“ሕገመንግሥታዊ ማሻሻያ ያስፈልጋል!”
‹‹በየአካባቢው የሚፈጸሙ ዘርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እንዲቆሙና ሀገራዊ አንድነት እንዲጎለብት ሕገ መንግስታዊ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልጋል›› ሲሉ የሶማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አቶ ኢብራሂም ኡስማን አስታወቁ።
የሶማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አቶ ኢብራሂም ኡስማን ከአማራ ብዘኃን መገናኛ ድርጅት ጋር በወቅታዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዳይ ዙሪያ ቆይታ አድርገዋል።
የሶማሌ ክልል ላለፉት 30 ዓመታት ገደማ በትህነግ የተዛባ የፖለቲካ መስመር ተበድሎ የኖረ፣ ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ ለራሳቸው ስልጣን በሚጨነቁ የሞግዚት መሪዎች ሴራ የግጭት ማዕከል ሆኖ የቆየ ነው ብለዋል።
ከሦስት ዓመት ወዲህ እንደ ሀገር በተከናወነው ፓለቲካዊ የለውጥ እርምጃ የሶማሌ ክልል ሕዝብ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጥያቄዎቹ እየተመለሱለት መሆኑን የገለጹት አቶ ኢብራሂም በክልሉ የሚኖሩ ሕዝቦች ተከባብረውና ተሳስበው እየኖሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
‹‹በተለያዩ ክልሎች እየተፈጸሙ ያሉ ዘርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች አሁንም ማኅበረሰባዊ ስክነት አለመረጋገጡን ያሳያል ፤ ዜጎች በሀገራቸው ተንቀሳቅሰው የመኖር መብታቸው እንዲከበርና ሰብዓዊ ክብራቸው እንዲጠበቅ ብሎም እንደሀገር ለመቀጠል ሕገ መንግስታዊ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈልጋል››ነው ያሉት።
‹‹ሀገራዊ ክብራችንን ከፍ ያደረጉ ታሪኮቻችንን ከማጉላት ይልቅ ልዩነትን የሚያጎሉ የተዛቡ የታሪክ ትርክቶችን በመምዘዝ አንድነታችንን ለመሸርሸር የሚንቀሳቀሱ ኀይሎችን ሴራ በመገንዘብ ሕዝቡ ከጥፋት አጀንዳዎች ራሱን በማራቅ አንድነቱን ማጠናከር አለበት›› ብለዋል ምክትል ርእሰ መስተደድሩ፡፡
የሶማሌ ክልል የተረጋጋና የሕዝቦች መፈቃቀድ የጎላበት እንዲሆን መሪዎች አይነተኛ ድርሻ መወጣታቸውን የገለጹት አቶ ኢብራሂም እንደ ሀገር የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት መሪዎች ከመገፋፋት ይልቅ መደጋገፍን አማራጭ ሊያደርጉ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
‹‹የሀገር ሉዓላዊነትን ለማስደፈር ከውስጥና ከውጭ የሚንቀሳቀሱ ኀይሎችን እኩይ ተግባር የምናከሽፈው ዛሬም እንደ ትናንቱ አንድ ስንሆን ነው››ብለዋል ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ።(አብመድ)