የፊንጢጣ ኪንታሮት (Hemorrhoid)
—————————–
የፊንጢጣ ኪንታሮት ወይም ሄሞሮይድ የሚከሰተው በፊንጢጣ ውስጥ የሚገኙ የደም መልስ የደም ስሮች በደም ተወጥረው ሲያብጡ ነው።
የህመሙ ዋና ዋና ምልክቶች
የኪንታሮት ህመም ምልክቶች እንደኪንታሮቱ ቦታ የሚወሰን ሲሆን የውስጠኛው የኪንታሮት ዓይነት ብዙውን ጊዜ በዓይን የማይታይ ቢሆንም በሚፀዳዱበት ወቅት ማማጥ ካለዎ የደም ስሮቹ ሊቆጡና በቀላሉ ሊደሙ ይችላሉ። አንዳንዴ በሚያምጡበት ወቅት የውስጠኛው ኪንታሮት ዓይነት ወደታች በመምጣትና በፊንጥጣ ውስጥ በማለፍ ህመምና የመቆጥቆጥ ስሜት ሊኖረው ይችላል።
የውጪኛው የኪንታሮት ዓይነት በፊንጥጣ ዙሪያ ባለው ቆዳ ስር የሚገኝ ሲሆን የደም ስሮቹ በሚቆጡበት ወቅት ሊያሳክኩ ወይም ሊደሙ ይችላሉ።
አንዳንዴ ደም በውጭኛው ኪንታሮት ውስጥ በመጠራቀምና በመርጋት ከፍተኛ ህመም፣ እብጠትንና መቆጣትን/ መለብለብን ሊያመጣ ይችላል።
በሚፀዳዱበት ወቅት/ሰገራ በሚወጡበት ወቅት ከፊንጥጣ የሚወጣ ህመም የሌለው ደም/መድማት፡- ይህን ክስተት በመፀደጃ ሳህን ላይ ወይም በሶፍት ላይ ሊያዩ ይችላሉ።
- በፊንጥጣ አካባቢ የማሳከክ ወይም የማቃጠል ስሜት ካለዎ
- በፊንጥጣ አካባቢ ህመም ወይም ምቾት ያለመሰማት ካለዎ
- በፊንጥጣ ዙሪያ እብጠት ካለዎ
- የሰገራ ማምለጥ ካለዎ
እንዴት መከላከል ይቻላል?
ለኪንታሮት የሚያጋልጠው ዋነኛ ምክንያት የሆድ ድርቀት ነው።
በትንሹ በሳምንት 3 ወይም 4 ጊዜ ሠገራ የማይወጣ ከሆነ ሠገራ በትልቁ አንጀት ውስጥ ይደርቃል።
ለማስወጣት በጣም መገፋት ይፈልጋል ይህም ግፊት ደም ከፊንጢጣ የደም ስሮች ወደ ልብ እንዳይመለስ በማድረግ እዛው እንዲጠራቀም አድርጎ ኪንታሮትን ያመጣል ከነበረም ያባብሳል።
የሆድ ድርቀትን ለማስወገድ ምን ማድረግ ይቻላል?
- ፍራፍሬ እና አትክልቶችን አዘውትሮ መመገብ (ብዙ ፋይበር ስላላቸው)
- ቆስጣና ጎመን(የሀበሻ) መመገብ
ህመም እና ማሳከኩን ለመቀነስ
- ለብ ያለ ውሃ ሠፋ ባለ ዕቃ ሞልቶ ከ 10- 15 ደቂቃ በመቀመጫ መቀመጥ።
- ምንም ነገር ውሃው ውስጥ መጨመር አያስፈልግም።
- ያለሀኪም ትዕዛዝ የሚሸጡ የኪንታሮት ህመም ማስታገሻዎችን መጠቀም (በሚቀባ ወይንም በፊንጢጣ በሚገባ) ፋርማሲስቱ በሚመክረው መልኩ መጠቀም።
- ሀይድሮኮርቲሶን(hydrocortisone) በውስጣቸው የያዙ መድኃኒቶችን ከ1 ሳምንት በላይ መጠቀም አይመከርም።
ከላይ የተዘረዘሩት መድኃኒቶች ባያሽሉ
- በቀላል ቀዶ ሕክምና ኪንታሮቶችን ማጥፋት ይቻላል። ለዚህ ሀኪምዎን ያማክሩ።
- አንድ ጊዜ ኪንታሮት ጠፋ ማለት ተመልሶ አይመጣም ማለት አይደለም።
የባህል ህክምና መሄድ ይመከራል?
የባህል ህክምናው የተለያየ ቢሆንም በአብዛኛው ሲደረግ የምንመለከተው ያበጠ የሚመስለውን ቦታ በመሰንጠቅ ወይንም በመውጋት የተለያዩ ቅጠሎችን በመቅበር እንዲቆስልና ተቀርፎ እንዲወድቅ ማድረግ ነው።
በእርግጥ የተወሰኑ ሰዎች በዚህ ህክምና የዳኑ መሆኑን ቢናገሩም ብዙ ለስቃይ የተዳረጉ ሰዎች አሉ።
በተለይም ህመሙ የሚከሰትበት ስፍራ አብዛኛውን ጊዜ ንፅህናውን ያልጠበቀ ስለሚሆን ቁስሉ ለኢንፌክሽን ይጋለጣል።
መግል ይቋጥራል ያመረቅዛል። ይህም ለመዳን ረጅም ጊዜ እንዲፈጅበት ያደርጋል።
በዶ/ር ዳግም (ቴሌግራም ሃኪም)-
(ምንጭ፡-ቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል)