በመተከል ጥቃት ጉዳይ ፓርላማው ቁርጥ ውሳኔ አሳለፈ
~ የዜጎች ሞት፣ መፈናቀልና ንብረት መውደም ስለሚቆምበት ሁኔታ እና ተጎጂዎች በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ለማድረግ የሚሰራ ቡድን እንዲቋቋም ውሳኔ ተላለፈ፣
ተከል ዞንን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የሚታየው የዜጎች ሞት፣ መፈናቀልና ንብረት መውደም በአስቸኳይ ስለሚቆምበት ሁኔታ እና ተጎጂዎች ተገቢውን ድጋፍ አግኝተው በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ለማድረግ ከምክር ቤቱ አባላት የተውጣጣ ራሱን የቻለ ቡድን እንዲቋቋም ውሳኔ ተላለፈ፡፡
ኢፌዴሪ 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዓመት የስራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ አካሂዷል፡፡
የሚቋቋመው ቡድን የሚደርሱ ጉዳቶችና በየጊዜው የሚታየውን ለውጥ እየተከታተለና እየገመገመ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳቦችን የሚያቀርብ ነው ተብሏል፡፡
ምክር ቤቱ በዛሬው መደበኛ ስብሰባው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን እና በሌሎች አንዳንድ የሃገሪቱ አካባቢዎች በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አስመልክቶ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡
በውሳኔው ሃሳቡ ላይ ሶስት ዋና ዋና ጭብጦችና ስድስት ውሳኔዎች ተካተውበታል፡፡
በዋና ዋና ጭብጦች ውስጥም በንጹሃን ዜጎች ላይ ማንነትን መሰረት ያደረገ አሰቃቂ ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ መፈናቀልና የንብረት መውደም መድረሱ ተረጋግጧል፡፡
መንግስት የተፈጠረውን ችግር ለማስቆምና የተጎዱ ዜጎችን ለመደገፍ እንዲሁም አጥፊዎችን ለህግ እንዲቀርቡ ለማድረግ የበኩሉን ጥረት እያደረገ መሆኑም በዚህ ወቅት ተመላክቷል፡፡
የንጹሃን ዜጎች ግድያ፣ አካል ጉዳት፣ መፈናቀል እና የንብረት ውድመት የተወሰሳበውና ቶሎ ሊቆም ያልቻለው ድብቅ የፖለቲካ አላማ ባላቸው አካላት ህገ መንግስታዊ መብትን ጥየቄ ውስጥ በሚያስገባ መልኩ ሲነዛ የነበረው የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ እና የተለያየ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው የውስጥ እና የውጭ የጥፋት ሃይሎች በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ አመራሮች ጽንፈኛ ሚዲያዎችን በመጠቀም መንግስትን ለማዳከምና የተጀመረውን ሃገራዊ ለውጥ ለመቀልበስ ሲሰሩ መቆየታቸው በዋና ዋና ጭብጦች ውስጥ ተካተዋል፡፡
በውሳኔ ሃሳብ ውስጥ ደግሞ መንግስት የህብረተቡን የቆየ አብሮነት ለማስቀጠል ህዝቡን ያሳተፈ ተከታታይና ቀጣይነት ያለው የፖለቲካ ስራና የህዝብ ማወያየት ስራ መስራት እንደሚገባው ተነስቷል፡፡
የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥም ትኩረት ሊሰጠው ይገባልም ነው የተባለው፡፡
መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ እንዲቀጥልና ከዚህ ጎን ለጎን አመራሩን በማጥራት ጥፋተኞች ላይ ተገቢውን ህጋዊ እና ፖለቲካዊ እርምጃ መውሰድና ውጤቱን ለህዝብ ማሳወቅ እንደሚገባውም ተነስቷል፡፡
ሚዲያዎች ህግና ስርአትን ተቀብለው እንዲሰሩ የሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ህግን በሚጥሱት ላይ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ፤ መንግስት የጀመረውን ተፈናቃይ ዜጎችን የመደገፍ ስራ በማጠናከር ወደነበሩበት ቀየ መመለስና በዘላቂነት ማቋቋምና ለተጎጅዎች የስነ ልቦና ስራ እንዲሰራም አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡
የምክር ቤቱ አባላትም መንግስት በመተከል ዞን የተፈጠረውን ችግር በመደበኛው ህግ ለመቆጣጠርና ማስቆም ካልቻለም ህግና ስርአትን ለማስከበር ሌላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሳያስፈልግ በትግራይ ክልል ታውጆ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማስፋት በመተከል ዞንም ተግባራዊ እንዲያደርግና የጀመረውን የህግ የበላይነት የማስከበር ስራ በዚህ አዋጅ መሰረት ማከናወን ይችላል ብለዋል፡፡
ምክር ቤቱ በዝርዝር ከተወያየበት በኋላ በአራት ተቃውሞ እና በሁለት ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል፡፡(ኤፍ ቢ ሲ)