በትግራይ 22 የልማት አውታሮችን ሲጠብቁ የነበሩ የፌደራል ፖሊስ አባላት እየተመለሱ ነው
ጥቅምት 24 ቀንን 2013 ዓ/ም ከምሽቱ 4፡00 ሰዓት አካባቢ ከሀዲው የህወዓት ጁንታ ቡድን ህገ-መንግስቱን በመጣስ የሀገር ሉአላዊነትን ተዳፍሮ መቀሌ ዙሪያ በሚገኙ በሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊትና በፌደራል ፖሊስ አባላት ላይ የክህደት ጥቃት ከፈፀመበት ጊዜ አንስቶ የሀገራችን የፀጥታ አካላት መቀናጀትና በመተባበር ጥቃቱን አክሽፈው በመልሶ ማጥቃት ህግን የማስከበርና የህልውና ዘመቻ አካሂደው የጁንታውን ታጣቂ ቡድን በከፍተኛ ልዕልና እና ወኔ እየተዋጉ በመደምሰስ በርካታ ድሎችን እያስመዘገቡ ያሉበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡
ከሀዲው የህወሃት ቡድን በሀገሪቱ ውስጥ የሴራ እንቆቅልሾችን ፈጥሮ በስውር በዘረጋው ወጥመድ ህዝብን በዘር በመከፋፈልና በመለያየት የተንኮል መርዙን በመርጨት ሀገር ሲያፈርስ ቆይቷል፡፡በአገራዊ የለውጥ ጉዞ ሁሉን ትተን በይቅርታ ወደ ፊት እንራመድ በሚል በፌደራል መንግስት ደረጃ ብዙ ጥረቶች ቢደረጉም ከሀዲው ቡድን ግን ለመቀበል ፈቃደኛ ባለመሆን በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ጥፋት ሲፈፅም ቆይቷል፡፡
ከዚህ አልፎም ቡድኑ በከተማ ውስጥ የጥፋት ተልዕኮውን ለመፈፀም ካቀደበትና ከተደረሰበት ጊዜ አንስቶ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በቀንና በለሊት በፖሊሳዊ ስልት፣ በሙሉ ትኩረትና ጥንቃቄ የፅንፈኛው ተላላኪዎች እኩይ ተግባር አስቀድሞ በማክሸፍ ለወንጀል ድርጊት ከሚጠቀሙበት የጦር መሳሪያዎች ጭምር በቁጥጥር ስር በማዋል የህዝብ አለኝታነቱን አረጋግጧል፡፡
በትግራይ ክልልም በዚህ እኩይ ቡድን የአፈናና የግድያ ወንጀል የተቃጣባቸው 22 የልማት አውታሮችን ሲጠብቁ የነበሩ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን አባላት በታላቅ ሞራል ከፍተኛ መስዋእትነት በመክፈል ጭምር ከፅንፈኛው ሃይል በማምለጥ በተለያዩ አቅጣጫዎች በእግር ተጉዘው ከወገን ጋር የተቀላቀሉ ሲሆን በግዳጅ ወቅት ተመድበው የተቋም ጥበቃ ተግባራቸውን ያከናወኑባቸው ተቋማትም፡-
Ø አሸጎዳ የንፋስ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ፤
Ø ተከዜ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ፤
Ø አፄ ዩሀንስ ቤተ መንግስት፤
Ø አሉላ አባ ነጋ፣ አክሱም፣ ሁመራ፣ ቱርካን ዳንሻና ሽሬ ኤርፖርቶች፤
Ø ዛሪማ፣ ማይጋባ የስኳር ማምረቻ ፕሮጀክት፤
Ø መቀሌና አዲግራት የነዳጅ ዲፖ፤
Ø የመቀሌ መረጃ ደህንነት መስሪያ ቤት፤
Ø መቀሌ ሀራ ገበያ ምድር ባቡር፤
Ø ራማ፣ ዛላንበሳ፣ መቀሌ እና ሉግዲ ጉምሩክ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎችና መሰል አካባቢዎች ናቸው፡፡
ግዳጃቸውን በሚገባ ተወጥተው የተመለሱት የፌደራል ፖሊስ አባላት ከ800 በላይ ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ በተጨባጭ 600 አባላት ከትግራይ ክልል ወጥተው በበየዳና በደባርቅ በኩል አድርገው ጎንደር ከተማ የገቡ ሲሆን 13 የተሰዉና 26 የቆሰሉ መሆናቸው ታውቋል፡፡
አባላቱ በጁንታው ቡድን ልዩ ሀይልና ሚሊሻያ ከመታገታቸው አስቀድሞ ከፍተኛ የሆነ ትንቅንቅ እንዳደረጉና ትጥቅና ዩኒፎርማቸውን አውልቀው እንዲሰጡ በፅንፈኛው ቡድን መጠየቃቸውን ጠቁመው፤ ይሁን እንጂ የሚደርስባቸው እንግልት ምንም ሳያሳስባቸው ዩኒፎርማቸውን ለጠላት አሳልፈው ከመስጠት ይልቅ ጠላት እንዳይጠቀምበት ሰብስበው ማቃጠላቸውን አስረድተዋል፡፡
ይህንን ተከትሎም ፅንፈኛው የህወአት ጁንታ ልዩ ሀይሉንና ሚሊሽያውን በመጠቀም በተያዙት አባሎቻችን ላይ አለም አቀፍ ስምምነቶችን በጣሰ ሁኔታ ጭካኔ የተሞላበት ግድያ፣ ግርፋትና፣ ሞራላዊ ስሜትን የሚጎዱ የተለያዩ እንግልቶችን ሲፈፅምባቸው እንደቆየና ከዚህ ሁሉ የተረፉትን ደግሞ በአውሬ እንዲበሉና በረሀ ላይ እንዲቀሩ ለማድረግ በከባድ የጭነት መኪናዎች አምጥቶ ተከዜ ወንዝ ላይ ቢጥላቸውም ረዥሙን በረሀ በእግር በመጓዝ አማራ ክልል በየዳ ወረዳ ገብተዋል፡፡
የመከላከያና የፌደራል ፖሊስ አባላቱ በየዳ ሲደርሱ የአካባቢው ነዋሪ የቆሰለውን በማከም፣ የተራበውን በማብላትና የታረዘውን በማልበስ ኢትዮጵያዊነታቸውን ያስመሰከሩበትና የኋላ ደጀን መሆናቸውን ያሳዩበትን ተግባር ፈፅመዋል፡፡
አጥፊ ቡድን ከመፈጠሩ አንስቶ በተንኮልና በጥላቻ የተሞላ ስለሆነ ባሳለፍናቸው ሁለት ዓመታት ብቻ በርካታ መሰሪ ተግባራትን ሲፈፅም ቆይቷል ያሉት አባላቱ። አሁን ግን ለመናገር እንኳን በሚከብድ መልኩ እንደ ወንድምና እንደአንድ ሠራዊት በምናያቸው የጁንታው ተላላኪዎች የተፈፀመብን ግፍ የፅንፈኛው የህወሃት ቡድን ለሀገርና ለህዝብ ደንታ የሌለው መሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ከተለያዩ ግንባሮች ከግዳጅ የተመለሱ የፌደራል ፖሊስ አባላት በፈጥኖ ደራሽ ሰሜን ዳይሬክቶሬት ካምፕ በአንድ እንዲሰባሰቡ ሲደረግ በወቅቱ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤልና የፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ም/ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፈንታ እንዲሁም የፌደራል ፖሊስ አስተዳደር ልማት ዘርፍ ኃላፊ ም/ኮሚሽነር ጀነራል ተኮላ አይፎክሩ ተገኝተው ከአባላቱ ጋር ውይይት አካሂደዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ከግዳጅ የተመለሱት አባላት ለሀገራቸውና ለህዝባቸው የከፈሉትን መስዋእትነት በከፍተኛ አመራሮቹ ፊት ከገለፁ በኋላ በትግራይ ክልል በተለያዩ ቦታዎች በመስራታቸው አካባቢውን ጠንቅቀው ሲለሚያውቁ በድጋሚ ወደ ክልሉ ተልከው የወንበዴው ቡድን የገባበት ገብተው ድባቅ ለመምታት እንዲችሉ ሀላፊዎቹን የጠየቁ ሲሆን ከፍተኛ አመራሮቹም የትኛውም መስዋዕትነት ተከፍሎ ጁንታውን ቡድን ከገባበት ገብቶ በመያዝና ለህግ በማቅረብ የተጀመረው ህግን የማስከበር ተግባር ግቡን እንደሚመታ ገልፀዋል።
የፌደራል ፖሊስ ሀይላችን ቀድሞ እንዳደረገው ሁሉ በቀጣይም ሀገሩን ከማንኛውም አይነት ትንኮሳ ለመጠበቅ በተጠንቀቅ ላይ ይገኛል፡፡
(ምንጭ :-የፌደራል ፖሊስ)