን ለማሳካት በሀገራችን ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ማኅበረሰቦች መካከል የእርስ በርስ ግጭት ሊያስነሱ የሚችሉ ጥቃቶችን ሆን ተብሎ በተቀነባበረ መንገድ እየፈፀሙ ይገኛሉ። ይህን ዕኩይ የፖለቲካ ዓላማቸውን ለማሳካት እስከመጨረሻው እስኪሸነፉ ድረስ ምንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ እንደማይሉ ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን ግልፅ ሆኗል።
ይህንን እና ሀገራችን ያለችበትህ አጠቃላይ ሁኔታ ከግምት በመክተት የሚከተሉት እርምጃዎች እንዲወሰዱ አጥብቀን እንጠይቃለን።
- የዜጎችን በሕይወት የመኖር መብት፣ ሰላም እና ደኅንነት መጠበቅ የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም በዜጎች ላይ ጥቃት እየተፈፀመባቸው ባሉ አካባቢዎች ያለው የመንግሥት መዋቅር በጥልቅ ተፈትሾ በየደረጃው የሚገኙ ኃላፊዎች ላይ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን የእርምት እርምጃ መንግሥት በአስቸኳይ እንዲወስድ እንጠይቃለን።
- ጥቃት ለደረሰባቸው ዜጎች መንግሥት ተገቢውን ክትትል፣ ካሳ እና መልሶ ማቋቋሚያ እገዛ በአስቸኳይ እንዲደረግላቸው፤ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ውስጥ አስፈላጊውን ርብርብ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን።
- ጥቃት በተደጋጋሚ የደረሰባቸውን እና ሊደርስባቸው የሚችል አካባቢዎችን በመለየት በአስቸኳይ በፌደራል መንግሥት የፀጥታ አካላት ቁጥጥር ሥር በማድረግ እና በአካባቢው ያሉ ጥቃት ፈፃሚዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድ እና በእነዚህ አካባቢዎች አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የደኅንነት ዕቅድ እንዲቀረፅ እና በአስቸኳይ ተግባራዊ እንዲደረግ እንጠይቃለን።
- ስጋት ያለባቸው አካባቢዎች የፌደራል መንግሥት ከሚሠራዉ የሰላም እና የደኅንነት ማስጠበቅ ሥራ በተጨማሪ በአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመተባበር የማኅበረሰብ አቀፍ ሰላም እና ደኅንነት ሥራ የሚሠራ ኃይል የማደራጀት፣ የማሠልጠን እና የማስታጠቅ ሥራ እንዲሠራ እንጠይቃለን።
- የፌደራል መንግሥት የፀጥታ መዋቅር በኃይል እጥረት ምክንያት ማሥፈር በማይችልባቸው ቦታዎች ላይ ማኅበረሰቡ እራሱን መከላከል የሚያስችለው አደረጃጀት እና ትጥቅ እንዲኖረው እንዲደረግ፤
የተፈጠሩ ችግሮችን እና አጠቃላይ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት እና ደኅንነት በተመለከተ ኢዜማ በቀጣይ በየደረጃው ካሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተመሳሳይ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በዘላቂነት ማስቆም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት የሚያደርግ ይሆናል።
ኢዜማ በእነዚህ ውይይቶች ችግሩን በመሠረታዊነት ለመፍታት እንዲቻል ዝርዝር ማብራሪያ የሚጠይቅ ሲሆን በየጊዜው በተፈፀሙት ጥቃቶች ውስጥ አስተዋፅዖ ያደረጉ አካላት ተጠያቂ የሚሆኑበት ውሳኔ እንዲሰጥም ክትትል ያደርጋል። ለሰላም እና የዜጎች ደኅንነት መረጋገጥ ማድረግ የሚችለውንም ኃላፊነትም ይወጣል፡፡
የችግሩን ጥልቀት እና ሊኬድባቸው የሚገባ መንገዶችን የሚያብራራ እና ችግሩን የሚመጥን ግብረመልስ እንዲሰጥ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት፣ ለፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት፣ ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን አዘጋጅተን የምንልክ መሆኑን እና አፈፃፀሙን የምንከታተል ይሆናል።
በሀገራችን ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የሚቆመው ሁሉም ዜጎች በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች በዜግነታቸው በዕኩልነት የታዩበት የፖለቲካ ሥርዓት ሲመሠረት ብቻ እንደሆነ እና ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ሀገራችን ያለችበትን አስቸጋሪ ሁኔታ በመረዳት የምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች በሙሉ የበለጠ ችግሩን የሚያባብስ እና ወደ እርስ በርስ ግጭት የሚከተን እንዳልሆነ እንድናረጋግጥ እና ማንነትን መሠረት ያደረገ ጥቃት የሚፈጽሙ ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳንሆን የአደራ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ
#ኢዜማ
መጋቢት 24 ቀን 2013 ዓ.ም