አንድ ሰው ሁለት ቦታ በአንዴ ቢሆን እኔ ዛሬ እስቴም አጅባር ሜዳም መሆን ነበረብኝ፤ ግን አጅባር ሜዳ ነኝ፡፡
(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም በፈረስ ጉግስ ደምቆ ስለሚከበረው የደብረ ታቦሩ አጅባር ሜዳ እና የእስቴው የመርቆሪዎስ በዓል አንድ ሰው አንድ ባይሆን የማይቀርባቸው ሁለት ቦታዎች በአንድ ቀን በተመሳሳይ ኩነት ሲል ውሎውን እንዲህ ያካፍለናል፡፡)
(ሄኖክ ስዩም ~ በድሬ ቲዩብ)
አንድ ሰው በአንድ ቀን መሆን የሚችለው አንድ ቦታ ነው፡፡ አንድ ቦታ ነኝ፡፡ ሁለት ቦታ በአንድ ጊዜ መሆን ብችል ዛሬ እስቴና አጅባር በሆንኩ፤ ሁለት ቦታ አንድ ቀን ልዩ የሆነ ሁለት ኩነት በአንድ ሃይማኖታዊ መሰረት፡፡
እኔ ግን አጅባር ሜዳ ነኝ፡፡ የሠይፈ አርእድ ሙሽራ ሠርጓ ነው፡፡ የታቦር ተራራ ከእልልታው ብዛት ዛሬ ከጉም ፈክቷል፡፡ ጉና ድረስ የጎነ ሆታ ይሰማኛል፡፡ ፈረሰኛው ፈረሰኛውን ሰማዕት ያጅባል፡፡ ጥምቀትን ለመሸኘት መጥቻለሁ፡፡ ጥርንም እሸኘዋለሁ፡፡ መርቆሪዎስ ነግሶ ጥር የለም፡፡ እነሆ ጥር ሃያ አምስት፤ ደብረ ታቦር፡፡
የብርሃን ተራራዋ በብርሃን ደምቃለች፡፡ የፈረሰኛው ጨዋታ ተአምር ሆኖብኛል፡፡ ብዙ ጊዜዬ ነበር፡፡ ብዙ ናፍቄዋለሁ፡፡ ተገናኘን፡፡ እንዲህ ማየት የሚቻለው ዳግም የዛሬ አመት ነው፡፡ መርቆሪዎስ ለመጣ፡፡
ትናንት የመርቆሪዎስ ታቦት ወደ ጥምቀተ ባህሩ ወርዷል፡፡ የጥምቀት ድባብ ማብቂያ ከመግቢያው ይበልጥ እንደሚደምቅ አየሁ፡፡ ፋርጣ ድምቅ ብላለች፡፡ ደብረ ታቦር በነጠላቸው ንጣት ብርሃን የሆኑ እናቶች ስሟን መስለዋታል፡፡
የሦስት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች ክብርት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ የክልል ከፍተኛ ኃላፊዎች። የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ። የከተማዋ ከንቲባና የሀገረ ስብከቱ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ በክብር እንግድነት ታድመዋል።
ጉግሱ ተአምር ነው፡፡ ውድድሩ እንዲህ አብሮ ለሌለ ሰው ቀለል ተደርጎ ሊገለጽ አይችልም፡፡ ድምቀቱን ለማየት አይደለም መስማት ዳር መቆምም ቢሆን አይስተካከለውም፡፡ ደማቁ ኩነት ተናፋቂ ነው፡፡ አጅባር ሜዳ፤ በጌ ምድር፤
በጌ ምድር ከፈረስ ጋር ሰንብቷል፡፡ ከቀናት በፊት ከዙርአባ በታች ጊዮርጊስ በፈረስ ሲነግስ አይቻለሁ፡፡ ከክምር ድንጋይ ግርጌ ተአምር ሲሆን ደርሻለሁ፡፡ ዛሬ የሁሉም ማጠናቀቂያ ነው፡፡ ሩቅ አይደለም፤ ሁሉንም በምስል ጭምር አሳያችኋለሁ፡፡ ከርሞ መች ይሆን ተመልሶ የሚመጣው እያልኩ ነው፡፡ አንቺ ደብረ ታቦር እንደምን ታድለሻል?