Connect with us

ታታሪዋን ከንቲባዬን አመሰግኑልኝ?!

ታታሪዋን ከንቲባዬን አመሰግኑልኝ?!
እሱባለው ካሳ

ነፃ ሃሳብ

ታታሪዋን ከንቲባዬን አመሰግኑልኝ?!

ታታሪዋን ከንቲባዬን አመሰግኑልኝ?!

(እሱባለው ካሳ)

ከንቲባኸን አየኸልኝ?… ገና አንተ ከእንቅልፍ ለመንቃት አልጋህ ውስጥ ስትገላበጥ እሷ ግን ቀድማ ነቅታ፣ ሰዎችን አስተባብራ፣ መጥረጊያዋን ይዛ ጃንሜዳ ተከስታለች፡፡ ሥራዋ የታይታ፣ የካሜራ ፍቅር አይምሰልህ፤ ከልብ ነው፡፡ እነታከለ ኡማ  ኮቪድ 19 ን ታከው የባህረ ጥምቀት ማደሪያ ቦታ ብድግ አድርገው ወደአትክልት ተራነት ከመቀየር አልፈው ቦታውን እንዴት እንዳግማሙት ለአንተ አልነግርህም፡፡ አትክልትን ያህል በቀላሉ አካባቢን ሊበክል የሚችል የገበያ ስፍራ ሲያዘዋውሩ በቂ መጠለያ፣ የመጸዳጃ ቦታ፣ የፍሳሽ እና የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ስፍራ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የመብራትና የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶች ሳይሟሉ በጥድፊያ ዝውውሩ መከናወኑ አሳዛኝ ነበር፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ በቦታው ላይ መብትና ጥቅም ያላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በጉዳዩ ላይ ምክር ሳትጠየቅ የተከናወነ መሆኑ ትልቅ የሕዝብ ቅሬታን ቆስቁሶ ከርሟል፡፡ በዚህም ምክንያት ሕዝበ ክርስቲያኑ “ቦታው የበዓል ማክበሪያዬ ነው፤ በሕግ አምላክ” የሚለው አቤቱታው ለወራት ሰሚ ሳያገኝ ዘግይቷል፡፡

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ይህን ስህተት ፈጥኖ ማረም ሕዝባዊ ተቀባይነቷን ከፍ እንደሚያደርገው ቀድማ ተረድታለች፡፡ እናም ወደጃንሜዳ የተዛወረውን የአትክልት ተራ መልሳ በማንሳት ቦታው እንደቀድሞው ለስፖርት እና ለጥምቀተ ባህር አገልግሎቱን እንዲሰጥ ላቧን እየዘራች ነው፡፡

ትላንት ምሽቱን ኃይሌ ጋርመንት አካባቢ ወደአሰራችው አዲሱ አትክልት ተራ ጎራ ብላ ሰራተኞችን እራት በመጋበዝ  “በርቱ ተበራቱ” ብላቸዋለች፡፡ ከንቲባዋ ኃይሌ ጋርመንት እግሯ እስኪቀጥን የተመላለሰችው ፕሮጀክቱ በአጭር ጊዜ እንዲያልቅ ካላት ብርቱ ፍላጎት ነበር፡፡ በእርግጥም ተሳክቶላት አሁን የኃይሌ ጋርመንት አዲሱ የአትክልት ተራ ስራ ለመጀመር የሚያስችል ቁመና ላይ አድርሳዋለች፡፡

አዳነች አቤቤ የሚያውቋት ለሥራ የተፈጠረች ጠንካራ ሴት ስለመሆኗ መስክረው አይጠግቡም፡፡ ያመነችበትን ነገር ከማሳካት ፈቅ የሚያደርጋት አንዳችም ኃይል የለም ይላሉ፡፡ በሰራችባቸው ተቋማት የቅርቦቹን እንኳን ብናይ ገቢዎች እና የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሰራተኛውን አስተባብራ ያከናወነቻቸው ግዙፍ ተግባራት ተቋማቱን አፍርሶ የመሥራት ያህል  የሚወሰድ ነው ሲሉ ያወድሷታል፡፡

እናም ታታሪዋ አዳነች አቤቤ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የጥምቀት በዓል እንደቀድሞው በታላቅ ድምቀት እንዲከበር ለማድረግ ፋታ የለሽ ሥራ ላይ ናት፡፡ ሰሞኑን የጃንሜዳው አትክልት ተራ ወደኃይሌ ጋርመንት አካባቢ የሚዘዋወር ሲሆን የጃንሜዳ ቦታም ጽድት ብሎና አምሮበት ከወትሮው በተሻለ ሁኔታ የዘንድሮ የጥምቀት በዓልን እንደሚያስተናግድ እየተጠበቀ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሰዎች በከንቲባዋ ያልተቋረጥ ጥረት መደመማቸውን ጽፈው አንብቤአለሁ፡፡ ግን ደግሞ ተያያዥ ጥያቄም አላቸው፡፡ በአዲስአበባ ብቻ ከስድስት በላይ ክፍለከተሞች የጥምቀት በዓልን ማክበሪያ ቦታ እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡ በከተማዋ የሚገኙ 40 ያህል የበዓል ማክበሪያ ቦታዎች ካርታ እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ ያቀረቡት ጥያቄና አቤቱታ እነሆ እስካሁን መልሱ ጥሪ አይቀበልም ሆኗል፡፡

ኦርቶዶክሶች ተስፋ አልቆረጡም፡፡ የወ/ሮ አዳነች አቤቤ አስተዳደር ልክ ለእሬቻ በዓል ማክበሪ ቦታ ፈጥኖ ካርታ አዘጋጅቶ እንደሰጠው ሁሉ ለኦርቶዶክሳዊን ጥያቄም (ምንም እንኳን የዘገየ ቢሆንም) አርኪ መልስ ይሰጣል ብለው አሁንም በተስፋ እየጠበቁ ነው፡፡

 

Click to comment

More in ነፃ ሃሳብ

Trending

Advertisement News.et Ad
To Top