Connect with us

” ይህ የቅዳሜ ምሽት ምርጥ ሙዚቃዎች ፕሮግራማችን ነው፤ አዘጋጅና አቅራቢ ታምራት አሰፋ ነኝ”

" ይህ የቅዳሜ ምሽት ምርጥ ሙዚቃዎች ፕሮግራማችን ነው፤ አዘጋጅና አቅራቢ ታምራት አሰፋ ነኝ"
Photo: Social media

ነፃ ሃሳብ

” ይህ የቅዳሜ ምሽት ምርጥ ሙዚቃዎች ፕሮግራማችን ነው፤ አዘጋጅና አቅራቢ ታምራት አሰፋ ነኝ”

” ይህ የቅዳሜ ምሽት ምርጥ ሙዚቃዎች ፕሮግራማችን ነው፤ አዘጋጅና አቅራቢ ታምራት አሰፋ ነኝ”

( ደመቀ ከበደ ፡ መሃል ሸገር)

ሞጣ ፡ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ነው ቤታችን። በዕድሜ ከገፉ አያቶቼ ጋር ነው ዕድገቴ። እርጅናቸውን በፀሎትና ምህላ በሚያመሰኩበት ዘመን እየጎረመስኩ ነበር።

ከአራት ዓይና ጎሹው ቅኔ ቤት ተማሪዎች የሚዥጎደጎደው ቅኔና ከቤተ ክርስቲያኑ የሚሰማው ቅዳሴና ፀሎት ለአያቴ ብርቅና ድንቅ ነበር። ዛሬ በብዙው ሊቆጨኝ ከመጤፍ ሳልቆጥረው አስኳላው ላይ በረታሁ።

ታዲያ ቤት ውስጥ ያለሁ ቅምጥል ብሆንም ብቸኛ ነኝ። ሌሎች ልጆች ሁሉ ራሳቸውን ችለዋል። የቀረሁት እኔ ነኝ ፡ በአያቶቼ ቤት።

ስንቀውጠው ውለን ከሰፈር ጓደኞቼ በጨለማ ስለያይ ቤት ውስጥ ብቸኛው አጫዋቼ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ነበር። ዛሬ ሁሉም አንጋፋ ጋዜጠኞች ቤተኛዬ ነበሩ ፡ ልክ እንደ አንድ ዘመድ ሲያወሩ ፣ ዜና ሲዘንኑ ፣ ሙዚቃ ሲያቀርቡ ወዘተ ስቱዲዮ ሳይሆን አንደኛ የቤታችን ክፍል ያሉ ይመስለኝ ነበር።

ቤት ካለሁ ሬዲዮ መክፈቴን ቤቱ እስኪነደል ድምፁን መበልቀጤን አልተውምና ቀን ሲሆን ጓሮ ነው የምሆነው ፡ ችባሃ የተሰኘች ዛፍ ነበረችን እሷ ስር እሆናለሁ።

በታምራት ሰበብ የአያቴን ምዝግዝግ እና ቁንጥጫ ብዙ ጊዜ ቀምሻለሁ። እደሰት እንጂ አላቄምም አልቆጭም ነበር።

ከሰኞ እስከ ሰኞ ያሉትን ፕሮግራሞች እከታተል ነበር። ከአቀራረብ እስከ መረጃና ሙዚቃ አመራረጥ እያንዳንዳቸውን በተለይም ከ1980ዎቹ እስከ 1990ዎቹ መጨረሻ / ነፍስ ካወቅሁበት ጀምሮ ዩኒቨርሲቲ እስከምገባ/ ያሉትን ጋዜጠኞች በደንብ አውቃቸዋለሁ።

በተለይ ለዜና ፋይሎችና ለቅዳሜና እሁድ መዝናኛ ዝግጅቶች አቅራቢዎች የተለየ ውዴታ ነበረኝ። ስማቸው ብዙ ነውና ዘርዝሬ አልጨርሳቸውም።

ዩኒቨርሲቲ ልገባ ስል አዲስ አበባ መጥቼ ዘነበወርቅ የሚገኘው ስቱዲዮ ሄጄ ሁሉንም አግኝቻቸዋለሁ። ሁለት ጋዜጠኞችን ግን አጣኋቸው። ጀርመን የሄደውን ነጋሽ መሃመድንና ከዚህ ዓለም የተለየውን ታምራት አሰፋን።

ጋዜጠኛ ከሆንኩ በኋላ የምወዳቸውንም የማደንቃቸውንም /ነጋሽንም በቅርቡ አግኝቸዋለሁ/ ሳገኝ ታምራት አሰፋን ሞት ስለቀደመኝ አዝናለሁ። 

እጅግ የበዛ ውዴታ አለብኝ ፣ እጅግ የበዛ ናፍቆትም ጭምር። ይድረሰው አይድረሰው ባላውቅም በርካታ ደብዳቤዎችን ፅፌለት ሁሉ ነበር።

እኔ የ 10 ኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ በ1994 ዓም ነው የተለየው። እንዴት እንደከፋኝ እስካሁን አልረሳውም።

ከዚያ በኋላ ያሉት ቅዳሜዎች ለኔ ዱልዱሞች ነበሩ።

ታምራት አሰፋ በቅርቡ ታላቄ ጀሚል ይርጋ የተለያዩ መረጃዎችን አጣቅሶ እንዳሰፈረው በ1945 ዓም ነው የተወለደው አዲስ አበባ ፡ ሽሮሜዳ።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በአምኃ ደስታ፣ የሁለተኛ ደረጃን ደግሞ በምሥራቅ አጠቃላይ ተምሮ አጠናቋል። ከመደበኛ ትምህርት በኋላ የመምህርነት ኮርሶችን የወሰደው ታምራት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሥራ የተሠማራው በመምህርነት ነበር – በወላይታ ሶዶ። 

የመምህርነት ሙያውን ከተወ በሁዋላም በነበረው የሙዚቃ ፍቅር ምክንያት በምድር ጦር ለሦስት ዓመታት የሙዚቃ ሥልጠና በመውሰድ በኢትዮዽያ ሬድዮና በተለያዩ ቦታዎች የሙዚቃ ኦርኬስትራ በመቀጠር የሳክስፎን ተጫዋች ሆኖ አገልግሏል።

በጋዜጠኛ ጀሚል መረጃ መሰረት በ1971 ዓም በድምፅ ላይብረርያንነት በጣቢያው ቋሚ ሠራተኛ ሆኖ የተቀጠረው ታምራት በሂደት ራሱን በሥልጠናና ፣ በልምድ በማብቃት በጣቢያው ከነበሩ ተወዳጅ የመዝናኛ ክፍል ጋዜጠኞች አንዱ ለመሆን የበቃ ነበር።

እስከ 1990ዎቹ መጨረሻ ድረስ የነበሩት ዓመታት የውጪ ሀገር ሙዚቃዎች ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ እንደልብ የሚገኙ አልነበሩም ቢባል ማጋነን አይለም። ዘወትር ቅዳሜ ምሽት በኢትዮጵያ ሬድዮ ከ4:00 ዜና በኋላ የሚተላለፈውንና በታምራት አሰፋ ተዘጋጅቶ የሚቀርበው “የባህር ማዶ ምርጥ ሙዚቃዎች ዝግጅት “ዋነኛ አማራጭ” ነበር – ለብዙዎቻችን። 

በተጨማሪም ታምራት በየአሥራ አምሥት ቀናት አንዴ በእሁድ ጠዋት መዝናኛ ፕሮግራም ላይ በአዘጋጅነትና በዝግጅቱ አጋፋሪነት ከመሥራቱ ባሻገር ከጋዜጠኛ በልሁ ተረፈና ፣ ደምሴ ዳምጤ ጋር በመሆን የእሁድ ከሠዓት የ”ዝክረ ሰንበት” ዝግጅት ላይ እጅግ የሚወደድ የነበረ “የተማሪዎች ጥያቄና መልስ ውድድር” ያዘጋጅም ነበር።

በኢትዮጵያ ሬድዮ በእሁድ ጠዋት ፕሮግራም አዘጋጅነቷ የምትታወቀው ጋዜጠኛ አባይነሽ ብሩ የዛሬ ዓመት ገደማ ከ”ታዛ” መፅሔት ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ ስለ ታምራት በሰጠችው ምስክርነት … “የእሁድ ጠዋት መዝናኛ ዝግጅት ከሚፈጥረው የሥራ ጫና አኳያ አንዳንዴ የቴክኒሻኑን ቦታ የሚሸፍንልን ነፍሱን ይማረውና ታምራት አሰፋ ነበር። 

ቴክኒሻኖቻችን ስለሚደክማቸውና ስለሚሰለቻቸው እሱ በፍላጎቱ ያግዛቸዋል። ታምራት የሙዚቃ ሰው፣ የፕሮግራም

ሰው፣ የቃለመጠይቅ ሰው፣ ብስል ያለ የሬዲዮ

ጋዜጠኛ ነበር።” በማለት ሁለገብ ባለሙያነቱን ገልጣለች።

ልሳነ መልካሟ ጋዜጠኛ መዓዛ ብሩም ስለ ታምራት አሰፋ ተባባሪነትና መልካም ጠባይ ስትናገር ‘በጨዋታ ዝግጅት’ ጅማሮ ሰሞናት FM Addis 97.1 ላይ ሳሉ ይገጥሟቸው የነበሩትን አንዳንድ ተግዳሮቶች በመቅረፍ በኩል ትልቅ ውለታ እንደዋለላቸው ገልፃለች።

ከ23 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ ሬድዮ ያገለገለው ጋዜጠኛ ታምራት አሰፋ ባደረበት ሕመም ምክንያት ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ታህሣሥ 8/1994 ሲሆን የቀብር ሥነስርዓቱም የተፈፀመው በቀጨኔ መድኃኔዓለም ነበር ብሏል ጀሚል።

የጋዜጠኝነት ዘርፉ ብዙ ነውና በየዘርፉ የማደንቃቸው፣ የማከብራቸውና አርአያ የማደርጋቸው ብዙ ናቸው። ህትመት ጋዜጠኝነት ላይ ፣ ሬዲዮ ላይ፣ ቴሌቪዥን ላይ የተለያዩ ሰዎች አሉኝ። በዚያው ልክም በዜና ፣ በትምህርታዊ እና በመዝናኛ ፕሮግራም እንደየዘውጉ ሞዴሎች ሞልተውኛል።

እና ብዙ የምወዳቸውና የማከብራቸውን መዘከር እንደነበረብኝ ይገባኛል፣ ግን የታምራት ነገር ሁሌም ይቆጨኛል። ሳላገኘው መሞቱና ብዙ ሰው ስለእሱ ህይወት ታሪክ አለማወቁ። በዚያም ላይ ሬዲዮ መዝናኛ ላይ ነው ነፍሴ ያለችው።

ስለ ታምራት ብዙ ማወቅ እሻለሁ።

ታምራት በመዝናኛው የሬዲዮ የጋዜጠኝነት ዘርፍ አብነቴ ነው ፡ ሞዴሌ። ሬዲዮ ላይ ከዜና በፊት መዝናኛ እሰራ ሳለሁ ስቱዲዮ የምገባው እሱን እያሰብኩ ነበር።

እንጀራ ሆነና ብዙ ብባክንም አንድ ቀን የእሱን ዝክር ትልቅ ፕሮግራም በአዳራሽ ከወዳጆቹ ጋር ማዘጋጀቴ አይቀርም።

የሬዲዮ ቀን ነውና ነው ዛሬ ታምራትን ማውሳቴ።

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top