የጸጥታ ስጋት ያጠላበት የባይደን በዓለ ሲመት
(እሱባለው ካሳ)
46ኛው ተመራጩ የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ፕሬዚደንት ጆይ ባይደን ዛሬ በይፋ ቃለ መሀላ ፈጽመው ስልጣናቸው የሚረከቡበት ቀን ነው፡፡ ሥነ ሥርዓቱ የሚከወነው በአሜሪካ ታሪክ ለየት የሚያደርገው በቅርቡ በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ህንጻ ላይ በተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች የአመጽ ጥቃት በተፈጸመበት ሰሞን የሚከናወን መሆኑ ነው፡፡
ተሰናባቹ የቀድሞ ፕረዝደንት ሚስተር ትራምፕ እስከአሁኗ ደቂቃ ድረስ የሚያስቡት አሸናፊ ስለመሆናቸው ብቻ ነው፡፡( BBC:- Mr Trump has still not fully accepted the result of last November’s election, which he lost to Democrat Joe Biden….) ስልጣናቸው ጀምበር እያዘቀዘቀች መሆኑን አስቀድመው ከተረዱበት ደቂቃ ጀምሮ ምርጫው ስለመጭበርበሩ ደጋግመው ተናግረዋል፡፡ ገና የምርጫ ሒደቱ፣ የድምጽ ቆጠራው በወጉ ሳይጠናቀቅ እሳቸው ድምጼን ተቀማሁ በሚል ለደጋፊዎቻቸው ስሞታ ከማቅረብ አልፈው አቤቱታ አስገብተው ውጤቱን ለመቀየር እልህ አስጨራሽ ትግል አድርገዋል፤ ግን አንድም ሕጋዊ አካል የሰማቸው አልነበረም፡፡
በአንጻሩ ርጋታና ጨዋነት የተካኑት የ79 ዓመቱ አዛውንት ተመራጭ ፕሬዚደንት ጆይ ባይደን ለትራምፕ መንፈራገጥ እምብዛም ቁብ ሳይሰጡ አነታራኪውን መንገድ ተጉዘው እነሆ ለዛሬዋ ታሪካዊ ቀን በቅተዋል፡፡
ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ በአንድ በኩል አዲስዋን ፕሬዚደንት ለመቀበል ሽር ጉድ ስትል በሌላ በኩል ጋጠወጥ የትራምፕ ደጋፊዎች ምናልባትም በጦር መሳሪያ የታገዘ አመጽና ሁከት ሊያስነሱ ይችላሉ በሚል ስጋት ተወጥራለች፡፡ እምብዛም ባልተለመደ መልኩ የጸጥታ ስራው ጥብቅ ሆኖ ሰንብቷል፡፡
የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች ከሳምንት በፊት የሀገሪቱ ምክር ቤት የሚገኝበት የካፒቶል ሕንጻን ከወረሩ እና ጉዳት ካደረሱ በኋላ ውጥረት ሰፍኗል፡፡ የሀገሪቱ መከላከያ ከውስጥ ጥቃት እንዳይነሳበትም በብርቱ ተሰግቷል፡፡ ሲኤንኤን እንደገበው ሁለት የብሔራዊ የጸጥታ ሠራተኞች ለትራምፕ ውግንና አላቸው በሚል ስጋት ለጊዜው ከስራቸው ዞር ተደርገዋል፡፡
በየኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በፀጥታ ስጋት ምክንያት የዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በዓለ ሲመት የሚፈፀመው ከ200 ሺህ በላይ ሰንደቅ አላማዎች በዝግጅቱ ስፍራ እንዲውለበለቡ በማድረግ ሲሆን ሰንደቅ አላማዎቹም በዝግጅቱ ላይ በአካል ለመታደም ያልቻሉትን አሜሪካውያን ይወክላሉ ተብሏል።
ትራምፕ ከነጩ ቤተመንግስት ጓዛቸውን ሸክፈው ለመውጣት እየተዘገጃጁ ባሉበት ቅጽበት ሲኤንኤን እንደዘገበው በ11ኛው ሰዓት ለ73 ያህል እስረኞች ይቅርታ ሰጥተዋል፡፡ ይቅርታውን ካገኙት መካከል በአንድ ወቅት የፖለቲካ ስትራቴጂስት የሆነ ግሰለብ እና ሁለት ስመጥር የሙዚቃ ባለሙያዎች ይገኙበታል ተብሏል፡፡
ግን ትራምፕ በተደጋጋሚ ካደረጉት ቅስቀሳ ጋር ተያይዞ በቅርቡ ደጋፊዎቻቸው አደባባይ ወጥተው ላደረሱት ጥፋት በይፋ “ኃላፊነቱን አልወስድም” ብለዋል፡፡ በአጭር አነጋገር ደጋፊዎቻቸውን “ሥራችሁ ያውጣችሁ” ብለዋቸዋል፡፡ ዛሬ አያድርስና ተመሳሳይ የሁከት ክስተት ቢፈጠር በዚህ ቃል ከተጠያቂነት ነጻ መሆን ይችሉ ይሆን?