Connect with us

በከባድ የውንብድና ወንጀል የተጠረጠሩት የፖሊስ አባላት ላይ ብይን ተሰጠ

በሰዎች የመነገድ ወንጀል የፈጸመው ኪዳኔ ዘካሪያስ በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ተወሰነ
ፌ/ጠ/ዐ/ህግ

ዜና

በከባድ የውንብድና ወንጀል የተጠረጠሩት የፖሊስ አባላት ላይ ብይን ተሰጠ

በከባድ የውንብድና ወንጀል የተጠረጠሩት የፖሊስ አባላት ላይ ብይን ተሰጠ

የፌዴራል ፖሊስን የደንብ  ልብስ ለብሰውና የፖሊስ መኪና ይዘው የውንብድና ወንጀል በመፈጸማቸው በዐቃቤ ህግ ክስ ቀርቦባቸው የነበሩት ግለሰቦች እንዲከላከሉ ፍ/ቤት ብይን ተሰጠ፡፡

1ኛ.ሻምበል ሁሴን መሀመድ፣ 2ኛ. ሃይሎም ገብሬ አስረስ፣ 3ኛ. ተመስገን ተወልደመድህን እና 4ኛ. ሀይሉ ገብረሩፋኤል የተባሉት ተከሳሾች በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀጽ 32 (1) ሀ እና 671 (1) ለ ላይ የተደነገገውን ድንጋጌ በመተላለፍ ካልተያዙ ግብረአበሮቻቸው ጋር በመሆን ታህሳስ 25 ቀን 2013 ዓ.ም በግምት ከጠዋቱ 3፡00 አካባቢ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው ኒያላ ሞተርስ ኮርፖሬሽን ጀርባ በተለምዶ ወለጋ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ተከሳሾቹ የፌዴራል ፖሊስ ሙሉ የደንብ  ልብስ ለብሰውና የሰሌዳ ቁጥሩ ፖሊስ 0606 ኢ/ት መኪና ይዘው በማሽከርከር ወንጀሉን ለመፈጸም ወዳሰቡት ስፍራ ተጉዘዋል፡፡

ቦታው ላይ እንደደረሱም የግል ተበዳይ ወ/ሮ ነጻነት መሳፍንት እና አቶ ዲሪዮ ሞሬሎ መኖሪያ ቤት በቀጥታ ያመሩ ሲሆን የያዙትን መኪና ጡሩንባ በመንፋት በር እንዲከፈትላቸው ያደርጋሉ፡፡ 4ኛ የዐቃቤ ህግ ምስክርም የመኪና ጡሩንባውን በመስማቷ በሩን የከፈተች ሲሆን ተከሳሾቹ  ምስክሯን ገፍትረው ወደ ውስጥ በመግባት ሻምበል ሁሴን የተባለው 1ኛ ተከሳሽ 1ኛ እና 4ኛ የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን በመያዝና በማሰር በሀይል እየጎተተ ገንዘብ ያለበትን ቦታ እንዲያሳዩት ሲያደርግ 2ኛ ተከሳሽ ሽጉጥ ይዞ ዶላር፣ መሳርያ እና የካዝና ቁልፍ አምጡ ብሎ በማስፈራራት የተቀበላቸው ሲሆን 3ኛ ተከሳሽ 1ኛ የዐቃቤ ህግ ምስክርን ጸጉር ጨምድዶ በመደብደብ ይዛው የነበረውን ቴን ፕላስ ሳምሰንግ ጋላከሲ ወስዷል፡፡

ሌላው ለጊዜው ያልተያዘው ግብረአበራቸውም በያዘው ሴንጢ ቤት ውስጥ የነበረውን ኮመዲኖ (ብፌ) በመፈልቀቅ ውስጡ የነበረውን 50 ሺ ብር፣ የአንገት ሀብል፣ የጆሮ ወርቅ፣ የእጅ ብራስሌት በአጠቃላይ 47 ግራም 21 ካራት የወርቅ ጌጣጌጦችን የዋጋ ግምታቸው 93.000 (ዘጠና ሲስት ሺ) ብር የሚያወጡ አውጥቶ ሲወስድ 4ኛ ተከሳሽ 1ኛ የዐቃቤ ህግ ምስክርን የደህንነት ካሜራ ሰርቨር የት እንዳለ እንድታሳየው አስፈራርቶ እንድታሳየው ካደረገ በኋላ ለጊዜው ያልተያዘው ግብራበራቸው የዋጋ ግምቱ 50 ሺ ብር የሚወጣ የደህንነት ካሜራ መረጃ ቋቱን ነቅሎ ወስዷል፡፡

3ኛ ተከሳሽ ተመስገን ተወልደመድህን በበኩሉ የገንዘብ ማስቀመጫ ካዝናውን በመክፈትና ውስጥ የነበረውን 459 ሺ ብር፣ የዋጋ ግምቱ 1 ሺ ብር የሆነ ሁለት ዋሌት የኪስ ቦርሳ፣ የዋጋ ግምታቸው 12 ሺ ብር የሆነ የተለያየ ብራንድ ያላቸውን አራት ሽቶዎች፣ 1 ሳምሰንግ ኤስ ቴን፣ 2 ኤች ፒ ላፕቶፕ፣ ስድስት የተለያየ ማርክ ያላቸው የእጅ ሰዓቶች በአጠቃላይ የዋጋ ግምታቸው 269 ሺ ብር የሆነ ንብረት እና በብር ሲመነዘሩ 302 ሺ የሆኑ የተለያዩ አገራት ገንዘቦችን እንዲሁም ንብረትነቱ በግሪን ላንድ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ስም የተመዘገበ እና የግል ተበዳይ ወ/ሮ ነጻነት መሳፍንት የምታሽከረክረው ግቢ ውስጥ ቆሞ የነበረ የሰሌዳ ቁጥሩ 3-51797 አ/አ የዋጋ ግምቱ 3 ሚሊዮን ብር የሆነውን ጂፕ መኪና ቁልፍን ከተበዳይ ላይ በሀይል በመውሰድ መኪናን አስነስተው ወስደዋል፡፡

ተከሳሾቹ በአጠቃላይ የዋጋ ግምታቸው 4.114.240 (አራት ሚሊዮን አንድ መቶ አስራ አራት ሺ ሁለት መቶ አርባ) ብር ዋጋ ያለውን ንብረቶችንና ጥሬ ገንዘቦችን ወስደው ተሰውረዋል በሚል ጥቆማ የደረሰው ፖሊስ ባደረገው ጠንካራ ክትትል ሊያዙ ችለዋል፡፡

በዐቃቤ ህግ በበኩሉ የምርመራ ሂደቱን በመምራትና ተገቢውን ክትትል በማድረግ እንዲሁም ተከሳሾቹ የፈጸሙትን ወንጀል የሚያረጋግጡ አስፈላጊ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች እንዲሰባሰቡ በማድረግ ተከሳሾች በፈጸሙት በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ከባድ የውንብድና ወንጀል ክስ መስርቶ ስልጣኑ ላለው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ላከ፡፡

በዚህም መሰረት ተከሳሾች ድርጊቱን አልፈጸምንም ብለው ክደው ቃል የሠጡ መሆኑን ተከትሎ ዐቃቤ ህግ ማስረጃዎቹን አቅርቦ አሰምቷል፡፡ ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው ፍርድ ቤትም ዐቃቤ ህግ ያቀረባቸው ማስረጃዎች እንደ ክሱ ያስረዱ በመሆኑ ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቶ የተከሳሾችን መከላከያ ምስክር ለመስማት ቀጠሮ ይዟል፡፡(ፌ/ጠ/ዐ/ህግ)

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top