የ13 ዓመት ታዳጊ አማሟት የፖሊስ ቃል
ሰሞኑን በተለያዩ ማህበራዊ ድረ-ገፆች ላይ የ13 ዓመት ታዳጊ ህፃን በሰው ተወስዶ ተገደለ በሚል የሚናፈሰውን መረጃ መሰረት አድርጎ የምርመራ ሂደቱን አጠናክሮ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ሟች ይስሃቅ አብርሃም የ13 ዓመት ዕድሜ ያለው ታዳጊ ሲሆን ቦሌ ሩዋንዳ አካባቢ በሚገኝ ፕሬስ ቲጂ በሚባል የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ የ8ኛ ክፍል ተማሪ ነው፡፡
የወንጀል ምርመራ መዝገቡ እንደሚያስረዳው ጥር 25/2013 ዓ.ም ከቀኑ 6፡00 ሰዓት አካባቢ የጠፋ መሆኑን ለፖሊስ ሪፖርት የተደረገ ሲሆን ፖሊስ ሪፖርቱ ከደረሰው ሰዓት ጀምሮ የምርመራ መዝገብ አደራጅቶ ክትትሉን ቀጥሏል፡፡
ጥር 28 ቀን 2013 ዓ.ም ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ቦታው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ጀርባ ለመሰረተ ልማት በተቆፈረ እና ውሃ በተጠራቀመበት ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ ህይወቱ አልፎ የተገኘ ሲሆን ፖሊስ በአካባቢው ላይ የተለያዩ የቴክኒክ እና የሰው ማስረጃዎችን በማሰባሰብ አስክሬኑን ለምርመራ ወደ ዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል ልኳል፡፡
ከአ/አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ዘርፍ ያገኘነው መረጃ እንደሚያስረዳው የሆስፒታል የአስክሬን ምርመራ ውጤቱ የካቲት 2 ቀን 2013 ዓ.ም ከሆስፒታሉ የተላከ ሲሆን አሟሟቱን የሚገልጸው ውጤት እንደሚያስረዳው ታዳጊው በውሃው ታፍኖ በተለይም ወደ አንጎል የሚገባው የአየር መጠን መቋረጥ እና የአንጎል መጎዳት እንደሆነ ይገልፃል፡፡
ምንም እንኳን የአስክሬን የምርመራ ውጤቱ በውሃ በመታፈን ምክንያት ታዳጊው ለሞት መዳረጉን ቢገልፅም ሌሎች የቴክኒክ እና አካባቢያዊ መረጃዎችን በማሰባሰብ የምርመራ ሂደቱ መቀጠሉን እና አጠቃላይ የምርመራ ውጤቱ ሲጠናቀቅ ለህዝብ እንደሚገለፅ ኮሚሽኑ ጨምሮ አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ ባስተላለፈው መልዕክት የተለያዩ ግለሰቦች በማህበራዊ ሚዲያ በመጠቀም ያልተረጋገጡና ከሚመለከተው አካል ያልተሰጡ የተዛቡ መረጃዎችን በማስተላለፍ ህብረተሰቡ ውዥብር ውስጥ እንዲገባ ማድረጋቸው ተገቢነት የሌለው መሆኑን ገልፆ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስቧል፡፡
በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ ያለው ማንኛውም ሰው በ0111 11 01 11 ወይም በነፃ የስልክ መስመር 991 ላይ በመደወል መረጃ መስጠት እንደሚቻል ኮሚሽኑ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡(አ/አ ፖሊስ ኮምሽን)