Connect with us

ኢዜማ ከሰባት ወራት በፊት ስለአዲስአበባ ከተማ የመሬት ወረራ ምን ብሎ ነበር?

ኢዜማ ከሰባት ወራት በፊት ስለአዲስአበባ ከተማ የመሬት ወረራ ምን ብሎ ነበር?
Photo: Social media

ዜና

ኢዜማ ከሰባት ወራት በፊት ስለአዲስአበባ ከተማ የመሬት ወረራ ምን ብሎ ነበር?

ኢዜማ ከሰባት ወራት በፊት ስለአዲስአበባ ከተማ የመሬት ወረራ ምን ብሎ ነበር?

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) በአዲስ አበባ ከተማ በስፋት ሲከናወኑ ነበሩ ባላቸው የመሬት ወረራ እና የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) ህገ ወጥ ዕደላን በተመለከተ …. ሰኞ ነሐሴ 25 ቀን 2012 ይፋ የዳሰሳ ጥናት ይፋ አድርጓል። 

ለመገናኛ ብዙሃን የተሰራጨው ይህ ጥናት፤ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሕገ ወጥ መንገድ የሚደረጉ የመሬት ወረራዎች እና ከህግ አግባብ ውጪ የሚደረጉ የጋራ መኖሪያ ቤት እደላዎች እንዳሉ ፓርቲው በማስረጃ ማረጋገጡን አትቷል።

በአስራ ሶስት ገጾች የተዘጋጀው ይህ ጥናት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በከተማይቱ “ታይቶ በማይታወቅ መጠን እና ስፋት ግልጽ የሆነ የመሬት ወረራ እና ሕገ ወጥ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕደላ ተደርጓል” ሲል ወንጅሏል። 

ጥናቱ ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ ተደርጎባቸዋል የተባሉ እና በአዲስ አበባ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች ያሉ ዘጠኝ አካባቢዎችን ሁኔታ በማሳያነት ጠቅሶ ዝርዝር ሁኔታቸውን አስቀምጧል።

“ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ ተግባር በሃገራችን አዲስ ያልሆነ እና በተለያዩ ጊዜዎች እና አካባቢዎች ትልቅ ችግር ሆኖ የቆየ ቢሆንም በአዲስ አበባ ከተማ ግን በዚህ ደረጃ እና ፍጥነት የተስፋፋበት ጊዜ አልነበረም”

“ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ ተግባር በሃገራችን አዲስ ያልሆነ እና በተለያዩ ጊዜዎች እና አካባቢዎች ትልቅ ችግር ሆኖ የቆየ ቢሆንም በአዲስ አበባ ከተማ ግን በዚህ ደረጃ እና ፍጥነት የተስፋፋበት ጊዜ አልነበረም” ያለው ኢዜማ፤ “የመሬት ወረራው በብዙ የከተማው አካባቢዎች እና ሰፋፊ መሬቶችን ዒላማ ያደረገ፤ በተናጥል የሚደረግ ሳይሆን በተቀናጀ መልኩ የሚፈፀም” መሆኑን በጥናት ማረጋገጡን ገልጿል።

“[የመሬት] ወረራው የከተሞችን አረንጓዴ ቦታዎች፣ የወንዝ ዳርቻዎች እንዲሁም ለመሰረተ ልማት አውታር ዝርጋታ በፕላን የተከለሉ ቦታዎችን ያካተተ በመሆኑ የጉዳቱን መጠን ከፍተኛ አድርጎታል” ብሏል የፓርቲው ጥናት።

በመሬት ወረራው ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ የነበሩት ግለሰቦች “ቦታዎቹ ከዚህ ቀደም የቤተሰቦቻችን መሬቶች ናቸው እና በቂ ካሳ ሳይከፈለን ከቦታችን ተነስተናል” የሚሉ ግለሰቦች መሆናቸውን ያመለከተው የኢዜማ ጥናት፤ የየአካባቢዎቹ የመንግስት ኃላፊዎችም ለድርጊቱ ድጋፍ በመስጠት መሳተፋቸውን ጠቁሟል። 

“ይህ በጠራራ ጸሀይ በተደራጀ መልኩ የተፈፀመው የመሬት ወረራ፤ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያሉ አመራሮችና የፍትህ አካላት ተጠሪዎች ከፍተኛ እገዛ የተደረገበት ብቻ ሳይሆን እነዚህ አካላት የጉዳዩ ዋና ተዋንያን ነበሩ” የሚለው የኢዜማ ጥናት አመራሮቹ “በተለያየ መልኩ ሊጠቅሟቸው ለሚፈልጉ ግለሰቦች፣ ቡድኖች እና አደረጃጀቶች መሬቱን ወረው እንዲይዙ አመቻችተዋል። 

የመንግሥትን ሥልጣን ለሕገ ወጥ ተግባር ከለላ እና ሽፋን እንዲሆን አድርገዋል። ከዚህም ባስ ሲል ከግለሰቦች ጋር በመመሳጠር እራሳቸው ወረራ ፈፅመዋል” ሲል ወንጅሏል።

 

የከተማይቱ ባለስልጣናት ይህን መሰል ድርጊት በጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕደላም መስተዋሉን ፓርቲው በጥናቱ ገልጿል። “የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢ-ፍትሐዊ በሆነ መልኩ ፈጽሞ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ለማይገባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች ቤት የማስተላለፍ ተግባር እንደፈፀመና እየፈጸመ መሆኑን አረጋግጠናል” ያለው ጥናቱ ለዚህም ከሁለት ሳምንት በፊት ከስልጣናቸው የተነሱትን ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ እና ካቢኔያቸውን በስም ሳይጠቅስ በደፈናው ተጠያቂ አድርጓል።

የኢዜማ ጥናት ከሁለት ሳምንት በፊት ከስልጣናቸው የተነሱትን ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ እና ካቢኔያቸውን በስም ሳይጠቅስ በደፈናው ተጠያቂ አድርጓል።

“የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለማስተላለፍ የወጣውን መመሪያ በመቀየር በግለሰብ ትዕዛዝ ቤቶች በሕገ ወጥ መንገድ ከታለመላቸው ዓላማ ውጪ እንዲሰጡ ምቹ ሁኔታን መፍጠሩ በጥናቱ ተረጋግጧል” ብሏል ኢዜማ።

“ቤቶችን እንደፈለጉ ያድሉ ነበር” በሚል በጥናቱ የተከሰሱት የአዲስ አበባ ከፍተኛ አመራሮች፤ ይህንን ድርጊታቸውን የፈጸሙት “ኢፍትሐዊ ሕጎችን እና መመሪያዎችን በማውጣት እና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ሕጎችን እና ደንቦችን በማሻሻል” እንደሆነ ተመልክቷል። ጥናቱ በ2011 እና 2012 የወጡ፤ ለከንቲባው እና ካቢኔው “ልዩ ሥልጣን” ሰጥተዋል የተባሉ መመሪያዎች በጥናቱ በማጣቀሻነት አቅርቧል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በየካቲት 2011 ዓ. ም ለ51 ሺህ ገደማ ተመዝጋቢዎች የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለማደል ዕጣ ማውጣቱን ያስታወሰው የኢዜማ ጥናት፤ በወቅቱ ቃል ከተገባው በተቃራኒ ከዕድለኞቹ ውጭ ያሉ ግለሰቦች ቤቶቹ መከፋፈላቸውን አትቷል። 

ቤቶቹ “ውስጥ ለውስጥ ታድለዋል” የሚለው ጥናቱ በዚህም ተጠቃሚ የሆኑት “የራሳቸው ድርጅት አባላት፣ ሹማምንቶች፣ የማይታወቁ ግለሰቦች እና ቡድኖች” መሆናቸውን አብራርቷል።

ከአዲስ አበባ ወሰን ውጪ ተገንብተዋል በሚል ሲያወዛግቡ የቆዩት የኮየ ፈጬ እና ሌሎች የኮንዶሚኒየም “ሳይቶች” ጉዳይም በኢዜማ ጥናት ተዳስሷል። በእነዚህ አካባቢዎች ለተገነቡ ኮንዶሚኒየሞች የተከናወነው”የዕጣ አወጣጥ እና አጠቃቀም ከመመሪያ ጀምሮ ችግር ያለበት መሆኑ ግንዛቤ መያዝ ተችሏል” ሲል ፓርቲው በጥናቱ አስፍሯል።

ከአዲስ አበባ ወሰን ውጪ ተገንብተዋል በሚል ሲያወዛግቡ የቆዩት የኮየ ፈጬ እና ሌሎች የኮንዶሚኒየም “ሳይቶች” ጉዳይም በኢዜማ ጥናት ተዳስሷል

“የአስተዳደሩ ቤቶች ልማት ቢሮ፤ የጋራ መኖሪያ እና የንግድ ቤቶችን ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ ወጥቶ የጸደቀውን መመሪያ ቁጥር 3/2011፣ ሰኔ 2011 ዓ.ም እና ከመመሪያው ቀድሞ የካቲት 27 ቀን 2011 ዓ.ም ዕጣው ለሕዝብ የተገለፀውን ተግባር ላይ ሳይውል ቆይቶ፤ ከዕጣ አወጣጡ በኋላ የወጣውን የአዲስ አበባ ከተማ ግብርና ማስፈጸሚያ ከላይ በተጠቀሰው መመሪያ ተክተው መሥራታቸው ሕግን የጣሰ ነው” ብሏል ጥናቱ።

ኢዜማ “በሕገ ወጥ መንገድ እየተካሄደ ነው” ያለው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕደላ እስካለፈው ሰኔ ወር አጋማሽ ድረስ መቀጠሉን በጥናቱ ጠቁሟል። በአዲስ አበባ ባሉ ቢሮዎች የሚያገለግሉ የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ሠራተኞች በሺህዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን ለማግኘት ተመዝግበው በሰኔ ወር የድልደላ ዕጣ እንደወጣላቸው ጥናቱ በማሳያነት ጠቅሷል።   

“ሁሉም ሠራተኞች የኮንዶሚኒየም ብሎክ ቁጥር እና የቤቱን ቁጥር በስማቸው ተረጋግጦ የተሰጣቸው ሲሆን፣ በተሰጣቸው የቤት ቁጥር የነዋሪነት መታወቂያ የተዘጋጀላቸው መሆኑን ለማወቅ ችለናል፡፡ 

ይህን ለማስፈጸም በኦሮሚያ ክልል ጽሕፈት ቤት በኩል ኮሚቴ ተቋቁሞ ኮንዶሚኒየም ቤቶች በሚገኙባቸው ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ወረዳዎች መታወቂያ የተሠራላቸው መሆኑን ከአካባቢው ነዋሪዎች መረጃዎች ተገኝተዋል” ሲል የኢዜማ ጥናት አትቷል።

ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ሰራተኞች በተጨማሪ “የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች፣ ልጅ እና የልጅ ልጅ” በሚል ለተመዘገቡ ግለሰቦች፤ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሕንጻዎች ውስጥ ያሉ የንግድ ቤቶች እንደታደላቸው ተጨባጭ ማስረጃዎች መገኘታቸውን ጥናቱ ገልጿል። እነዚህ የኮንዶሚኒየም የንግድ ቤቶች በእግር ኳስ ደጋፊነት ስም ለተሰባሰቡ ማኅበራት በተመሳሳይ ሁኔታ መከፋፈላቸውንም ጥናቱ ጠቁሟል።

ኢዜማ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕደላም ሆነ በመሬት ወረራ ታይተዋል ያላቸው “ሕገ ወጥ ተግባሮች” ተጽዕኗቸው “ዛሬን የሚሻገር ለነገም የሚተርፍ ነው” ሲል በጥናቱ አሳስቧል። ድርጊቱ “የኅብረተሰቡን ቀጣይ ህግን የማክበር ባሕሪ በከፍተኛ ደረጃ የሚጎዳ በመሆኑ ጥፋቱ የከፋ ነው” ሲልም አጽንኦት ሰጥቷል።

ኢዜማ በጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕደላም ሆነ በመሬት ወረራ ታይተዋል ያላቸው “ሕገ ወጥ ተግባሮች” ተጽዕኗቸው “ዛሬን የሚሻገር ለነገም የሚተርፍ ነው” ሲል አሳስቧል

“ሀገር እና ሕዝብ የሰጣቸውን አደራ ችላ በማለት ሥልጣናቸውን ለሕገ ወጥ ተግባር እየተጠቀሙ ያሉ የከተማው የመንግሥት ኃላፊዎች ሕጋዊ ተጠያቂነታቸው አይቀሬ ነው” ሲል የተነበየው ኢዜማ፤ በተመሳሳይ ተግባራት የተሳተፉ ደላሎች፣ ሕገ ወጥ መሬት ተቀባዮች ገዢዎችም ሆኑ ሻጮች ከተመሳሳይ እርምጃ እንደማያመልጡ አስጠንቅቋል።

ኢዜማ፤ ስልጣን ላይ ያለው መንግስት በጥናቱ የተገኙት ውጤቶች እና ድምዳሜዎችን ተመልክቶ የሕግ የበላይነትን እንዲያስከብር በጥናቱ ጠይቋል። “በወንጀል ጭምር መጠየቅ ያለባቸውን የመንግስት ኃላፊዎች እንዳሉ” እናምናለን ያለው ተቃዋሚ ፓርቲው፤ የመንግስት ህግ የማስከበር እርምጃ እነርሱንም ጭምር ያካተተ መሆን እንዳለበት አሳስቧል።   

“እስከዛሬ በነበረው ሥርዓት እንደሚደረገው በሥልጣናቸው ያለአግባብ የተጠቀሙ እና ሥልጣናቸውን ለግል ጥቅማቸው ወይም የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የተጠቀሙ ባለሥልጣናት ከቦታቸው ገለል በመደረግ ወደሌላ ሥልጣን የሚዛወሩበት ሳይሆን ላደረሱት ጉዳትና ለፈፀሙት ወንጀል በሕግ አግባብ የሚጠየቁበት ሥርዓት ሊበጅ ይገባል” ብሏል ኢዜማ።

ባለስልጣናቱን ተጠያቂ በማድረግ ቀዳሚ ሚና ያላቸው “የፍትህ ተቋማት ናቸው” የሚል እምነቱን በጥናቱ ያንጸባረቀው ኢዜማ፤ በጥናቱ የደረሰባቸውን ወንጀሎች እና ሥልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ማስረጃዎች ለሚመለከታቸው አካላት ለማስገባት ማቀዱን ጠቁሟል። 

በዚህም መሰረት ፓርቲው በማስረጃዎች የተደገፈ “የወንጀል ይጣራልኝ” አቤቱታ ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ ለፌደራል ሥነ ምግባር እና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን እና ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እንደሚያስገባ አስታውቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር – ተስፋአለም ወልደየስ)

 

Click to comment

More in ዜና

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top